እግዚአብሔር ለሀገራችን ሰላሙን ያውርድልን!


እግዚአብሔር ለሀገራችን ሰላሙን ያውርድልን!
ከጋዜጠኛ ወሰንሰገድ መርሻ ደምሴ
 
 
ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌን(ደራሲ፣ተርጓሚ፣የታሪክ አጥኝና የቋንቋ ሊቅ) ከበፊት ጀምሮ ከማደንቃቸው ጸሐፍቶች ማካከል አንዱ ናቸው።
 
 በሚያነሷቸው ርዕሰችና ነጥቦች  የበርካታ ተደራሲያንን ቀልብ መሳብም ይችላሉ። ደፋር ናቸው  እስካሁን ድረስ በስደትም የቆዩት ይኸው ደፋርነታቸው ይመስለኛል።
   ፕሮፌሰር ጌታቸው በኢትዮጲስ ጋዜጣ የምሁራን መድረክ የሚለው አምድ ላይ ቋሚ አምደኛ በመሆናቸው እኔም  ጋዜጣዋን በየሳምንቱ ስለምገዛት  የሚጫጭሩትን ሀሳቦች ብዙውን ጊዜ አነባላው ።
 መቼም ውጭ ስላሉ በዚህ ድህረ ገጼ ወይንም ብሎጌ ላይ መልዕክቴ በቀጥታ ይደርሳቸዋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።
  ቀድሞ የሀገራችን መሪ በነበሩት በኮሎኔል መንግሥቱ፣በአቶ መለስና በአቶ ኃይለማርያም አስተዳደር ጊዜና በአሁኑ ወቅት ደግሞ በዶክተር አብይ አስተዳደር ጊዜ በመገናኛ ብዙሐን የሚያነሷቸው ሀሳቦች በጣም አራምባና ቆቦ ሆኖ ነው ያገኘሁት ።ያ ደፋርነታቸውና ሚዛናዊ የሆነ አስተያየታቸው ጠፍቶ ነው ያየሁት። ምናልባት አንዳንዴ እድሜ እየገፋ ሲመጣ መዘንጋት ብቻ ሳይሆን የፍራቻ መንፈስም አብሮ ስለሚመጣ ከዛ የመነጨ ነው ብዬ እንዳልደመድም አሁንም በስደት ላይ ነው የሚገኙት። 
  ከሀገራችን ተሞክሮ ስነሳ ዘራፍ ይል የነበረው ወጣቱ ትውልድ እንደዛሬ ብሄርተኛ ሳይሆን በፊት ለሀገሩ ከእሱ የሚጠበቀውን ያደርግ ነበር ። አሁን ግን እንደዛ አይደለም ብሄርተኛነት የተጠናወተ ጭፍን በግ ሆኗል። 
 የጦር መሪና አዋጊ የነበረው ደግሞ ትዳር  መስርቶ ልጆች ማፍራት ሲጀምር በፊት ከተነሳበት ዓላማና ግብ ወደ ኋላ ማፈግፈግ  ይጀመረበት ወቅት ላይ ደርሰናል። እንዲያውም አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍላችን « ቤተሰቤ እኔ ከሞትኩኝ ለእነሱ ማን አላቸው ?..» ማለት ከጀመረ አመታትን አስቆጠረ። በዚህም የተነሳ ወደፊት ከመጋፈጥ ይልቅ ወደ ኋላ ማፈግፈግ ጀማምሯል።
  በእርግጥ ውጭ ሆኖ መጻፍና ሀገር ውስጥ ሆኖ መጻፍ በጣም ከፍተኛ ልዩነት አለው። ውጭ ሆኖ እንደፈለገው ሲቸከችክና በየማህበራዊ ሚዲያ ላይና በፓል ቶክ ላይ  ሲለፈልፍ ቆይቶ ኢትዮጵያ ሲመጣ መጅራቷን እንደተመታች ውሻ ለአንድ ወርም ይሁን ከዛም በታች አሊያም ከወራትም በላይ በኢትዮጵያ ቆይታቸው በየቦታው ተልከስክሰው መሄድ ብቻ አይደለም ፤ተሸማቀውና  ብርድብርድ ብሏቸው ሀገር ቤት ገብተው እንደዛው ሆነው የሚመለሱ ጋዜጠኞች፣አክቲቪስቶች፣የፖለቲካ ሰዎችን ወዘተ. ለመታዘብ ችያለው ።
  ፕሮፌሰርን ግን እስካሁን ባያጋጥሙኝም  ውጭ ሆነው እየጻፉት ያለው ሁኔታ ግን መንታ መንገድ ላይ ያሉ አድርባይ ያስመስሏቸዋል። ብዙውን ጊዜ ዶክተር አብይን ሲያንቆለጳጵሱ ሌሎችን መሪዎች ደግሞ እታች አድርገው ሲረግጡ  ነው በጽሑፋቸው ላይ የምመለከታቸው ። ስለዚህ ነው ይህን ሀሳብ ለመጫጫር የወደድኩት።
  በእርግጥ ቋንቋ አዋቂ በመሆናቸው የሚጽፉት ጽሑፍ ቅኔ አዘል ነው እንዳልል የሚያነሱት ሀሳብ ልክ እንደ ቡዲዝም ኅይማኖት ተከታዮች እውነትነት ያለው፣ትክክለኛ መሆኑ የተረጋገጠ ምክንያታዊ አቀራረብ ነው ለማለት ይከብደኛል ። አንድ ምሳሌ ላንሳ።ኢትዮጲስ ጥቅምት 16 ቀን 2012 ዓ/ ም ባወጣው እትም ላይ «ሽልማት ዓይነቱ፥ ጥቅሙና ተጽዕኖው» በሚል ርዕስ በጻፉት ጽሑፍ ላይ «…የሰላም ሽልማቱን ያስገኘው በሁለቱ ሀገሮች መሪዎች(በዶክተር ዐቢይና በአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ) መካከል በተፈፀመው የሰላም ውል ስለሆነ፥ ሽልማቱ ለሁለቱም መሪዎች በኅብረት መሰጠት ነበረበት የሚሉ አንዳንድ ሰዎች አሉ።ግን አቶ ኢሳያስ አፈውርቂ በሂደት ውስጥ የሚሸለመው ምንም ሥራ አልሠራም።በሁለቱ ሀገሮች የነበረው ሰላም የደፈረሰው የኢትዮጵያ የአልጀርሱ ውሳኔ ለኤርትራ የሰጠውን መንደር አላስረክብም ስላለች ነበር።ድምበር ላይ መፋጠጥ ተወግዶ ሰላም ሆነ።ኤርትራውያን ወደ ኢትዮጵያ ጎረፉ።በተፈጠረው ሰላም ዋናው ተጠቃሚ ኤርትራ ነች። የኢትዮጵያ ጥቅም ወታደሯቿን ከወሰኑ ላይ ማንሳት ብቻ ነው። አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ለጥቅሙ የዋለውን ዕርቅ አልቀበልም ሊል አይችልም ነበር።...»እያለ ጽሁፋቸው ይቀጥላል።
  በአንድ ወቅት ለጀርመን ራዲዮ ከጃፓን ስዘግብ በኤርትራ የጃፓን አምባሳዳርን አናግሬያቸው ነበር።በኢትዮጵያና በኤርትራ ድንበር ጉዳይ የጀርመን ሬዲዮ አብዛኛዎቹ ጋዜጠኞች ከኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን በኮንትራት የሄዱ የኢህአዲግ  አፍቃሪዎች ስለነበሩ ቃለ ምልልሱን ባያቀርቡልኝም (ስሟን ለጊዜው መጥቀስ የማልፈልገው ባሏ የኢህአዲግ አባል ሌላ ሰው ቃለመጠይቅ ያደረግነው ስላለችኝ ነው ቃለ መጠይቁ ያልተሰራው ። እኔም ባዛው ዘጋቢኔቴን አቁሚያለው) 
  ፕሮፌሰር እንዳሉት የኢትዮጵያ መንደርን ኤርትራ አልሰጥም ስላለች ሳይሆን ኤርትራውያኖች የሚሉት የተባበሩት መንግስታት የወሰነው ውሳኔ ባድሜ የኤርትራ ስለሆነ የፀጥታው ኮሚቴ የወሰነው ውሳኔ ተግባራዊ ይሁን የሚል አቋም ነው የነበራቸው  ።
 ይሁንና ኤርትራውያን ይህንን ድርቅ ያለ አቋማቸውን የቀየሩት  በዶክተር አብይ አመራር ጊዜ ነው።ግን እሳቸው ብቻቸውን ሳይሆን በአቶ ኢሳያስ ቀና አመለካከት መሆኑን ፕሮፌሰር እስካሁን ድረስ አለመገንዘባቸውን ከጽሑፋቸው መረዳት ብቻ አይደለም  እንደ አገኙት የትምህርት ደረጃና  ማዕረግ  ስለሚናገሩት ነገር ተአማኝነት አሳማኝ የሆኑ ማስረጃዎችን ሳያጣቅሱ ማቅረባቸው ደግሞ በጣም ያሳዝናል።
 በኤርትራና በኢትዮጵያ ያለውን አለመግባባት አቶ ኃይለማርያምም ብዙ ጥረት አድርገዋል ከገዥው ፓርቲ ድጋፍ ብዙ ስላላጉኙ ያደረጉት ጥረት ባይሳካም ድርድሩ እልባት እንዲያገኝ ብዙ ለፍተዋል ። 
  የዶክተር አብይ ጥረት የተሳካው ከገዥው ፓርቲ ሙሉ ድጋፍ ስላላቸው ነው ድርድሩ የተሳካው ብል አልተሳሳትኩም ። በእዚህ ላይ አቶ ኢሳያስም ፍቃደኝነታቸው ባይኖር ኖሮ በተለይም በሕወሀትና በቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብና ስልጣን ላይ ባለው አመራር አካላት ያለው የፖለቲካ ቁማር ጨዋታ እንዲሁም በኢህአዲግ አባል ድርጅቶች መከከል ፊትና ጀርባ መሆን ለሁለቱም ወገኖች ለድርድሩ መሳካት ከፍተኛ አስተዋጾ አድርጓል።  
 ብዙውን ጊዜ ኦሮሞዎች በተለይም ቄሮና ጁሀር ለውጡን በኢትዮጵያ ያመጡት እነሱ እንደሆኑ ይናገራሉ። ይሁንና ይህ ስእተት  መሆኑን  የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከዶይቼ  ቭሌ (DW) ቴሌቪዥን ጣቢያ  “ኮንፍሊክት ዞን” ከተባለ ፕሮግራም ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ ገልጸዋል።እሳቸው ለውጡን ስለሚፈልጉ እንጂ አምባገነን ቢሆኑ ስልጣኑ በእጃቸው ስለሆነና የመከላከያም ሆነ የፖሊስ ሠራዊቱ በእሳቸው የሚመራ ስለሆነ «አለቅም ማለት እችል ነበር !» ብለዋል። “አምባገነን ተብዬም ልጠራም አይገባኝም” በእሳቸው  የስልጣን ዘመን ስለተፈጸሙ ግድያዎች፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና የሙስና ወንጀሎች ተጠያቂ እንዳልሆኑም  ገልፀዋል። እንዲያውም እነዚህን ጉዳዮች በተመለከተ የደህንነት ባለስልጣኖቻቸው በወቅቱ በቂ መረጃ ይሰጧቸው እንዳልነበር ነው የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር የተናገሩት ። 
በኢትዮጵያ አሁን ያለው የለውጥ ሁኔታ እንዲመጣ የራሳቸውን ድርሻ መወጣታቸውን ነው  የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሰመሩት “እኔን አምባገነን አድርጎ መሳል ትክክል አይደለም” ማለታቸውን ሰምተናል።
  እንደነ ፕሮፌሰር ያሉት ሙሁራኖች ደግሞ ለውጡን ያመጡት ዶክተር አብይ ብቻ፤ የኢትዮጵያና የኤርትራ ችግር የተፈታው በዶክተር አብይ  ብቻ ፤ የለውጥ አዋርያው ዶክተር አብይ ብቻ…ብላ ብላ ሲሉ። በአንፃሩ ደግሞ ቄሮና  ጁሀር ለውጡን ያመጣነው በለማ ቲም የሚመራው ቡድን ነው ይሉናል። 
  እንደኔ አይነቱ ምስጊን ሕዝብ ደግሞ ምንም  ለውጥ እስካሁን አላየንም እንዲያውም በርካታ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ የዩንቨርስቲ ተማሪዎች በዲግሪና በዲፕሎማ  ተመርቀው ሥራ ፈት የሆኑበት ፤ ስራተ አልበኝነት የበረከተበት በተለይም  አዛዥና ታዛዥ የሌለበት ጊዜ ላይ መሆናችንን ነው የማውቀው። በዚህም የተናሳ አብዛኛው ሰው የአቶ መለስ አስተዳደርን መናፈቅ የጀመረበት ጊዜ ላይ ደርሰናል። በእርግጥ በእሳቸው ጊዜ  ቤተክርስቲያን ሲቃጠል አላየንም  ፤መንፈሳዊ አባቶች እንደ በግ የሚታረዱበት፤ሰዎች በብሄር የተነሳ ከአካባቢው የሚፈናቀልበት፤ሰዎች  በሰላም ወጥተው  በሰላም መግባት ያልቻሉበት ወቅት ላይ አልነበርንም ። 
  ለእኔ ከዶክተር አብይ አስተዳደር ይልቅ የአቶ መለስ አስተዳደር ይሻለኛል። ምክንያቱም በአብዛኛው አሁን እየታየ ያለው ችግር በእሳቸው የአመራር ዘመን  አልነበረም።እርሶ ውጪ ስለሆኑ ኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ የወሬ ወሬ ሰምተው ነው እንደመሰለኝ የሚጽፉት  ስለዚህ የሕዝቡን ችግርና መከራውን አብረው ቢቻል ኢትዮጵያ መጥተው  ቢጽፉ ይመረጣል።ደግሞ ለየትኛው ዕድሜ  ፕሮፌሰር ? በእርግጥ ሰው እያረጀ ሲሄድ ዕድሜ ያሳሳል ይላሉ አባቶች እውነት ይሆን?

 

  ለማንኛውም አክቲቪስቶች ፣የፖለቲካ አመራሮች፣የመገናኛ ብዙሀኖች፣ ሙሁራኖችና ሌሎችም ለዚች ሀገር ምስቅልቅል ማለት በሕዝብ ፊት ከተጠያቂነት አታመልጡም። የሰላም አምላክ የሆነው እግዚአብሔር ለሀገራችን ሰላሙን ያውርድልን ።አበቃው! ክብረት ይስጥልኝ!