ሥጋት ያንዣበበት ሀገራዊ ምርጫ!


 

ሥጋት ያንዥበበት አገራዊ ምርጫ 
 
 ከጋዜጠኛ ወሰንሰገድ መርሻ ደምሴ
 
   እንደምን አላችሁልኝ ውድ አንባብያኖቼ ለመሆኑ ስለ ተርቡት(ተርብ)ምን ያህል እውቀቱ አላችሁ?ብዘዎቻችሁ እከሌ እኮ ተርቡት(ተርብ)ነች ሲባል ሰምታችሁ ይሆናል።
  ተርቡት(ተርብ) የምትባለው በራሪ ነፍስ ስትሆን እንደ ማር ዐይነት ታበጃለች ነገር ግን በውስጡ ምንም አይገኝበትም ።በቤቷም ውስጥ በያይነቱ  ትል ይገኛል።በመና(ን)ደፍም  ከንብ እጅግ ትከፋለች ፤ መርዟ ከሷ አይለይምና  ...የተርብ እንጀራ የበላ ውሻ ክፉ ይኾናል። 
  እናም እከሌ እኮ  ተርቡት
(ተርብ) ነች ካለን እንደ ሴቶች ትጠምቃለች ፣ትጋግራለች ፣ድግሷ ጣዕም የለውም  ፣ ባሏ ቢመታትም መልሳ ትመተዋለች ፤ አሸር ባሸር ሰርታ «ከፈለክ ብላ ካልፈለክ ተወው » ብላ ታቀርባለች፤ በመሰናዶዋ ሁሉ ጉድፍ ይገኝባታል። 
   ለወንድ ብዙ ጊዜ ቃሉን ባንጠቀምበትም ። ቃሉን ያለቦታው እንሸነቅርና ሌላ ትርጉም ሲሰጠው እንሰማለን «እከሌ ተርብ ነው » እንልና ጎቦዝ ሥራ ላይ ፈጣን እንደሆነ ተልኮ ፈጥኖ የሚደርስ የሚመስለን  በርካቶች ነን ። ከላይ ከቀረበው ትርጓሜ አንፃር ግን ተርቡት(ተርብ)
የምንለው ክፉ የሆነ፣ ጨቅጫቃ፣ በሥራው ስውን የማያረካ ፣ቶሎ ተናዳጅና ለፀብ ቶሎ የሚፈጥን ሰው ወዘተ. የሚል ትርጉም እናገኛለን።
  ከተርቡት(ተርብ) የባሰም አለ ዝንቡት (ዝንብ) ይህን ቃል ከላይ እንደተጠቀሰው ለወንድ ሳይሆን ለሴት ነው የምንጠቀመው «እከሌ እኮ ዝንቡት ነች ! » ካልን ካገኘችው ወንድ ጋር የምትተኛ ሴት ወይንም አመንዝራ ሴት ነች። እንደማለት ይቆጠራል።
  እንደሚታወቀው ዝንብ ከማንኛውም እንስሳ ላይ  ቁስልና መግልን ደምና ዕድፍን ሁሉ የምትቀስም ናት ያረፈችበት ነገር ሁሉ የሰው ልጅ ይጸየፈዋል። ያንዱን ቁስል ቀሥማ ላንዱ ታጋባለች ባቄላ በተሰበረ ጊዜ አገዳ ውስጥ ገብታ ትደበቃለች። 
  ዝንብ የምትውልባቸውን ነገሮች  ስንጽፍ የምታነቡት አንባቢያኖች እንዴት እንደተፀየፋችሁ ተስፋ አድርጋለሁ ።
  ዛሬ በሀገራችን  እንደ ተርቡት(ተርብ)እና እንደ ዝንብ የሆኑ ሰዎች በሀገራችን ውስጥ በርካታ ናቸው ። እንዲያውም ኃላፊነት ቦታ ላይ በአብዛኛው የሚቀመጡት እንደነዚሁ አይነቱ ሰዎች ናቸው። ወደ አንድ መሥሪያ ቤት ጉዳይ ሊያስፈፅሙ ጎራ ያሉ እንደሆነ በቅንነት እርሶን ከሚያስተናግዶት ሰው ይልቅ ።እንደ ተናካሽ ውሻ በስድብና በግልምጫ ከእራስ እስከ እግሮት እታች አድርሰው እላይ  የሚገላምጦት በርካቶች ናቸው።
 በተለይም ሸገር  አውቶብስን ታዝበው ከሆነ ለመሳፈር ተራዎትን ጠብቀው ለመግባት ሲሞክሩ ትኬት ቆረጩ(ጯ) ወርዳ(ዶ) መቁረጥ ሲገባቸው እንደባለስልጣን ወንበር ላይ ተቀምጠው ሰውን እያባሉና ለሌቦች ሲሳይ እያዳረጎት ትኬት የሚቆርጡም የጠገቡ ትኬት ቆራጮች አሉላችሁ ። አለፍ ሲሉ ዝርዝር ካልያዙ የቆረጡ ትኬት ላይ መልሱን ከጻፉ በኋላ ሲወርዱ እንደሚሰጦት ይነገሮታል። ታዲያ ወይ የተበጫጨቀ ብር ከደና ብር ጋር ቀላቅለው ይሰጦታል። ወይንም ደግሞ መልሰቶትን ሳይቀበሉ ዘንግተውት ጥለውት ለመውረድ ይገደዳሉ። 
  የሸገር አውቶብሶችን 
 ውስጡን ካዩ ደግሞ ወንበሮቹ ዝናብ ከጣራውና ከመስኮቱ ስር በተንጠባጠበ  ወንበር
 ላይ ተቀምጠው ሱሪዎት ወይንም ቀሚሶት የተባላሸቦትም አይጠፉም። በተለይም ከመጨረሻው ኋላ ወንበር ላይ ያለው አቧራ ጉድ ያሰኛል።
  አንዳንድ መስኮቶቹ የሚያፀዳቸው አጥተው በጭቃ ለብሰው ሲታዩ ባለቤት የሌላቸው ይመስላሉ።በዚህ ላይ እስከ ፑንት ጠቅጥቀው ይዘው ይሄዱና ሲመለሱ ሰው ሳይዙ ባዶ  የሚመለሱ አውቶብሶች ማየታችን  የሚያሳዝን ነው።
  የተገዙት የሸገርም ሆነ የአንበሳ አውቶብሶች የሚያፀዳቸው አጥተው ካለ ጊዜያቸው ያረጁ መምሰላቸው  የተርቡት(ተርብ)ምሳሌን የሚያመለክት ነው።
በሰለጠነው ዓለም ያሉት
  አውቶብሶቹ ሀገራችን ካሉት ጋር ተመሳሳዮች  ናቸው።
 ይሁንና የፅዳታቸው ነገር ግን አይነሳ አራምባና ቆቦ ነው። አውቶብሶቹን የሚያጸዱት አሽከርካሪዎቹ(ሹፌሮቹ) ናቸው።በዚህ ላይ የትኬቱንም ሥራ የሚሰራው እራሱ ሹፌሩ ነው።
እነሱ ሀገር የተመቻቸ መንገድ ስላላ፤ሀገራቸው አፈርና ጭቃ ምናምንትሴ ስለሌለ ሊባል ይቻላል። ይህ አይደለም ለምሳሌ ቤት ውስጥ የምንጠቀምባቸው የተለያዩ ዕቃዎች ንፅእናቸው ካልጠበቅንላቸው ተበላሽተው ከጥቅም ውጭ ነው የሚሆኑት የምንጠቀምባቸውም አውቶብሶች እንደዛው ናቸው መገልገል ብቻ ሳይሆን ንጽእናቸውን መጠብቅና ማስጠበቅ የሚመለከታቸው ወገኖች ኃላፊነት ይመስለኛል  ለማለት ነው።
  ሌላው ኢትዮጵያ ውስጥ አጭበርባሪ ስለሚበዛ ትኬት ቆራጭ መኖሩ አያስከፋም። ይሁንና ጠዋት የያዘው ሹፌርና ትኬት ቆራጩ ብዙ ተገልጋይ በሌለበት ሰዓት ላይ ከ4 ሰዓት እስከ 7 ሰዓት ወይንም ደግሞ ከሰዓት የያዘው ደግሞ ከ 8 ሰዓት እስከ 10 ሰዓት በየተራ አውቶብሶቹን  የሚያፀዱበት መንገድ ቢፈለግ ለእኛም ለተገልጋዮቹም ለእራሳቸውም ጤንነት መልካም ይሆናል ባይ ነኝ።በዚህ ላይ ሥራ አጥ በበዛበት ሀገራችን ውስጥ የሥራን ባህልን  ከመዳበሩም ባሻገር ሳይሰሩ ደመወዝ ከመቀበል ደክመውና ለፍተው ደመወዛቸውን ቢቀበሉ ከሕሊናም ተጠያቂነት መዳን ይቻላል። ተሳሳትኩ ጎበዝ ?
 እንድው ስለ አውቶብሶቻችን አነሳው እንጂ አዲስ አበባችን ብዙ ጉድ ይዛለች ሌላው ቀርቶ ዝናብ የሚያስገቡ የሸራ ወይንም የላስቲክ ቤቶች ዛሬ ወደ ቦሌ ሚካኤል  900 ብር  ወደ ዋና ዋና ከተማ የሆኑ አካባቢዎች ስራ አሉ ወደ ተባሉ ቦታዎች እስከ 2000 ብር የጪቃ ቤት አየር ጤና የመሳሰሉ እስከ 900 ብር ወደ ጀሞ እስከ 1500 ብር ከክፍለ ሀገር ከሲዳማ፣ከወላይታ ወዘተ ለሚፈልሱ ሊስትሮ፣ጀብሎ፣ሻይና ቡና ፣ሽንኩርት ወዘተርፈ ለሚቸረችሩ ለሶስትና ለአራት እየሆኑ ማከራየት አዲስ አበባችን ውስጥ ከተጀመረ ሰነባበተ ።ለሥራ እያሉ ወደ ከተማ የሚፈልሱትም እነዚሁ የደቡብ፣ የኦሮምያ እንዲሁም የአማራ ክልል ተወላጆች ትምህርታቸውን እየተዉ እንደሆነም  ያጫወቱኝም አልጠፉም። የነገ ሀገር ተረካቢ የሚሆነው ትውልድ ምን ይሆን ገንዘብ ወይስ እውቀት? ለመሆኑ ወዴት እያመራን ነው? 
  እንደው ስለ ተርቡት(ተርብ)
ካነሳው አይቀር እግረ መንገዴን ላንሳው ብዬ እንጂ የዛሬው የርዕሴ አቅጣጫ "ሥጋት ስለ አንዥበበት አገራዊ ምርጫ" ነው። 
  
  የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ  ከተርቡት(ተርብ) ይሁን ወይንም ...ከየትኛው ወገን እንደሆነ ፍርዱን ለእርሶ ልተወውና የ2012 ዓ/ም ምርጫ  ዙሪያ የምለው ይኖረኛል። ምርጫው ዘንድሮ ይከናወናል።በዚህ ምርጫ ለየት የሚያደርገው የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት የኢህአዲግ ተቃዋሚ የነበሩት ወ/ት ቡርትካን ሚዴቅሳ መሆናቸው፤ኢህአዲግ  ተከፋፍሏል መባሉና አሸባሪ የተባሉት ኦነግና ግንቦት 7 ጨምሮ ሌሎች ፓርቲዎች በምርጫው ላይ መሳተፋቸው ብቻ ነው። 
  የዘንድሮው ምርጫ በተያዘለት ጊዜና ወቅት እንደሚካሄድ ምርጫ ቦርድ አሳውቋል። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ከዚህ በፊት በመገናኛ ብዙሀን በኢትዮጵያ ስለሚካሄደው ምርጫ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ «..በምርጫ ቦርድ ስራ ውስጥ መንግስታቸው ጣልቃ እንደማይገባ ፤ የምርጫ ቦርድ ምርጫው መካሄድ አለበት ብሎ በወሰነው ውሳኔ መሰረት ምርጫው እንደሚከናወን…»ገልጸው ነበር።
   ከዚህ አንፃር ምርጫ ቦርድ ያለ ተፅእኖ እየሰራ መሆኑን እንዲሁም ምርጫው ዘንድሮ እንዲካሄድ የወሰነው  መንግስት ሳይሆን የምርጫው ቦርድ ውሳኔ መሆኑን ያሳያል። 
  የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ጠቋሚነት በምክር ቤቱ አፅዳቂነት ስልጣናቸውን  ይዘው ሥራቸውን ከጀመሩ አመት እንኳን አልሞላቸውም ። ከዚህ አንፃር ምርጫው ከመከናወኑ በፊት ብዙ ነገር ሰርተዋል ማለት ይከብዳል። 
  ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ይካሄዳል ብለው ሲወስኑ በሀገሪቱ ውስጥ እየታዩ ያሉ የፖለቲካ አለመረጋጋትና በየቦታው የታዩ ግጭቶች፣የፖለቲካ ፓርቲዎች መበራከት፣ጽንፈኞችና የፖለቲካ መካረር ፣የሀገሪቱ መንግስት በአንዳንድ ቦታዎች እየታዩ ያሉ የአስተዳደር ችግሮችን መቆጠጥር አቅቶት በኮማንድ ፖስት እየተዳደሩ የሚገኙ ቦታዎች መኖር፣በየክልሉ እንደ ቄሮና ፋኖ የመሳሰሉ ሕገወጥ ማህበራትና አደረጃጀት መበራካት ፣ወደ ሀገር ቤት የገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በቂ ዝግጅት አለማግኘታቸው ፤ ምርጫው ፍትሐዊና ዲሞካራሳዊ እንዳይሆንና ሕዝብ ያላመነበት ምርጫ እንዳይመሰረት ያደርገዋል ። የሚባሉትን 
የተለያዩ የሙሁራኖችና የኅብረተሰቡን አስተያየቶች ተቀብለው መፍትኤ ለማድረግ ምርጫ ቦርድ ጥሯል ወይ ? ብለን እንድንጠይቅ ያደርገናል። 
  የተለያዩ የክልል ርዕሰ መስተዳደሮችና ፕሬዝዳንቶች  በአዲስ አመት መግቢያ ላይ የጠቆሙትም ይህንኑ የሚያሳይ ነው። 
  መጥቀስ ቢያስፈልግ የትግራይ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳደር  ዶ/ ደብረጽዮን ገብረሚካኤል «…በሀገሪቱ በተፈጠረው ችግር እያንዳንዱ ድርጅትና አመራር የየራሱን ድርሻ መውሰድና በመፍትሄው ላይ ተባብሮ መስራት ተገቢ ነው።ነገር ግን ይህ አልተፈፀም …» ሲሉ ፤ የኦሮሚያ ክልል ም/ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ «…ከዚህ በፊት ትጥቅ ለመፍታት ፍቃደኛ ያልሆኑ በድቡብና በምዕራብ ኦሮሚያ በሚገኙ ኃይሎች ላይ እርምጃ በመውሰድ የኅብረተሰቡን ሰላም ማስፈን ተችሏል። …ዜጎችን ከቀያቸው የሚያፈነቅሉ ወገኖች እርምጃ ተውስዷል።...የፖለቲካ ፓርቲዎች ከፖለቲካ ዘረኝነት አለመውጣታቸውና መጠላለፋቸው ዋንኛ ችግር ሆኗል።             በተጨማሪም ብሔርተኛና ኅይማኖትን መሠረት ያደረገ ፅንፈኝነትን ከሕግ ውጭ ፍላጎትን ለማስፈፀም የሚደረግ ተስተውሏል።...»ብለዋል።
  የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ አሻድሊ ሐሰን «...ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በክልላችን እየተከሰተ ባለው አለመረጋጋት የሰዎች መፈናቀልና ግድያ ወንጀሎችን ለመካለካል ከአጎራባች ክልሎች ጋር በመቀናጀት በጋራ መስራትና በየደረጃው ከሚገኙ የኅብረተሰቡ ክፍሎች ጋር በመወያየት ሰላምን ማስፈን የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ በተለየ ትኩረትና በላቀ ቅንጅት የሚፈፀም ይሆናል።...» 
  የደቡብ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ እርስቱ ይርዳው «...በክልላችን ባለፈው አመት ብዙ ችግሮችን  ያሰለፍንበት ዘመን ነው። ...የፀጥታ ችግሮች ምክንያት  የክልላችን ሕዝቦች ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍለዋል።በከፍተኛ ሁኔታ ሥጋት ላይ ወድቀዋል።..» ሲሉ የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ተመሰገን ጥሩነህ «...ባለፉት ጥቂት ጊዜያት የተሻለ አንፃራዊ ሰላም ያላገኘንበት ነው።በ2011 ዓ/ም የክልላችንን ፕሬዝዳንት ጨምሮ ሌሎች አመራሮችን ያጣነበት ጭምር ነው። ስለዚህ በቀጣዩ አመት ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል...» ብለዋል።
  ከዚህ ከክልል ፕሬዝዳንቶችና ርዕሰ መስተዳድሮች የአዲስ አመት መልዕክት አንፃር በየክልላቸውን ያለውን ችግር ለመፍታት ጊዜ የሚያስፈልጋቸው ሆኖ ነው ያገኘሁት ። ይህ ብቻ አይደለም  ከስደት ወደ ሀገር ቤት የገቡት  ተቀዋሚ  ፓርቲዎች  ከኅብረተሰቡ ጋር ለመተዋወቅና በመሐከላቸው ያለውን አለመግባባት ለመፍታት ጊዜ ያስፈልጋቸዋል። ሕጋዊ የማህበር እውቅና የሌላቸውና ትክክለኛ ያልሆነ አካሄድ እየሄዱ ያሉትን እንደ ቄሮና ፋኖ የመሳሰሉ የወጣቶች ስብስብ ከዚህ በፊት ካየነው ተሞክሮ አንፃር ለሀገራችን ብጥብጥና እረብሻ መንስኤዎች ስለሆኑ ሕጋዊ አካሄድን እንዲከተሉና እንዲጓዝ መስመር እንዲይዙ ማድረግ ያስፈልጋል።
 በየክልሉ እየታዩ ያሉ የሰዎች መፈናቀልና ግድያ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት ማግኘት ይኖርበታል።
  የምርጫ ሕጉ ስር ነቀል ለውጥ ተደርጎበታል ወይ?ገለልተኛና የፍርድ ቤቶች አካላት በሀገሪቱ ውስጥ አሉ ወይ? የፖለቲካ አለመረጋጋት፤  በየቦታው የሚታዩ ግጭቶች ተፈተዋል  ወይ ብለንም መጠየቅ ያስፈልጋል።
   በተለይም የምርጫ ሕጉ ላለፉት ሁለት አሥር አመታት የገዥውን የወያኔ/ የኢህአዲግ  ፓርቲን የሚረዳ እንጂ ለሕዝብ የቆመ እንዳልሆነ ከዚህ በፊት ያየናቸው የሕዝብ ተቃውሞና እረብሻ የዚሁ መንስኤ ውጤት ነው። በመሆኑም የምርጫ ሕጉ ስር ነቀል ለውጥ  መደረግ አለበት።ከዚህም ሌላ ገለልተኛና የፍርድ ቤቶች አካላት በሀገሪቱ ውስጥ እንዲኖሩ ማድረግ የኅብረተሰቡ ብቻ ሳይሆን የመንግስት አካላትም ኃላፊነት ጭምር ነው ።ለዚህ ደግሞ በሜዳው ላይ ገዢው ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚውም የሚጫወቱበት ኳስ እኩል ሊሆን ይገባል።
   ምርጫው ከመካሄዱ በፊት ሌሎችም ሊስተካከሉ የሚገቡ ነገሮች አሉ ። በፖለቲካ ፓርቲዎችና በኅብረተሰቡ መካከል ያሉ ልዩነቶችና ግጭቶች የሚፈቱበት መንገድ መፈለግ ይኖርበታል።
 በአንዳንድ ክልሎች ያሉ እየታዩ ያሉ የወሰን ጉዳዮችና በኅይማኖት ዙሪያ የሚነሱ አለመግባባቶችና ግጭቶች መቆም አለባቸው። በወሰን ጉዳይ ላይ ያሉ ችግሮች ለመፍታት የሀገራችንን ፍኖታ ካርታ ከየት ተነስቶ እስከ የት እንደሆነ በግልፅ ማሳወቅ፤ በዚህ ፍኖተ ካርታ ላይ የክልሎችንም የየገባኛል ሁኔታ መፍታት ፤የምርጫ ሕጉ ስር ነቀል በሆነ ሁኔታ የሀገራችንን ነባራዊ ሁኔታ በአገናዘበ መልኩ እየታየ ያለውን የፖለቲካ ትኩሳት ሊያበርድ በሚችል መልኩ ለውጥ መደረግ አለበት  የሚል እምነት አለኝ።
  አንዳንድ የታጠቁ ኃይሎች በሰላማዊ መንገድ ትጥቃቸውን አውልቀው ከኅብረተሰቡ ጋር እንዲቀላቀሉ ማድረግም ከምርጫው በፊት ሊደረግ የሚገባው ነገር ነው። የፖለቲካ አለመግባባቶች  በፓርቲዎች መካከል የሚፈታበት መንገድም ሌላው ዋንኛው አንገብጋቢ ጉዳይ ነው።
  በመሆኑም የ2012 ዓ/ም አገራዊ ምርጫ  ከመከናወኑ በፊት ያንዥበበውን ሥጋት ማስወገድ ከወዲሁ ይገባል እላለው  አበቃው።ክብረት ይስጥልኝ።