የሩዋንዳን የዘር ማጥፋት ስናስታውስ ሀገራችንን አንዘንጋት !


 

ከወሰንሰገድ መርሻ ደምሴ

(ደራሲ፣ጋዜጠኛና ማህበራዊ ሀያሲ)

 ሩዋንዳ  በሀገሯ  ላይ  ላይ የተፈፀመውን የዘር ጭፍጨፋ አክብራለች። በሁቱና በቱትሲ መካከል በተነሳው ግጭት  ሀገሪቱን ሲመራ የነበረው  የሁቱ ጎሳ አባሎች በቱትሲ የጎሳ አባሎች ላይ ከ800 ሺህ በላይ ያደረሱትን ጭፍጨፋ በሌላ ሀገር ላይ እንዳይደገም  በተዘጋጀው  በዚህ የመታሰቢያ  በዓል ላይ  የኢትዮጵያውን ጠቅላይ ሚኒስትር ጨምሮ ሌሎች የአፍሪካ ሀገር መሪዎችም  ተገኝተዋል። ይሁንና በአንዳንድ  አፍሪካ ሀገሮች ኢትዮጵያን ጨምሮ ያላባራው የዘር ማፅዳት ዘመቻው አሁንም እንደቀጠለ ነው ።ለመሆኑ ይህን የዘር ማጥፋት ዘመቻ እንዴት ማቆም ይቻላል።ከሩዋንዳስ ምን እንማራለን በሚለው ርዕሰ ዙሪያ ዛሬ ያተኮርኩበት የብዕር አቅጣጫዬ ይሆናል።እንደምን ከረማችሁልኝ ውድ አንባቢያኖቼ ! 

 አልጀዚራ  ሰሞኑን  ባቀረበው  ይህንኑ የሩዋናዳ ጭፍጨፋ በተመለከተ  ካቀረበው ዘገባ እንነሳ ። ሙካሬሜራ ላውረንስና ንኩንዲዬ ታቺን ከ30 ዓመታት በላይ ጓደኛሞች ነበሩ።በፊት አብራው ብዙ ነገር ያሳለፉ  ቢሆንም በተለይም ባሏን እንዴት አድርጎ ጓደኛቸው እንደገደለው  ለመናገር ፈልጎ  አንገቱን ወደ መሬት  አቀረቀረ።

ሦስቱም ጎረቤታሞችና የዕድሜ ልክ ጓደኞች ነበሩ፣ በሩዋንዳ ምቢዮ መንደር አብረው ይኖሩ ነበር። ግን በ1994 እ.ኤ.አ ታሲን ጓደኛውን እንዲገድል ትእዛዝ ደረሰው ። ታሲን ለአልጀዚራ እንደተናገረው « የደረሰኝ ትእዛዝ ነበር። የተባልኩትን ካላደረኩ ቤተሰቤ እንደሚገድሉብኝ አስፈራርተውኛል፣ስለዚህ ይህን ማድረግ እንዳለብኝ  ተሰማኝ።» ይላል።

በወቅቱ ሩዋንዳን ይገዛ የነበረው አብላጫው  የሁቱ ጎሳ ነበር።ታዲያ  በቱትሲዎች ላይ የጅምላ ግድያ ዘመቻ ሲጀምር በ20ኛው ክፍለ ዘመን ከተከሰቱት የማካብሬ ክስተቶች አንዱ እንደነበር አልጀዚራ ተናግሯል። ከ800,000 በላይ ሰዎች - በአንዳንድ ግምቶች ደግሞ ከአንድ ሚሊዮን - በ 100 ቀናት ውስጥ በሜንጫ በሚይዙ ሁቱዎች አማካይነት በእጃቸው እየታረዱ ቱትሲዎች ሞተዋል ። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በወቅቱ  እንደገለፀው  ከ250,000 በላይ ሴቶች የወሲባዊ ጥቃት  ተፈፅሞባቸው  ነበር።

አሁን፣ ሎረንስና ታሲየን ከግድያ ቦታ ወደ ጽናትና አንድነት በተለወጠች መንደር ውስጥ ጎረቤት ሆነው  ይኖራሉ። እ.ኤ.አ. በ1994 በቱትሲዎች ላይ በተፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጻሚዎችና በህይወት የተረፉት በሩዋንዳ ካሉት ስድስት የእርቅ መንደሮች  ምቢዮ መንደር አንዱ ነው ። «መርሳት አንችልም በጭራሽ መርሳትም አይቻልም።»  አለች  ላውረንስ። «አሁን በሰላም እንኖራለን።ደግሞ ግን ድርጊቱን እናስታውሳለን።» ብላለች።

የእርቅ ታሪካቸው የተሳካ ቢመስልም፣ የተፈጠረው የዘር ማጥፋት ሰው ሰራሽ ነው ተብሎ ቢተችም። ሩዋንዳውያን የዘር ማጥፋት ትሩፋትን ይዘው ከህይወት ጋር እየታገሉ ይገኛሉ። በሕይወት የተረፉ ብዙ ሰዎች የሚወዷቸው ሰዎች እንዴት እንደተገደሉና ከገዳዮቻቸው ይቅርታ በመጠየቅ እውነትን በማወቃቸው ተጽናንተዋል። ሌሎች የጅምላ መቃብሮች መገኘታቸውንና የገዳዮች ማንነት ማጋለጣቸውን ስለሚቀጥሉ ሌሎች እንደዚህ ዓይነት የዘር ጭፍጭፋ ያካሄዱ ወገኖችን መደበቅ አልቻሉም ። በወቅቱ የዘር ጭፍጨፋው ከመካሄዱ 

ከኤፕሪል 6 ቀን 1994 በፊት በሩዋንዳ የጎሳ ግጭት ለአስርተ አመታት ሲካሄድ ነበር።ልክ አሁን ኢትዮጵያ ላይ እያየነው  እንዳለው  ነገር ።ነገር ግን በዚያን ቀን ነበር የወቅቱ ፕሬዝዳንት ጁቨናል ሀቢያሪማና የቡሩንዲው ፕሬዝዳንት ሳይፕሪያን ንታያሚራ አሳፍራ የነበረችው  ጀልባ(bot)  በተተኮሰ መሳሪያ ሁለቱም ፕሬዝዳንቶች በመሞታቸው ። ለዚህ ደግሞ ፕሬዝዳንቱ ሁቱ ስለነበሩ  የሁለቱ ፕሬዚዳንቶች ሞት የሁቱ ጽንፈኞች የሆነው  በቱትሲ  የሚመራውን የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር ( Rwandan Patriotic Front (RPF) ) ለድርጊቱ ተጠያቂና እንዲወቅስ አድርጎታል።ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ  የሚመሩትንና ስልጣን ከያዙ ጀምሮ ገዢውን ሁቱዎችን ሲዋጋ የነበረው  አማፂ ቡድን በ1979 ዓ.ም.  የሩዋንዳ  አርበኞች  ግንባር (Rwandan Patriotic Front (RPF))

አውሮፕላን መትተው  የጣሉ ሲሆን ይህ ደግሞ  ቱትሲዎችን መግደል ለመጀመር ሰበብ እንደሆነም  ይነገራል። ምክንያቱም  ድርጊቱ የተፈፀመው በሁቱስ  ተወላጆች አማካይነት ነበር። ሁቱዎች በረራውን የተጠቀሙበት ሁሉም ቱትሲዎች መጥፋት አለባቸው የሚል እምነት እንዲያንሰራራ በማድረግ በሩዋንዳ የሚኖሩ ሁቱዎች ወዲያውኑ የግድያ ዘመቻ እንዲጀምሩ  ማሳመን ጀመሩ ። ታሲን እንዳለው  አውሮፕላኑ ከተከሰከሰ በኋላ አዲስ በተፈጠረው የሬዲዮ ቴሌቭዥን ሊብሬ ዴስ ሚሌ ኮሊንስ (Radio Television Libre des Mille Collines station)ጣቢያ ሁቱስ ሁሉንም  ቱትሲዎች እንዲገድሉና የሚከላከልላቸው እንዳይኖር ወ ይም እራሳቸውን እንዲገድሉ ትእዛዝ መስጠቱን  ሰማሁ ብሏል። ጥላቻን የሚናገሩ የሬድዮ መልእክቶች ና ታዋቂ የሆኑ የቱትሲዎችን ሰዎች  ስም  የሚጠቁሙ  ሬዲዮ ጣቢያዎችም  ነበሩ። ከ45,000 በላይ ግድያዎችን በማነሳሳት ተጠያቂ  የነበረው  ይህ  ሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያ  ነበረ። ሁቱ የሚመራዉ  ጦርም  ብጥብጥ በማበረታታትና  የግድያ ዘመቻዎችን በማደራጀት  ከፍተኛውን ሚና ተጫውቷል።ታዲያ ታሲን በወቅቱ በግድያው  ከሁቱ ወገን  ጋር ተቀላቀለ። የመንግስት ሃይሎችና ሁቱ ሚሊሻ ቡድኖች ኢንተርሃምዌ( Interahamwe, a name that means “those who attack together” )

 በመባል የሚታወቁት ፣ ትርጉሙ  « በአንድ ላይ የሚያጠቁ» 

ማለት ነው - በኪጋሌ  ቱትሲዎችን መግደል ጀመሩ ፣ እንዲሁም  ለተራው የሁቱ  ሰዎች መሳሪያ እያከፋፈሉ ነበር።

ሁቱዎች  የቱትሲ  ህዝቦችን ለማጥፋት ለዓመታት ሲዘጋጁ  እንደነበሩ ከዓመታት በፊት በበርካታ  ሁቱ ስብሰባዎች  ላይ የተሳተፈው  ታሲን ገልጿል።ነገር ግን « የ1994  እ.ኤ.አ ይፋዊ  የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው።» ብሏል። ጭፍጨፋው  ሲጀመር 47 ዓመቱ ነበር። ቱትሲዎችን «በረሮ» እና «እባቦች» (“cockroaches” and “snakes” ) ናቸው  በማለትስለዚህ  መጥፋት ስላለባቸው  ሰብዓዊነት በማጉደል የመግደል ዘዴዎችንና የዘር ማጥፋት አስተሳሰቦችን ለማስፋፋት እንዴት እንደተነጋገሩ  ያስታውሳል።

ኤፕሪል 7፣ ታሲየን ቱትሲዎችን እንዲገደሉ ለማድረግ በወቅቱ የአንድ ዘርን ለማጽዳት በተዘጋጀው ቡድን ጋር  በመሆን  በዋና መንገድ መጋጠሚያዎች ላይ አብሮ ቆሞ ነበር።እነዚህን የቱትሲ ዜጎችን በመግደል በተሳተፈው  ቡድን  ላይም  አብሮ ተሳትፏል።ከዒላማዎቹ አንዱ የሎረንስ ባል ነበር። ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ሁቱዎች የቱትሲ ቡድን አባል ከሆኑ በፆታና በእድሜ ሳይለዩ ጎረቤቶቻቸውን ለመግደል ገጀራ፣ የእጅ ቦምቦች፣ ሽጉጦችና ሌሎችም ለጭካኔ የሚያገለግሉ መሳሪያዎች ተጠቅመዋል። ቱትሲዎችን ለመከላከል የሞከሩ  ሁቱዎችም የሞት ሰለባ   ሆነዋል።

ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ደኅንነት የሚያገኙባቸው የአምልኮ ቦታዎች ቢሆኑም  ይህ ግን የጅምላ ጭፍጨፋና  ማፈናቀል በአብዛኛው  አልሰራም ። በዘር ማጥፋት በሁለተኛው ሳምንት በሺዎች የሚቆጠሩ - በአብዛኛው  ሴቶችና ህጻናት - ከምቢዮ 30 ደቂቃ ርቀት ላይ በሚገኘው የኒያማታ ቤተክርስቲያን ከሞት ለመትረፍ ወደዛው  አመሩ ። የሁቱ ታጣቂዎች ቤተክርስቲያኑን የሚከላከሉትን ታጣቂዎች ገድለው ከውስጥም ከደጃፉም የእጅ ቦምቦችን ወረወሩ። ከዚያም ኢንተርሃምዌዎች ከውስጥ የተረፉትን በሙሉ  በሜንጫ  አረዷቸው።

ዛሬም  እልቂቱ በመላው ቤተ ክርስቲያን እየታየ ነው። በጣሪያው ና በግድግዳው ላይ በጥይት የተበሳሱ ቀዳዳዎች አሉ።አልባሳት፣ የሬሳ ሣጥኖችና የአፅም ቅሪቶች ወለሉን አበላሽቶታል። በደም የተበከለ ጨርቅ መድረኩን ይሸፍናል።በመሬት ውስጥ የተቀበሩ  አፅሞች ፤በጥይት የተመቱ ቀዳዳዎች ምልክት የተደረገባቸው በርካታ የራስ ቅሎችም  ይታያሉ።ከ10,000 በላይ የሚሆኑ በቤተክርስቲያኑ ውስጥ  የተሰባሰቡና ያለቁ የአካባቢው ተወላጆች በቤተክርስቲያኑ አጠገብ በጅምላ ተቀብረዋል። በመላ አገሪቱ ተመሳሳይ ክስተቶች ተከስተዋል። እልቂቱ ያበቃው በሐምሌ ወር የኡጋንዳው አርፒኤፍ የቱትሲ አማፂ ቡድን ኪጋሊን በመያዝ የሁቱ መንግስትን ገልብጦ  ነው። ከዛን ጊዜ ጀምሮ  መሪዋ ፖል ካጋሜ  በአሁኑ ወቅት ፕሬዝዳንት ሆነው በሩዋንዳ ሀገሪቱን መግዛታቸውን ቀጥለዋል።

አስደንጋጭ  ይቅርታ

ብዙዎች አሁንም የሚወዷቸውን ሰዎች ማን እንደገደሉባቸው አያውቁም. ።ላውረንስ በ2003 እ.ኤ.አ ታሲን ከእስር ቤት ጽፎላት ባሏን ስለገደለባት ይቅርታ ሲጠይቅ  ነው የአወቀችው። መንግስት ግድያውን በተመለከተ የእምነት ክህደት ቃላቶችን ለመስጠት ፍቃደኛ የሆነ ሰው  የእስር ቅጣትን የሚቀንስ ህግ በወቅቱ አውጥቶ ነበር። በዘር ማጥፋት ወንጀል ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተሳታፊዎች ላይ የቅጣት ውሳኔን ለማፋጠን በአካባቢው የሚገኙ «ጋካካ» ፍርድ ቤቶች (ጋካካ በአካባቢው  የኬንያ ሩዋንዳ  የሱዋሊ ቋንቋ «ሳር» ማለት ነው ) በማህበረሰብ የሚመራ የፍትህ ስርዓት ነው። « ይህን ባደርግም እንኳ በጣም አዝኜ ነበር፤ ግን እስር ቤት ሆኜ ድርጊቴን መጋፈጥ እንዳለብኝ አውቃለሁ። »  ስትል ታሲን ተናግራለች።

ሎረንስ ደብዳቤውን ተቀብላ ባሏን የገደለው ሰው ጓደኛዋና ጎረቤቷ መሆኑን ስታውቅ በጣም  ደነገጠች።

«ደብዳቤውን ማንበብ ለኔ በጣም ከባድ ነበር።»  ስትል ሎረንስ ለአልጀዚራ ተናግራለች።« ምን እንደተፈጠረና ለምን እንደተፈጠረ መገመትም ሆነ መረዳት አልቻልኩም።» ትላለች። እስረኞችን ወደ ማህበረሰቡ መመለስ እንደገና በሁቱ ሚሊሻዎች ጥቃት እንዳይደርስባቸው እሷም ሆነች ሌሎች የቱትሲ ዘሮች  አሁንም  ድረስ ፍራቻ አላቸው።

ገዳዮች ና የተረፉ  ጎን ለጎን

ታሲየን ከእስር ቤት ከተለቀቀ በኋላ አጥፊዎቹ በሕይወት የተረፉትን በአካል ይቅርታ እንዲጠይቁ  በአካባቢው አንድ ቄስ ስብሰባ አዘጋጁ። በመጀመሪያው ክስተት ሰዎች ዓይናፋር ሆነው ፈርተው ነበር ።አንዳቸው ለሌላው ምን እንደሚሉ አያውቁም ነበር።በሁለተኛው ስብሰባ ላይ ግን ታሲን ድፍረት አግኝቶ ወደ ሎሬንስ ቀርቦ ለራሱ እንዲህ በማለት ተናገረ፡«ይቅር ካላለችኝ ያን መቆጣጠር አልችልም፣ ነገር ግን ማድረግ የምችለው ባደረግኩት ነገር መፀፀቴን በመግለፅ ይቅርታ መጠየቅ ብቻ ነው። » በማለት ተናግሯል።

ሦስት ዓመታት ፈጅቷል፣ ግን ላውረንስ ታሲን ይቅር አለችው።

እ.ኤ.አ. በ 2005 ሁለቱም በሀገሪቱ ዙሪያ ካሉት ስድስት የእርቅ መንደሮች አንዱ በሆነው  ምቢዮ መንደር በመንግስትና በእስር ቤት ሩዋንዳ መካከል በተቋቋመው ሽርክና ከተገነቡት ፣ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈፃሚዎች ወደ ህብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ለመርዳት በተቋቋመ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ተዛውረዋል።

የመንደሮቹ አላማ ነፍሰ ገዳዮችና የተረፉ ሰዎች እርስ በእርሳቸው እንዲኖሩ, ህይወታቸውን እንደገና እንዲገነቡ ፤ያለፈውን በማስታረቅ. በ1994ቱ የዘር ማጥፋት ወንጀል በመርሳት  በሁለቱ ብሄረሰቦች መካከል እኩልነት እንዲፈጠርና ዜጎች እርስ በእርስ እንዳይበቃቀሉ ለማድረግም አስበው  ነበር።

በኔዘርላንድ በሚገኘው የቲልበርግ የህግ ትምህርት ቤት የሽግግር ፍትህ ረዳት ፕሮፌሰርና የሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ወንጀል ኤክስፐርት ፌሊክስ ሙክዊዛ ንዳሂንዳ የመንግስት ፖሊሲዎች እርቅን ለማበረታታት እገዛ አድርገዋል በማለት ይገልጻሉ።

ከእነዚህ ፖሊሲዎች መካከል አንድነትና ዕርቅ ላይ ያተኮሩ ተቋማትን መፍጠርና ብሔርን ከግል መለያነት  ማስወገ ድ ይገኙበታል።

የዘር ማጥፋት ወንጀል የመንግስትን ትረካ ለመቃወም በመሠረቱ ሕገ-ወጥ ተደርጎ ነበር። የሩዋንዳ መንግስት ታሪክን ለፖለቲካዊ ጥቅም መጠቀሚያ በማድረጉ  ትችት ገጥሞታል። የመንግስት ተቃዋሚ መሪዎች ወይም ተቺዎች በዘር ማጥፋት ርዕዮተ ዓለም ሕጎች ታስረዋል። ግልጽ ያልሆነ ተቺዎች እንደ ፖለቲካ መሳሪያ ተቆጥረዋል።

ንዳሂንዳ በሩዋንዳ ያለው የፖለቲካ ነፃነት ከአገሪቱ አስቸጋሪ ታሪክ፣ የዘር ማጥፋት ውርስ እና ያስከተለው ስብራት ሩዋንዳ እንዴት ከውስጧ እንደምትወጣ መገመት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል። የማስታረቅ ሂደቶች ከዚህ ጠባብ መንገድ ለመውጣት  የበለጠ ውስብስብ  ናቸው  ብለዋል ።

ንዳሂንዳ « ግለሰቦች በተራራ ላይ እንዴት እርስበርስ እንደሚግባቡ፣ በመንደሮች ውስጥ አብረው እንደሚኖሩ፣ የዕለት ተዕለት ግንኙነታቸውን እንደሚያዳብሩና አንዳንዴም በአደጋው ​​የተረፉትን ወንጀለኞችን በመከፋፈል በቤተሰብ መካከል ጋብቻን እንደሚመርጡ ከመንግስት ስራ በላይ ነው። » ብለዋል ።

ሁሉም ሰው ሰላም አላገኘም። ይቅርታ ማግኘት !

ታሲየን እና ላውረንስ በዕርቅ መንደር ውስጥ ለ19 ዓመታት ኖረዋል እና ተቀራራቢ ናቸው። የታሲን ልጅ በቅርቡ ሲያገባ ሎረንስ በሠርጉ ላይ ተገኝታለች።ከዘር ማጥፋት የተረፉ ቡድን የኢቡካ ዋና ፀሃፊ ናፍታታል አሂሻኪዬ በኪጋሊ ኪኩኪሮ አካባቢ ከሚገኘው የኒያንዛ የዘር ማጥፋት መታሰቢያ ጣቢያ ሰራተኞቹ ሰሞኑን በተከበረው  የመታሰቢያ ዝግጅቶችን በመዘጋጀት ላይ እያሉ ሳር ሲቆርጥና ቀለም  ሲቀቡ ከአልጀዚራ ዘጋቢ ጋር ተነጋግረው ነበር።ናፍታታል  ለአልጀዚራ እንደተናገረው «ሰዎች አሁንም እየተሰቃዩ ነው ብዙዎች ይህንን መርሳት የለባቸውም» «ምክንያቱም ብዙ ቅሪቶች ስላልተገኙ እንዲሁም ሁሉም አጥፊዎች አልተፈረደባቸውም። የጅምላ መቃብሮች እየተገኙ ነው። ባለፈው ጥቅምት ወር በሁዬ ክልል ውስጥ በቤት እድሳት ወቅት አጥንቶች ተገኝተዋል። ይህም በአካባቢው የፍለጋና የቁፋሮ ጥረቶችን ያነሳሳ ሲሆን ይህም ከ 1,000 በላይ ሰዎች ቅሪት እንዲገኝ አድርጓል።» በማለት ገልጿል።

«ለ30 ዓመታት  ያህል የመንደሩ ነዋሪዎች ጎረቤቶቻቸው ከዚህ ቀደም ስለተከሰተው ነገር እውነቱን እንዲነግሯቸው  ጠይቀው  ነበር፤ ማንም  ምንም ነገር አላመነም። ከዚያም አስከሬኑን አገኙ።» አለ አሂሻኪዬ። «ይህ ደግሞ  መተማመንንና የእርቅ ሂደቱን  ያዳክመዋል።» ብሏል።

« ከዘር ማጥፋት የተረፉ ሰዎች ሩብ ያህሉ አሁንም ከአእምሮ የጤና ችግር  ጋር እየታገሉ ነው ያሉት »አሂሻኪዬ  እንደሚለው። የዘር ማጥፋት ከተፈጸመ በኋላ የተወለዱ አዳዲስ ትውልዶች ለአቅመ አዳም ሲደርሱ ቀጣይነት ያለው  ድጋፍ እንደሚያስፈልግ»  ገልጿል።

የሁለቱም ወንጀለኞችና የተረፉ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ስለ ያለፈው ጊዜ በግል እንዴት እንደሚነጋገሩ መቆጣጠር እንደማይችል ንዳሂንዳ ጠቁመዋል። የሩዋንዳ ዲያስፖራ፣ በአብዛኛው የፕሬዚዳንት ካጋሜን የአስተዳደር አካሄድ ከሚተቹ ሰዎች ጋር፣ በአገር ውስጥ ካሉ ሩዋንዳውያን ጋር በጣም ተቃራኒ አመለካከቶች አሏቸው - እንደዚህ  አይነቱ ልዩነት ያላቸውን ለማስተናገድ ቀላል ሊሆኑ  የማይችሉ ልዩነቶችን ለማስተናገድ  እንደተቸገሩ  አክሎ  ተናግሯል።

ንዳሂንዳ « የመረጋጋት ሁኔታ  ባለበት አካባቢ ስለወደፊቱ ጊዜ እርግጠኛ ሆኖ አብሮ መኖር ይቻላል ወይ ? ዳግመኛስ ይህ አይነቱ የዘር ጭፍጨፋ  እንደማይከሰት  ምን ማስተማመኛ  አለ? የሚለው  ሁኔታ በብዙ ሰዎች አእምሮ ውስጥ ይኖራል።» ብለዋል።

ነገር ግን ጉዳዮች አሁንም ለብዙዎች ቢቀጥሉም፣ ብዙ ጊዜ በዝግ በሮች ተደብቀዋል፣ እንደ ላውረንስና ታሲየን ያሉ ሰዎች ያለፈውን ለመቀበልና አብረው ለመቀጠል መንገድ አግኝተዋል። በ ምብዮ Mbyo መንደር ውስጥ, ሁለቱ ጎረቤቶች አብረው ወደ ቤተ ክርስቲያን ይሄዳሉ።ምግብ ይጋራሉ ፤አንዳቸው የሌላውን ልጆች ይንከባከባሉ።በዓይኖቹ እንባ እያነባ የሎረንስን እጅ ሲይዝ ታሲን ለሎረንስ ይቅርታ ምን ያህል አመስጋኝ እንደሆነ ተናግሯል።

«በጣም መጥፎ ነገር አድርጌ እሷንና ቤተሰቧን ጎዳሁ።» ሲል ተናግሯል፣ «አሁን፣ በሳምንቱ የመታሰቢያ ዝግጅቶች ወቅት ምኞቴ ከእሷ ጎን መሆን ብቻ ነው። እንደምወዳትና እንደምጠብቃት ማሳየት እፈልጋለሁ። ከእኔ ጋር ደህንነት እንዲሰማት እፈልጋለሁ።» ብሏል።ይህን የሩዋንዳን የዘር ጭፍጨፋ ስናስብ  በሀገራችን ውስጥ ብሄርን ተኮር ያደረገው የዘር ጭፍጨፋዎች ትዝ ማለቱ  አይቀርም።

በኢትዮጵያ ላለፉት 3 እና 4  ዓመታት እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች ና እየተስፋፉ ያሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ከግምት ውስጥ በማስገባት የጅምላ ግድያና የዘር ማጥፋት ዘመቻ በተለይም  ምሑራኑ ክፍል  ብዙም ትኩረት የሰጡትም  አይመስልም።ይሁንና በአንዳንድ አካባቢዎች የተካሄዱ የዘር ጭፍጨፋን የሚያወሱ ጥናቶች መኖራቸውም አልቀረም ለምሳሌ  ከህዳር 9-10 ቀን 2020 በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ በደረሰው በማይካድራ እልቂት የተረፉትን የአማራን ህያው ተሞክሮዎች መርምራ ተደርጎባቸው  ይፋ የተደረጉ ይኖራል። በዚህ ምርምር ጥልቅ ቃለ-መጠይቆች በወቅቱ ከዘር ጭፍጨፋው  የተረፉ ከ15  ሰዎች ጋር በተደረገው ቃለ ምልልስ ሆን ተብሎ በተመረጡት አካባቢዎች የሕይወት ልምዳቸውን ትርጉም ና ይዘት ምን  እንደሚመስል  ለመረዳት  ጥረት ተደርጓል። መረጃው በጥራት የተገለበጠ፣ የተተረጎመና ጭብጥ በሆነ መልኩ ተተንትኗል። ጭብጡ ትንተና በቅድመ-እልቂት  የደረሱ ጭቆናዎችና መድልዎ ላይ ያተኮሩ ሰባት ጭብጦችን አካቷል።አሰቃቂ ገጠመኞች፣ ነፃ ማውጣት፣ ጭንቀቶችን የሚያባብሱ፣ ከጭፍጨፋ በኋላ የተፈጸመ ኢፍትሃዊነት፣ የተረጂዎች የመጀመሪያ ፍላጎቶችና ከእልቂት የተረፉ ሰዎችን የማቋቋም ዘዴዎች እንዴት እንደነበሩ ለማየት ተችሏል። ጽሑፉ  የማህበረሰብ ሰራተኞች እንደ ግለሰብ፣ቤተሰብና ማህበረሰቦች ከጅምላ የተረፉ ልዩ ልዩ ፍላጎቶችን ለማሟላት የተደረጉ  ሙያዊ የስነ-ልቦና ፕሮግራሞችን እንዲሁም ጣልቃ ገብነቶችን ለማቅረብ ያለውን ሚና ያጎላል ተብሏል።እንደዚህ አይነት ጥናቶች  በሀገራችን ውስጥ መደረጋቸው የችግሩን ሰር በማግኘት በሀገራችን ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ  የመጣውን የዘር ጭፍጨፋ ከስሩ መንቅሎ ለመጣል ከፍተኛ አስተዋጾ ይኖረዋል ተብሎ  ይጠበቃል።አሊያዚያ ግን በየጊዜውና በየቦታው  ሰው  እንደ ውሻ ሞቶ የሚገኝ ከሆነ የሁቱና የቱትሲ አይነት የዘር ጭፍጨፋ መነሳቱ አይቀሬ ነው።በሩዋንዳ እ.ኤ.አ ከ1994 ድርጊቱ

ከመፈፀሙ  ከ10 አመታት በፊት ይህ የዘር ማጥፋት ዘመቻ እያቆጠቆጠ ነበር።በወቅቱ ማቆም ቢቻል ኖሮ በሩዋናዳ የተከሰተው  የዘር ተኮር  ጭፍጨፋው ባልተከናወነ ነበር።ኢትዮጵያ ውስጥም እየታየ ያለው ነገር ይሄው ነው።

 

የዓለም አቀፉ የሰበአዊ መብት ተከራካሪ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባለፈው የካቲት ወር ኢትዮጵያን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ  በአማራ ክልል ከህግ አግባብ ውጭ የሚፈጸሙ ግድያዎች ይቁም፣ ወንጀለኞች ለፍርድ ይቅረቡ ሲል መግለጫ አውጥቶ ነበር።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ሰራዊት በአማራ ክልል ርዕሰ መዲና ባህር ዳር በሰላማዊ ሰዎች ላይ ያለፍርድ የሞት ቅጣት የፈፀመ ሲሆን በአንዳንድ አጋጣሚዎች የቤተሰብ አባላት ወዳጅ ዘመዶቻቸውን የመቅበር መብት ተነፍገዋል ሲል  አስታውቋል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው በዚሁ መግለጫው 

«በባህር ዳር ከተማ ከህግ አግባብ ውጪ በህገወጥ ወታደሮች የተፈፀመ ቅጣት» በሚል ርዕስ ፣ በቀበሌ 14 አካባቢ በአቡነ ሀራ እና ልደታ ሰፈሮች 8 ንፁሀን ዜጎች ላይ የመከላከያ ሰራዊት አባላት 6 ሰላማዊ ሰዎችን ከህግ አግባብ ውጪ የሞት ቅጣት እንደፈፀሙባቸው የሚያሳይ ነው። ኦገስት 2023

ከሁለት ወራት በኋላ፣ በጥቅምት 10 እና 11፣ የመከላከያ ሰራዊት (ENDF) አባላት በከተማዋ ሴባ ታሚት ሰፈር ውስጥ ቢያንስ አምስት ሲቪሎችን ጨምሮ ሌሎች ስድስት ሰዎችን ከህግ አግባብ ውጪ ገደለዋል ብሏል። የኢትዮጵያ መንግስት በባህር ዳርና በመላው አማራ ክልል እየተካሄደ ካለው የትጥቅ ግጭት ጋር ተያይዞ የሚፈጸሙ  የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ላይ ውጤታማ የሆነ ገለልተኛ ምርመራ በአስቸኳይ ሊከፍት ይገበዋልም  ሲል ገልጾ ነበር።

የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ቀጣናዊ ዳይሬክተር

ቲጌሬ ቻጉታህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭት የኢንተርኔት አገልግሎትን በመዝጋት፣ ከፊል የመገናኛ ብዙሃን በመቋረጡና በመካሄድ ላይ ባለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመናገርና የመገናኛ ብዙሃን ነፃነትን እንዲሁም የአጸፋዊ እርምጃ ፍርሀትን በመፍራት እያስከተለ ያለው የሰብአዊ መብት ተጽኖ ከፍ  እያለ  መጥቷልም ብሏል።

«የኢትዮጵያ መንግስት በባህር ዳርና በመላው የአማራ ክልል እየተካሄደ ካለው የትጥቅ ግጭት ጋር ተያይዞ የሚፈጸሙ  የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ላይ ውጤታማ የሆነ ገለልተኛ ምርመራ በአስቸኳይ ሊከፍት ይገባልም» ሲል አምስቲ ገልጿል። በቂ ማስረጃ ሲገኝ ጥሰቱን ፈጽመዋል የተባሉት ሰዎች የሞት ፍርድ ሳይቀጡ ዓለም አቀፍ የፍትሃዊ የፍርድ ሂደት መስፈርቶችን ባሟሉ ችሎቶች መከሰስ አለባቸው በማለት የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ክልላዊ ዳይሬክተር ቲጌሬ ቻጉታህ ተናግረዋል።  

በዚህ አጭር መግለጫ ላይ እንደተገለጸው የአለም አቀፍ የሰብአዊ ህግ (IHL) ከባድ ጥሰቶች በአለም አቀፍ ህግ መሰረት ወንጀል የሆኑ የጦር ወንጀሎች ሊሆኑ ይችላሉ ብሎ። ያለፍርድ ቤት ትህዛዝ መግደል በአለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ህግ መሰረት በህይወት የመኖር መብት መጣስ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ፣ በዓለም አቀፍ ህግ መሰረት ወንጀሎችን ለሚፈፅሙ ከባድ በደሎች ታማኝ ፍትህና ተጠያቂነት በሌለበት ሁኔታ የስርአት ቅጣት ወንጀለኞችን ማበረታታቱን ቀጥሏል።ብሏል። በአገር አቀፍ ደረጃ እየተንሰራፋ ያለውን የፍትህ ተጠያቂነት እጦት ማቆም ጊዜው አሁን ነው  ሲልም  ገልጿል ።

«በኢትዮጵያ ውስጥ፣ በአለም አቀፍ ህግ መሰረት ወንጀሎችን ለሚፈፅሙ ከባድ በደሎች ታማኝ ፍትህና ተጠያቂነት በሌለበት ሁኔታ የስርአቱ የወንጀል ፈጻሚዎችን ማበረታታቱን መንግሥት ቀጥሏል የሚለው አምንስቲ በአገር አቀፍ ደረጃ እየተንሰራፋ ያለውን የፍትህ ተጠያቂነት እጦት ማቆም ጊዜው አሁን ነው ብሏል። በአቡነ ሀራ ና ልደታ የነሀሴ ወር የፍትሃዊ ጥፋቶች

የአይን እማኞች እና የቤተሰብ አባላት እንዳሉት ተጎጂዎቹ የተገደሉት በቅርብ ርቀት ላይ በተተኮሰ ጥይት ነው የሚለው  አምንስቲ።

ከህግ አግባብ ውጭ  ከተገደሉት ሰዎች መካከል አንዱ አቶ ይታገሱ አያሌው ሲሆኑ፣ ልደታ አካባቢ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በመከላከያ(ENDF) ወታደር በጥይት ተመትተው መሞታቸውን የ17 አመት ዘመድ ቢኒያምን ጨምሮ በርካታ ምስክሮች ተናግረዋል። አንዲት ሴት  የተተኮሰው ነሀሴ 8 ቀን ጧት ላይ ኢንጀራ እየጋገሩ ነበር የተኩስ ድምጽ መስማት እንደተጀመረ  ተናግረዋል።

«ከቀኑ 8 ሰዓት አካባቢ ከሙሉጌታ ሪል ስቴት በኩል የተኩስ ድምጽ መስማት ጀመርን። በግቢው ውስጥ የነበሩ ሰዎች አቶ ይታኩ እንደሚሉት በግቢው ውስጥ እንጀራ መጋገር ሴትየዋ  አቁመው ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ጠይቀዋል። እሷም፣ «ልጄ ቁርስ የለውም፣ እና ልጨርስ ትንሽ አለችኝ» አለችው። ለመስማት ፈቃደኛ አልሆነችም። ከቀኑ 9፡15 አካባቢ የተወሰኑ ወታደሮች እየሮጡ መጡ። አንድ ሰው በመንገድ ላይ እያሳደዱ ነበር ብዬ አስባለሁ። ከዚያም ወደ ግቢው መተኮስ ጀመሩ ።በተተኮሰው ጥይት አንድ ሰው ሞተ። በአጥሩ ላይ ያለውን ቀዳዳ ተኩሰው  ወጡ።» ብለዋል።

ሌሎች ተጎጂዎች የ55 ዓመቱ ነጋዴ አቶ አይነው ደፍርሽ እና ሁለቱ ልጆቻቸው ካሳሁን እና አብርሃም ናቸው። ሦስቱ ሰዎች ከቤተክርስቲያን ወደ ቤታቸው ሲሄዱ በመንገድ ላይ በጥይት ተመተው ተገድለዋል። አንድ የቤተሰብ አባል ለአየነው ስልክ ሲደውሉ የመከላከያ ENDF ነው ብለው የሚያምኑት ግለሰብ ስልኩን አንስተው «ትንሽ አደጋ ነው » ብሎ ተናግሯል። በመጨረሻ የቤተሰብ አባላት ሶስቱን አስከሬኖች ወደ ቤት ወሰዱ። 

በባህር ዳር ከተማ የመጀመሪያው ጦርነት ከሁለት ወራት በኋላ ጥቅምት 10 ቀን በሌሎች የከተማው ክፍሎች በተለይም በሰባ ታሚት አካባቢ ጦርነት እንደገና ተቀሰቅሷል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል በጥቅምት 10 እና 11 በመከለከያ ENDF ወታደሮች በስድስት ሰዎች ላይ ያለፍርድ መገደላቸውን አረጋግጧል። ከነሱ መካከል በመከላከያ ENDF ወታደሮች በጤና ጣቢያ ውስጥ ያለፍርድ የተገደሉ ታካሚ  ይገኝበታል። የመከላከያ ENDF ወታደሮች በተመሳሳይ ጤና ጣቢያ ውስጥ የጤና ሰራተኞችን በጥይት ደብድበዋል እንዲሁም  አስፈራርተዋል።

በዚሁ አካባቢ መከላከያ ENDF ወታደሮች የ69 አመቱ አዛውንት ታደሰ መኮንን ቤት ከገቡ በኋላ ጥቅምት 11 ቀን 2009 ዓ.ም ጧት ላይ ሶስት ወንድማማቾችንና አንድ ጎረቤቶቻቸውን ያለፍርድ ገድለዋል። አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያነጋገራቸው ሶስት የተለያዩ ሰዎች የመከላከያ ENDF ወታደሮች የአቶ ታደሰ ሶስት ልጆችንና አንድ ክፍላቸውን የተከራየውን አንድ ሰው  ገድለዋል ብለዋል።

ጥቃቱ በተፈፀመበት ወቅት ከቤተሰቡ ጋር የነበረው  የአቶ ታደሰ ዘመድ ካሳ ለወታደሮቹ በር እንደከፈተላቸው ተናግሯል፣ እናም [የመጨረሻ ወታደሮች] ወንድ ቤተሰብ አባላትን በሙሉ ከግቢያቸው  አስውጡ። ከመከላከያ ENDF ወታደሮች አንዱ  ከሰዎቹ መካከል  «ማንንም  አትተዉ; ሁሉንም ላይ  ተኩሱ» ብሎ ትህዛዝ መስጠቱንና መገደላቸውን ገልጿል።

እንደ አቶ ካሳ ገለጻ፣ የመከላከያ ሰራዊት ( ENDF )  ወታደሮች መጀመሪያ ቤተሰቡ አስከሬኑን እንዳያገኝ ስለከለከሉ ወታደሮቹ እስኪወጡ  መጠበቅ ነበረባቸው። የሟቾቹ አስከሬኖች ከጠዋቱ 9 ሰአት እስከ ምሽቱ 4 ሰአት ላይ በመንገድ ላይ እንዳሉ ሶስት እማኞች ተናግረዋል። ቤተሰቡ የሰበካ  ጉባሄ አባላት የሆኑበት ቅርብ ቤተ ክርስቲያን ሳይሆን የተቀበሩት አንድ ቦታ ነው።አስከሬናቸው የሰበካ ጉባሄ በሆኑበት አካባቢ በተለያየ ቤተ ክርስቲያን መቅበር ነበረባቸው  ብለዋል  አቶ ካሳ።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል እያንዳንዱን ቃለ መጠይቅ ጠይቋል ወንጀለኞችን እንዴት የመከላከያ ENDF ወታደሮች መሆናቸውን እንደለዩዋቸው። አብዛኞቹ መከላከያ ሰራዊት በባህር ዳር ከተማ ውጊያው ከመጀመሩ በፊት ለሶስት ወራት ያህል ሲንቀሳቀስ እንደነበርና ዩኒፎርማቸውን እንደሚያውቁ ተናግረዋል። አንዳንዶች እንደሚሉት የመከላከያ ENDF ወታደሮች «መሳሪያውን አምጡ  ፤ ፋኖን ትደግፋለህ? ለተጎጂዎች ወይም ለቤተሰቦቻቸው መረጃ ትሰጣለክ  እየተባሉ እርምጃ እንደተወሰደባቸው  ተናግረዋል።»  ብሏል።

አምንስቲ በትግራይ ክልል የተፈፀሙ ጥሰቶች በተመለከተም በትግራይ ያለው ጦርነት ከቆመ ከአንድ አመት በላይ የ መከላከያ ENDF ወታደሮች በሌላ የትጥቅ ግጭት ውስጥ የሰብአዊ መብቶችንና የአለም አቀፍ የሰብአዊ ህጎችን መጣስ ቀጥለዋል ይላል አምንስቲ።

«ከ2020 መገባደጃ ጀምሮ በመከላከያ ENDF እና በተባባሪ ሃይሎች የተፈጸሙ የወንጀል ጥሰቶች በአለም አቀፍ ህግ መሰረት የተፈጸሙ  ወንጀሎች ተጠርጥረው ፍርድ ቤት መቅረብ እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ማረጋገጥ አለባቸው  ብሏል።

«ኢትዮጵያን በተመለከተ ወደ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ምርመራ የምንመለስበት ጊዜ ነው። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት አባላትን ጨምሮ የሀገሪቱ አጋሮች በኢትዮጵያ ያለውን የሰብአዊ መብት ሁኔታ እንደገና ለመመርመርና የአለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ኤክስፐርቶች ኮሚሽን ICHREE ግኝቶችን ለመከታተል አፋጣኝ እርምጃዎችን መውሰድ አለባቸው።ብሏል። ይህ ጊዜ ኢትዮጵያን ወደ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ትዝብት የምንመልስበት ጊዜ ነው  በማለት አምንስቲ  ገልጾ ነበር ።

ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ድርጅቱ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል  ምላሽ አላማግኘቱን ገልጿል።

እ.ኤ.አ. ነሐሴ 2023 በአማራ ክልል በኢህአዲግ (የአሁኑ ብልፅግና) እና በፋኖ ሚሊሻዎች መካከል አለም አቀፍ ያልሆነ የትጥቅ ግጭት

ተቀሰቀሰ። ከዚህ በፊት አጋሮች የነበሩት  ሁለቱ ወገኖች ፣ ወደ ጠላትነት ተቀይረው፣ ቀደም ሲል በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል አብረው ተዋግተዋል። ውጊያው በህዳር 2022 በፌዴራል መንግስትና በህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሀት) መካከል የተደረገውን የእርስ በርስ ጦርነት ስምምነት እንዲቆም ተደረገ።በሚያዝያ ወር 2023 የፌደራል መንግስት የክልል ልዩ ሃይሎችን ወደ ፌደራል ሃይሎች ለማዋሃድ የተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ነው ወደ  ግጭት ለመግባት የቻሉት። በዚህ ውሳኔ ቅር የተሰኘው የአማራ ልዩ ፖሊስ ሰራዊት አባላት ፋኖ ሚሊሻዎችን ተቀላቅለዋል። እ.ኤ.አ. ኦገስት 1 2023 የኢትዮጵያ መከላከያ ENDF «በፋኖ ስም የሀገሪቱን ሰላም እያናጋ ነው።»ሲል ከሰሰ። እ.ኤ.አ. ነሐሴ 2 ቀን 2023 በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ነዋሪዎች በኢህአዲግ እና በፋኖ ሚሊሻ መካከል ግጭት መፈጠሩን ለመገናኛ ብዙሃን ተገለጸ።

 

እ.ኤ.አ. ነሐሴ 4 ቀን 2023 የኢትዮጵያ መንግስት በአማራ ክልል ተባብሶ የነበረውን ሁከት ተከትሎ ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሀገር አቀፍ ደረጃ አወጀ።

አዋጁ ከታወጀ በኋላ የእርስ በእርስ ግጭቱ በአማራ ክልል አሁንም እንደቀጠለ ነው።በኦሮሚያና በአንዳንድ ክልሎችም ግጭቶችና ዘርን ተኮር ያደረገ  እርምጃዎች እየተወሰደ ነው ።የመንግሥት ወታደሮች ብቻ ሳይሆን  የመንግሥት ተቃዋሚ ኃይሎችም የመንግሥት ደጋፊ የሆኑ ወገኖችንና ቤተሰቦቻቸውን  በመግደል ላይ ይገኛሉ።በመንግሥትና በተቃዋሚ ኃይሎች መካከል እኔ አይደለሁም እከሌ ነው እየተባባሉ ድርጊቱን እየፈፀሙ የመሸዋወዱ  ሁኔታ ለማንም አይጠቅምም።እናቱና አባቱ  ፊትለፊቱ የሞተበት ልጅ ነገ ሲያደግ ምን አይነት ስሜት ይዞ ነው  የሚነሳው።ሀገር ልታድግ የምትችለው።ሰላም ሲኖር ነው።ሰላም ከሌለ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ እየተንቀሳቀሱ ሰርቶ መብላት የሚቻለው ሀገር ሰላም ሲሆን ብቻ ነው።ዛሬ ህዝባችን በሰላም ከቤቱ ወጥቶ በሰላም ወደ ቤቱ የማይገባበት የሰቀቀን ጊዜ ላይ ደርሰናል።ለስልጣን የሚፋተጉ ወገኖች መጀመሪያ ህዝብን ማዳመጥ ያስፈልጋል።የህዝብን ችግር ማወቅና መፍትሄ መስጠትም አንድ ሊባል የሚገባ ጉዳይ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር  ዐብይ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው «ሩዋንዳውያን የ’ኪዊቡካ 30’ አመት በምታስብቡት ወቅት ኢትዮጵያ አብራችሁ ቆማለች።» 

 

“Ethiopia stands with the people of Rwanda as you commemorate ‘Kwibuka30’.” ብለዋል።ይህን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ብሄርን ተኮር ያደረገውን በተለያዩ ክልሎች የሚታየውን  የዘር ጭፍጨፋ ለማስቆም ምን ያደረጉት ጥረት አለ? የራስዋ እያረረባት የስው ታማስላለች ወይም ከናትዋ ልጅዋ ትብስ ባቄላ አሮባት እጅዋን ትልስ

 እንደሚባለው ካልሆነ በስተቀር ለማለት የፈለኩት ዶክተር ዐብይያለአቅም እና ያለቦታቸው  ነው በሩዋንዳ የተገኙት ለማለት ነው።ምክንያቱም  እውነት እንነጋገር ከተባለ ኢትዮጵያ ውስጥም አሁንም ይህ አይነቱ  ዘርን ያማከለ ጭፍጨፋ  በየቦታው  አለ።

 ።  ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዛሬ ኪውቡክ ላይ ሆነው  የሩዋንዳን የዘር ጭፍጨፋ ሲያከብሩ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደዚህ አይነቱ የዘር ጭፍጨፋ እንዳይከሰት ለራሳ

ለራሳቸውም  ሆነ ለህዝባቸውም ቃል መግባት ይኖርባቸዋል እላለው።  አበቃው  ክብረት  ይስጥልኝ።