ለኢትዮጵያችን ሰላም ስንል ብንዋሽስ ?


 

 ከወሰንሰገድ መርሻ ደምሴ (ጮራ ዘ አራዳ) 

(ደራሲ፣ጋዜጠኛና ማህበራዊ ሀያሲ)

 

«የፖሊሲ ወይም የመመሪያ ጥበቡ የተቃዋሚውን ወገን የፖለቲካ ስሌት ውድቅ የሚያደርግ የሃገርን ጥቅምና ጉዳት የሚዳስስ የፖለቲካ ቀመር  መዘርጋት አስፈላጊ ነው።»ዶክተር ኽንሪ ኪስንጀር 

  ከላይ ያለውን አባባል የተናገሩት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር የነበሩት ዕውቁ ዲፕሎማት ዶክተር ኽንሪ ኪስንጀር  «ዲፕሎማሲ »በሚለው መጽሐፋቸው ላይ ነበር ይህን ሀሳብ የጠቆሙት።

 የአንድ አገር መንግሥት አገሩን በተመለከተ በሚደረጉ ማንኛውም የውጭም ሆነ የውስጥ የፖለቲካ ሂደቶች ውስጥ እንዲህ አይነቱ ሁኔታ በብዛት ተግባራዊ ሲያደርጉ ይስተወላሉ።

 አሁንም ሆነ ወደፊት በአገራችን ውስጥ ከውስጥም ሆነ ከውጭ የሚከሰተውንና የተከሰተውን  የፖለቲካ ሱናሚ  ማብረድ የተቻለውና የሚቻለው ለአገራቸውና ለወገናቸው የሚያስቡ ምሁራኖች ባዘጋጁት የፖለቲካ ቀመር መሰረት የተጠነሰሱት አሳቦች እየዳበሩና እየተሻሻለ ተግባራዊ እንዲሆን በማድረጋቸው እንደሆነ ለማንኛችንም ግልፅ ነው።

 በእርግጥ በአብዛኛው የአገራችን ምሁራኖች በተለይም በፖለቲካ ሳይንስ ላይ በቂ ዕውቀት አለን የሚሉ ወገኖች ከደርግ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚጠቅመውንና የሚሆነውን የፖለቲካ ርዕዮት ዓለም ተግባራዊ ከማድረግ ይልቅ ከአድርባይነት ባልዘለለ መልኩ አገሪቱን በመምራት ላይ ለሚገኙ ወገኖች የሚጠቅም ሕግና ድንብ በማርቀቅ የአድርባይነት ሥራ ሲሰሩ ነው የቆዩት።

 የእኛ አገር ሙሁራኖችና ፖለቲከኞች እንጨት ሸጦ ያስተማረውን ሕዝብ ከመካስና ወደ ተሻለ የኑሮ ደረጃ ከፍ እንዲል ከማድረግ ይልቅ የባሰ ወደ ድህነት የሚከተውን ፖሊሲ አርቅቀው  ሲተገብሩ ነው  ያስተዋልነው።

ይህ ብቻ አይደለም በተማሩበት የሙያ ዘርፍ ያላቸው ብቃትና ሕዝብን የመምራት አቅማቸው ውስን መሆን ከዚህ ሌላ  ምን ያህል ደካማ  እንደነበረም ባለፉት ጊዜያት በአገራችን ውስጥ በተካሰተው ችግሮች ሳቢያ በግምገማና በተለያዩ ብቃት ማነስ ከአላፊነታቸው እንዲነሱ ከተደረጉ ባለስልጣኖቻችን ሁኔታ መረዳት ይቻላል።

  በአንድ አገር ውስጥ የሚከሰቱ ግጭቶችና አለማግባባቶችን ለመፍታት በፖለቲካ ውስጥ አስተማማኝ የቁማር ጨዋታወይንም የፖለቲካ ቀመር መኖር ወሳኝነት አለው። 

 ክላውስዊትዝ የተባለ ፖለቲከኛ ስለ ፖለቲካ ዘመቻ እንዲህ በማለት ይገልጸዋል።

«ዲሞክራሲ መስጠትና መቀበል ግድ ነው።ለሰዎች በመርህ ደረጃ ከተቀመጠው መሆን ወደ ሚችለው አሊያም ወደ አልታሰበው ሁኔታ ሊጓዝ ይችላል።ይህ ደግሞ ሐሳብን ሊለውጥ ወይንም ሊያስለውጠን ያስችላል።በዚህም የተነሳ ሐሳብን በማስለወጥ፣በሚደረጉ ድርድሮች፣በሚነሱ ነጥቦች ዙሪያ እንዲሻሻሉና እንዲቀየሩ በማድረጉ በኩል ጉሉ ሚና አላቸው።አንዳንዴ ሁኔታዎች ምስቅልቅልና ተስፋ አስቆራጭ አሊያም  አስደንጋጭ  ሊሆኑ ይችላሉ።

 ድርድሩ ተሳታፊዎችን መሪ የሌላቸው ተቀያያሪ ባሕሪ የተላበሱ አጭበርባሪዎች እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል» በማለት ይገልጻሉ።

 አባባሉ የፖለቲካውን ቁማር ጨዋታ ወይንም  ቀመር አስቸጋሪነት የሚያሳይ ነው።

እንደተባለው ይህ አይነቱ ሁኔታ በአገር ውስጥ ጉዳይ ላይ አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር ተግባራዊ የማድረጉ ሁኔታ አስፈላጊ ላይሆን ይችላል።

ምክንያቱም ሕዝብን መዋሸትና ማጭበርበር ስለማይኖርብን ነው።በእርግጥ የአገሪቱን ሰላምና አንድነት በመጠበቁ በኩል ለሚደረገው የማረጋጋት ሁኔታ ይህ አይነቱ የፖለቲካ ዘመቻ ቀመር ወይንም የፖለቲካ ቁማር ጨዋታ ጠቀሜታው የጎላ ይሆናል።ከሌላ አገርና መንግሥት ጋር በሚደረገው ውይይትና ስምምነት ግን ሁሉም ነገሮ ጎልቶ የሚንጸባርቅ ከመሆኑም ባሻገር ድርጊቶቹ ተግባራዊ ቢሆኑ ሊያስከፉ የሚችሉ አይደለም።ይህ መሆን የሚቻለው ግን በፖለቲካ ውስጥ ያለውን ልምድ፣ጥበብ፣ከበላይ አካሎቻችን የሚሰጡንን መመሪያዎች ተግባራዊ እንድናደርግ የተሰጡንን የቤት ሥራዎች በአግባቡ መወጣት ስንችል ብቻ ነው።

 ለዚህም ነው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር የነበሩት ዕውቁ ዲፕሎማት ዶክተር ኽንሪ ኪስንጀር «የፖሊሲ ወይም የመመሪያ ጥበቡ የተቃዋሚውን ወገን የፖለቲካ ስሌት ውድቅ የሚያደርግ የሃገርን ጥቅምና ጉዳት የሚዳስስ የፖለቲካ ቀመር  መዘርጋት አስፈላጊ ነው።» የሚሉት።

 ማንኛውም የውጭ ዲፕሎማትም ሆነ የውጭ አገር ዜጋ

በኢትዮጵያ ውስጥ የሚሰማራው ለአገሩ ጥቅም ሲል መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።

ምክንያቱም የአገሩ ጥቅም በማስከበሩ በኩል ሁኔታዎችን በማመቻቸት በኩል የሚያደርገው እንቅስቃሴዎች በሙሉ በጥንቃቄና በብልሀት የታገዙ ስለሆነ ነው።ይህም ማለት ዲፕሎማቶችም ሆኑ የውጭ አገር ሰዎች የሚሰሩትና የሚያደርጉት ነገሮች ሁሉ በአጠቃላይ የተጠኑ ናቸው።ለዚህ ደግሞ የቅርብ ተባባሪያቸው የሚሆኑት ከአገራቸው አንድነትና ነፃነት ብሎም ጥቅም ይልቅ ለገንዘብ ህሊናቸውን የሸጡ  አሳሞች የሆኑ ባንዳ ኢትዮጵያውያኖች የአገርን ሚስጥር በመሸጥም ይታወቃሉ።እነዚህ ባንዳዎች ከጣሊያን ወረራ ጊዜ ጀምሮ እስካሁን እስከ አባዩ ግድብ ድረስ ምን ያህል ጉዳት በሕዝባችንና በአገራችን ላይ ሲያደርጉ እንደቆዩ ለማየት ችለናል። በዚህ በኩል የኢትዮጵያ የውጭ ጉድይ ሚኒስቴር እንደሌሎች የሰለጠኑ አገሮች በየኢምባሲው የሚመድባቸው ወይንም የመደባቸው ሰዎች የአገርን ስም ክብር በማስጠበቁ በኩል ምን እየሰሩ እንደሆኑ መከታተልና የሥራ አፈጻጸማቸውን መገምገም፤

አንድ ሰራተኛ ለረጅም ጊዜ በአንድ ኢምባሲ ውስጥ እንዲቆይ አለማድረግ ይጠበቅበታል።ከዚህ ሌላ የስርዓቱ ደጋፊና ተቃዋሚ መሆናቸውንም መገንዘብ ሌላው አስፈላጊው ነገር ነው።

በእርግጥ እንግሊዞች እንደሚሉት An ambassador is an honest man lies abroad for the sale of his country  «አምባሳደር ለሃገሩ ሲል በውጪ ሃገር የሚዋሽ ሐቀኛ(ተአማኝ)ሰው ነው»እንደሚሉት አስፈላጊ ሊሆን ይችላል።ግን እስከ ይት ድረስ ነው ይህ አይነት ቁማር ጨዋታ እየተጫወቱ ሊዘልቁ የሚችሉት  የሚለው ቃል ሊሰመርበት ይገባል።

   ሌላው በመዝሙር ዳዊት 67 ቁጥር 37 ላይ እንደተጠቀሰው «ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች»ይላል። እንጂ  ወደ አሜሪካ ወይንም ወደ ሌላ የአደገች አገር ትዘረጋለች ብሎ የተጻፈ ነገር አላየንም።ካለፉት ጊዜያትም ሆነ በአሁኑ ወቅት እንደ ተማርነው አሜሪካም ሆነ የቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት የአሁኗ ሩሲያ ጥሩ ነገር ሲያደርጉልን  አልነበሩም። ወደፊትም ያደርጉልናል ብለን አናስብም።

 ሌላውን ትተን አሜሪካ ከአመታት በፊት በአባይ ጉዳይ ለግብፅ አግዛ ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማድረግ የፈጠረችውን ሁኔታ ማስታወስ ይቻላል።የቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት የስታሊንን ጽንሰ ሀሳብ በአገራችን ላይ በማስረፅ ዛሬ እጇን አጨብጭባ ብቻውን እንዳልቀረች «የእራስን ዕድል በእራስ መወሰን እስከ መገንጠል »የሚለውን ሁኔታ ደርግ ኢሠፓን በባዶ ቃላት እያማለለችና የኢኮኖሚውን ጥቅም እያስጠበቀች ኢትዮጵያን ከኤርትራ እንድትገነጠል ብታደርግም እሷም በኢትዮጵያ ላይ ባደረገችው ደባ የእጇን አግኝታ ብትንትኗ ለመውጣት ችሏል።

ሶቭት ኅብረት ብትንትኗን እንዲወጣ ያደረጋት የዕድገትና የአንድነት ፀር የሆነው የእራስን እድል በእርስ የመወሰን እስከ መገንጠል የሚለው በእንግሊዘኛው self determination up to secession የሚለው የስታሊን ፅንሰ ሐሳብ በተለይም ርዕዮት ዓለሙ በመላው ሶቭት ኅብረት

ተቀባይነት አግኝቶ ስለነበር ነው።

አሁንም  በኦሮሚያና በሌሎች ክልሎች ጦር የሰበቁ ወገኖች  ይህንን  የስታሊን ፅንሰ ሐሳብ እንግበው  እንዳይጓዙ  ፍራቻ አለኝ። 

 ኢትዮጵያ ከሱማሌላንድ ጋር፤ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር፤ኢትዮጵያ ከኬንያ፤ኢትዮጵያ ከኡጋንዳ፤ኢትዮጵያ ከሱዳን፤ኢትዮጵያ ከጅቡቲ ከአደጉ ሀገሮች ኢትዮጵያ ከአሜሪካ፤ኢትዮጵያ ከቻይና፤ኢትዮጵያ ከፈረንሳይ፤ኢትዮጵያ ከጀርመን ሌላው ቀርቶ ከቱርክና ከተባበሩት አረብ ኤሜሬት ጋር  ያደረገቻቸቅን ስምምነቶችና አካሄዶችን  ስናጤን  የኢትዮጵያን ጥቅም በማስገኘቱ በኩል  የተካሄደው  አካሄድ  ጥሩም  ሆነም  አልሆነም  ይህ የሚያሳየው  የዶክተር አብይ መንግስት ከውጭ አገራት ጋር የሚያደርጉት የፖለቲካ ቀመር  ወይንም የፖለቲካ ቁማር

ጨዋታ የተዋጣለት  ነበር ወይም አልነበረም  ብሎ  ለመናገር አስቸጋሪ ቢሆንም  ከሞላ ጎደል  እንደሌሎቹ መሪዎች  ግትር ከመሆን ይልቅ ፍሌክሴብሊቱ  በመሆኑ እረገድ  ዶክተር ዐብይ የተሻሉ ናቸው።

 ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ከግብፅ ጋር ከፕሬዝዳንት ናስር ጀምሮ የነበረው አለመግባባትና አማጽያንን በማደራጀትና ኢትዮጵያ ሰላም እንዳትሆን ከፍተኛ ምዋለ ንዋይ በማፍሰስ ጉሉ ሚና ስትጫወት ቆይታለች።  አባይን በመገደብ እያደረግነው ያለውን እንቅስቃሴ ግን ልታቆመን አልቻለችም።በፖለቲካውም የቁማር ጨዋታው  ግብፅን ከዚህ በፊት ከሚረዷት ዓረብ አገሮች እንዲሁም አማፅያንን በመርዳትና መሸሸጊያ ከሚያደርጉ ከጎረቤቶቻችን ከኤርትራ፣ከሱዳን፣ከሱማሊያ፣ከኬንያ፣ክጅቡቲ ጋር የጀመረችው  መልካም ግንኙነትና በአካባቢው ሰላም ዙሪያ  ከፍተኛ ቅቡልነት አገራችን ለማግኘት መቻሏ በቁማር ጨዋታው  የበላይነትን ለማግኘት አስችሎናል።

 አንድ ሰው  የተማረ ስለሆነ ብቻ አገር መምራት አይችልም።ከዚህ በፊት ብዙም  የሰለጠነው  ዓለም  ትምህርት ያልነበራቸው አባቶቻችን በአሁኑ ወቅት ተምረናል ከሚሉ ባለስልጣኖቻችን የተሻለ በብሄር፣በጎሳ፣በኅይማኖት ያልተከፋፈለ ህዝብ አንድ አድርገው አስረክበውናል።እኛ ትውልድ ጋር  ሲደርስ የሀገር ፍቅሩንና  አብሮ በአንድነትና በፍቅር የመኖር እሴቶቻችንን አፈራርሰነው ከመተማመን ይልቅ  ተለያይተን በጎሪጥ  መተያየት ላይ ጀምርውናል።ስለዚህ   ባለስልጣን መሆን አለብኝ የሚል ሰው ስልጣን ላይ ከመውጣቱ በፉት የብሄርተኝነት አመለካከትካባውን   በቅድሚያ  ማንሳት  ይገባዋል።

ምናልባትም  እኮ የግድ  ባለስልጣን  መሆን አልብኝ ብሎ ክችች ብሎ ከሚያኮርፍ ይልቅ  ግለሰቡ ባለስልጣን ከመሆን ይልቅ በተሰማረበት ሙያ ውጤታማ  ሊሆንም  ይችላል።እንዲያውም  ባለስልጣን መሆን በፊት በነፃነት ሲንቀሳቀስ የነበረውን መብቱንም በራሱ ላይ አሳጥቶና ገደቦ እራሱን በካቴና እንደማሰርም ይቆጠራል። 

 በአፍሪካ በአብዛኛው ፖለቲከኞች ይህን አይገነዘቡም  ለእነሱ ስልጣን ሀገር ምድሩ የሚሰግድለት፤እንዳሻው  በሀገሩ ላይ ወገኑንና ህዝቡን እንደፈለገ  እያደረገና እርስ በእርስ እያባላ መኖር ደስታ ነው  የሚሰጣቸው። ይህ ብቻ አይደለም  የስልጣን ሽኩቻዎችም እንደቀጠለ ነው።ይህ ላለፉት በርካታ አመታት  የአገራችን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካውያን የውስጥ ችግር ሆና ቆይቷል።ወደፊትም ሊቀጥል ይችል ይሆናል።

 የአቶሚክ ኢነርጂን ቀመር ያገኘው  ፕሮፌሰር አልበርት አንስታይን የእሥራኤል ፕሬዝዳንት እንዲሆን በጋዜጠኞች ተጠይቆ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥቶ ነበር«በሳይንቲፊክ ጣጣዎች ብትጠይቁኝ ለእኔ ተስማሚ ናቸው።ሰዎችን ለመምራት ግን የተፈጥሮ  ስጦታ ወይም አስፈላጊ ልምድ የለኝም» በማለት አገር ለመምራት ብቃት እንደሌለው ገልጾ ነበር።

ታዋቂው ፈላስፋ የማያውቁትን አውቃለው ብለው ማሰብ እንደሌለባቸው እንዲህ በማለት ገልጾ ነበር «አንድ ሰው የማያውቀውን ነገር አውቀዋለሁ ብሎ ማሰቡ በእርግጥ የተጨበጠ ድንቁርና ነው።...የእኔ ዕውቀት አለዋቂ መሆኔን ማወቄ ብቻ ነው።»ብሏል።

 ከዚህ አንፃር የፖለቲካ ቀመር ወይንም እንደ ውጫሌው 17ኛው አንቀፅ አይነት ጣሊያን እንደተጫወተችብን አይነት የፖለቲካ ቁማር ጨዋታ መጫወት ትርፉ ኪሳራ ነው የሚሆነው።

ወደ ኋላ 22 አመት ተመልሰን በምርጫ  84 ላይ ተከስቶ የነበረው ን ሌላኛው የፖለቲካ ቁማር ጨዋታ መሪዎቻችን በኃይል የያዙትን በካርድ ላለመልቀቅ ሌላኛው አንዱ አሳዛኝ ማሳያ ሆኖ አልፏል።ዋንኛ የኦሮሞ ተቃዋሚ ፓርቲ የሆነው ኦነግ ምርጫው አስር ቀናት ብቻ በቀሩት ጊዜ ጊዜ እራሱን ከምርጫው አግሏል።ወያኔ በወቅቱ ኦነግ ከምርጫው እንዲወጣ ያደረገው የፖለቲካ ቁማር ጨዋታ ግን ያሳዝን ነበር።

«...በደም የተገኘ ድላችንን በካርድ አናስረክብም ።በመላው ኦሮሚያ በቂ ዝግጅት የለንም።ኦህዴድ ተጠናክሮ አልወጣም ሳምሶናይታቸውን አንጠልጥለው ለመጡት ኦነጎች በምርጫ ስም አገሪቱን አናስረክብም ።ወይ ምርጫው ይሰረዛል፤አሊያም ኦነግ ከምርጫው መውጣት አለበት!»የሚል አቋም የወያኔ አመራሮች በመያዛቸው

በመጨረሻው ዕለት ዋዜማ ኦነግ ከምርጫው እራሱን በማግለሉ ወደ ጫካው ለመግባት መገደዱ ይታወሳል።

የኢህ አዴግ አመራሮች በወቅቱ ሁለት የፖለቲካ ቁማር ጨዋታ ወይም ቀመር ይዘው ብቅ ብለው ነበር።የመጀመሪያው አሳብ ኦህዴድን ማጠናከር ሲሆን፤ሁለተኛው ደግሞ የመጀመሪያው ካልተሳካ  ኦነግን ማላመድ Domesticate ማድረግና ጭንግፍ እየሆነ ያስቸገረውን ኦህዴድን ማስወገድ የሚሉ አማራጮችን ይዞ ነበር ሲንቀሳቀስ የነበረው።ሆኖም ኦህዴድን ማጠናከርም ሆነ ኦነግን ማላመድ የማይቻልበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል።ይሁንና የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ «ኦነግን ማላመድ»የሚለውን አሳብ አጥብቆ ይገፉበት እንደነበር ነው የተገለፀው።

  የአገሪቱ መሪዎችና ፖለቲከኞቻችን በሕዝቡ ላይ የዘሩት የጥላቻና የዘር ፖለቲካ ፤በአገርና በህዝብ ላይ ያመጡት ጉዳት ዛሬም በግልፅ እየታየ ነው።ይህ አገርን የማፈራረስና ዘር የማፅዳት ፖለቲካ አንድ ቦታ መቆም እንዳለበት በቅርቡ በአገራችን ውስጥ የተከሰተው ድርጊት ያመላከተ ነው።

ለዚህም የአገር ሽማግሌዎች፣

የኅይማኖት አባቶች፣

ፖለቲከኞች፣ሚዲያውና ለሰላም የቆመው ሕዝብ በአጠቃላይ ስለሰላም መዘመርና የተጀመረውን የፖለቲካ  ቁማር ጨዋታ በይበልጥ ማጠናከር ያስፈልጋል።

 በተደረገው የፖለቲካ ቁማር ጨዋታ አብዛኛው ተቃዋሚዎች የኢትዮጵያ መንግስት የሚያካሂደውን የፖለቲካ አካሄድ የሚደግፉ እንዳሉ ሁሉ የማይደግፉም አሉ።

 «...የፖለቲካ ቁማር ጨዋታ የትም አያደርስም።አብላጫ ድምፅ ያለው ሃገሪቱን ሊመራት ይገባል።መንግስት ዴሞክራሲን እንደ ማጭበርበሪያ መጠቀም 

አይኖርበትም »በማለት ይገልጻሉ።

 የፖለቲካ ችግሮቻችንን የሚፈለፍሉትና የሚያባሉን ጠላቶቻችን ናቸው።ጠላት ደግሞ ምንግዜም ለጠላቱ በጎ አይመኝም ።ጠላቶቻችን ደግሞ ከጎረቤት አንስተን እስከ ሩቅ ያሉ ወገኖች ፤ከትንሽ

እስከ ትልቅ ይለያያሉ እንጂ በጣም ብዙ ናቸው።የጠላትነት መንሥኤዎች ጥቅማጥቅም (ቅኝ ገዢዎች)፣ድንበር፣አባይ፣ስትራቴጂ ፣ እና ሃይማኖት ሆነው ቆይተዋል።ይህ ችግር ያለፈ ለታሪክ የተተወ ሳይሆን ፤ለዛሬም ለነገም እየተሻሻለና መልኩን እየለወጠ የሚከሰት ስለሆነ በረጋ መንፈስ እና በጥንቃቄ መያዝ ይኖርብናል።

መሪዎቻችን ከሁሉም በላይ ሊገነዘቡት የሚገባው ነገር ቢኖር አገር ከመምራታቸው አስቀድሞ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት ይበልጥ መጣር ይኖርባቸዋል።ይህን ደግሞ ለማሳካት የህዝቡን ፍላጎትና የልብ ትርታ ማዳመጥና ህዝቡ የሚፈልገውን ነገር ከሞላ ጎደል ተግባራዊ ማድረግ ዋንኛው አላማቸው ሊሆን ይገባል።ሌላው  በዚህ አስከፊና እርስ በእርስ እየተባላን ሰላም በሌላት ኢትዮጵያችን ሰላምን በሀገሪቱ ለማምጣት ህዝብን መዋሸትና ያለ የሌለውን ነገር እየቀባጠሩ መጓዝ ከጉዳቱ ይልቅ ጥቅሙ የሚያመዝን ይመስለኛል።ሰው ዋሽቶ የተጣሉ ሰዎችን ያስታርቅ የለ? ስለዚህ በኢትዮጵያ ሰላም ለማምጣት ውይይቱና ድርድሩ እንዳለ ሆኖ  ብውሸት ቢደራረብበት የሚያመጣው ጉዳት አይታየኝም።ጉዳት የሚኖረው ውሸቱ ለበጎ አላማ መሆኑ ቀርቶ ቃታ ለመሳብ ከሆነ አደጋ አለው።«ሕዝብ የማይደግፈው አማጺ ከባህር የወጣ አሳ ነው»እንደሚባለው እንዳይሆን መሪዎቻችንና ተቃዋሚ ፖለቲከኞቻችን  ጠንክረው መስራት ይኖርባቸዋል እላለው ።አበቃው!ክብረት ይስጥልኝ!