መጪው የኢትዮጵያ እጣ ፋንታ


ከወሰንሰገድ መርሻ ደምሴ (ጮራ ዘአራዳ)

(ደራሲ፣ጋዜጠኛና ማህበራዊ ሀያሲ)

 የዐብይ እና የኢሳያስ ፊትና ጀርባ መሆን 

 የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የምስራቅ አፍሪካ  ኃያል መንግስት የመሆን ታላቅ ምኞት አላቸው።  እሳቸውና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይን አላማቸውን ለማሳካት እንቅፍትና ለስልጣናቸው አስጊ ነው ብለው  ስለሚያምኑ በጣምራ ሆነው  ተወግተዋል።  በዚህ ጦርነት ውስጥ ብዙም ድርሻ የሌላቸው ኤርትራውያን ባድሜን  በእጃቸው ለመክተት ሲሉ በዚህ እርባና በሌለው ግጭት ውስጥ  ተሳትፈው  ነበር ።

 የኢትዮጵያ ጦር ከኤርትራ ወታደሮች ጋር በቅርበት በመቀናጀትና አልፎ ተርፎም በኤርትራ አዛዦች እየተመራ ዘመቻውን ከኤርትራ ሲያካሂድ መቆየቱ የአደባባይ ሚስጥር ነው።  ያም ሆኖ ይህ ግን ኤርትራ በህዳር ወር በፕሪቶሪያ የተፈረመውን የጦርነት ማቋረጥ ስምምነት (CoHA) ድርድር ላይ  ባለመሳተፏና ዶክተር  ዐብይ ከህወሓት ጋር  ስምምነት በመፍጠራቸው  የኤርትራ ባለስልጣኖችን አስቆጭቷል።

 ሰነዱ ወደ ሰሜን ትግራይ የሚዘረጋው የኤርትራና የኢትዮጵያ ድንበር አከላለል ላይ በተመለከተ ምንም እንኳን በሄግ የተሰበሰበው የተባበሩት መንግሥታት የድንበር አካለል ቡድን ውሳኔ  ቢሰጥም ህወሓት አሁንም  ውሳኔውን እንደ አከራካሪ ጉዳይ ነው የሚመለከተው  ይሁንና የዶክተር አብይ መንግስት ግን ከዚህ ለየት ያለ ሀሳብና አመለካከት  ነው  ያለው።የሄግን ውሳኔ ማክበር አለብን  ባይ  ናቸው።በዚህም የተነሳ በመቶ ሺህ የሚቆጠር ደም የፈሰሰበትን ባድሜን ሻዕቢያ  ይህንን የሰሜኑን ጦርነት ተንተርሶ በእጁ በቀላሉ አስገባ።

 በአብይና በአቶ ኢሳያስ መካከል የተደረገው  የመመቻቸት ጋብቻ ለትግራይ መሪዎችና አክቲቪስቶች ትልቅ የፕሮፓጋንዳ ጥቅም ሰጥቷቸው ነበር።ዐብይን “ብሔራዊ ከዳተኛ” ብሎ በመሳል ሲናገሩ ኤርትራዊያንን ደግሞ  «ሰይጣናዊ አመለካከት ያሏቸው» በማለት ተችተዋል ።በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የመጀመሪያዎቹ ሁለት የስልጣን ዓመታት ውስጥ ብቻ ሁለቱ መሪዎች ቢያንስ 14 ጊዜ ከአዲስ አበባ ወደ አሥመራ፥ ከአሥመራ ወደ አዲስ አበባ ተመላልሰዋል። 

ይህ ግን የመቶ ሺህዎችን ሕይወት ከቀጠፈው የትግራይ ጦርነት በስምምነት መጠናቀቅ በኋላ ፈጽሞ ሊታይ  ግን አልቻለም።ቢቢሲ እንደገለፀው  የኤርትራ ሕዝባዊ ግንባር ከፍተኛ አመራርና የቀድሞ ዲፕሎማት የነበሩት አምባሳደር አብደላ አደም በበኩላቸው በዐቢይ እና በኢሳያስ መካከል ያለው ግንኙነት “የግል” እንደሆነ ከዚህ በፊት በኢሳያስ እና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መካከል የነበረውን በመጥቀስ “ታሪክ ራሱን እንደደገመ” ይናገራሉ። 

የሁለቱ አገራት መሪዎች ግንኙነት ተመስርቶ የነበረው የጋራ ጠላት ባሉት ህወሓት ላይ ነው የሚሉት አምባሳደር አብደላ፣ በሁለቱ ሀገራት መካከል መደበኛ የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ለመፍጠር ያለመ አልነበረም ይላሉ።

«በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል እንደ የድንበር ማካለል፣ የኢኮኖሚ ስምምነት እና ግንኙነት የመሳሰሉ ዋና ዋና ጉዳዮች አሉ። ግን ይህ ሁሉ ወደ ጎን ተትቶ ቆይቷል። ህወሓት ለማጥፋት ያለሙት ውጥን ‘እንቅፋት’ ስለገጠመው ሳይሳካ ቀርቷል።»የሚሉት ዲፕሎማቱ፣ ለዚህም ቀጥተኛ የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት እና ጫና መፍጠር ዋና ምክንያት እንደሆነ ይገልጻሉ። 

ከዚህ ባሻገር፤ ኤርትራ ከፕሪቶሪያ የተኩስ አቁም ስምምነት በመገለሏ ፕሬዝደንት ኢሳያስ ክህደት እንደተሰማቸው ያስረዳሉ።

ይህንንም ሲያብራሩ ፕሬዝደንት ኢሳያስ በአፍሪካ ሕብረት፣ በአሜሪካ እና በኢጋድ አደራዳሪነት የተደረገውን ስምምነት «የማስተጓጎል ዘዴ» ሲል መውቀሳቸውን ይጠቅሳሉ። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመካከላቸው ያለውን አለመግባባት ለመፍታት ሙከራ ማድረጋቸውን የሚናገሩት አምባሳደር አብደላ፣ ከኤርትራ መሪ በኩል አዎንታዊ ምላሽ አለማግኘታቸውን ይገልጻሉ። 

የአማራ ክልል ግጭትና የአኤርትራ አቋም

 

ከትግራይ ጦርነት በኋላ ወደ ተመሳሳይ ደም አፋሳሽ ግጭት የገባው የአማራ ክልል ሁኔታ ቢያንስ በሁለቱ መሪዎች መካከል አለመተማመን ሊፈጥር የሚችል አደገኛ ሁኔታ ነው ይላሉ አምባሳደር አብደላ።

ኤርትራ ህወሓት መራሹን የኢህአዴግን አገዛዝ ለማስወገድ እንደ ግንቦት 7 ያሉ ታጣቂ ቡድኖችን እና ተቃዋሚዎችን ስታሰለጥንና ስታስታጥቅ ነበረ።አሁንም ፋኖን የምታሰለጥነውና ወደ ውጊያ የምታሰማራው ኤርትራ አድርጎ ነው የኢትዮጵያ መንግሥት በተደጋጋሚ የሚገልጸው።ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ የውጭ ጠላቶች ኢትዮጵያ በቀጠናው ጎልታ ትወጣለች በሚል ስጋት የውስጥ ግጭቶችን እያባባሱ ናቸው ብለዋል

የውጭ ጠላቶች በኢትዮጵያ ላይ “የውክልና ጦርነት” ከፍተውባታል ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ተናገረዋል።

ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ይህን ያሉት የ128ኛውን የአድዋ ድል በዓል አስመልክቶ ‘በአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም’ በነበረው ዝግጅት ላይ ተገኝተው ባሰሙት ንግግር ነው።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ኢትዮጵያ ባላት ስትራቴጂካዊ አቀማመጧ እና በታሪኳ ምክንያት “ምንጊዜም በክፉ የሚመለከቷት የውጭ ጠላቶች አሏት” ብለዋል።

«እነዚህ የውጭ ጠላቶች የኢትዮጵያን ሰራዊት ፊት ለፊት ተዋግተው ማሸነፍ እንደማይችሉ ያውቃሉ። በቀደሙት ጊዜያት በተለያዩ የሀገሪቱ ጠረፎች ኢትዮጵያን ለማንበርከክ ባካሄዷቸው ጦርነቶች አሳፋሪ ሽንፈት ተከናንበዋል።»

የውጭ  ጠላቶች በኢትዮጵያ ላይ “የውክልና ጦርነት” ከፍተዋል- ሲሉ ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ገልጸዋል።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ በዚህ ንግግራቸው የውጭ ጠላቶች የሚላቸውን በስም አልጠቀሷቸውም።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ በዚህ ንግግራቸው  የውጭ ጠላቶች የሚሏቸውን በስም አልጠቀሷቸውም።

የውጭ  ጠላቶች፣ ኢትዮጵያውያን ያለፉትን ጦርነቶችን ያሸነፉት በአንድነት በመቆም መሆኑን ተገንዝበዋል ያሉት ፊልድ ማርሻሉ በቀጥታ ከመግጠም  ይልቅ የውስጥ  ክፍፍል ፈጥሮ ማዳከምን መርጠዋል በማለት  ከሰዋል።

ፊልድ ማርሻሉ የውጭ ጠላቶች በኢትዮጵያ ላይ ጦር ከማዝመት ይልቅ «እርስ በእሰርስ የሚያጋጭ ትርክት በመፍጠር ከፋፍሎ በማዳከም እና ባንዳዎችን ቀጥረው የውክልና ጦርነት እንዲያካሂዱላቸው ማድረግን መርጠዋል።ሲሉ ተደምጠዋል።

እነዚህ የውጭ  ጠላቶች  የሀገር ፍቅር ስሜት የሌላቸውን ዜጎች “ሀገራቸውን እንዲወጉ በመመልመል በገንዘብና በትጥቅ” በመደገፍ የውክልና ጦርነቱን አጠናከረው  መቀጠላቸውን ፊልድ ማርሻሉ አክለው ገልጸዋል።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ እንዳሉት ካለፉት አምስት አመታት ወዲህ እነዚህ ጠላቶች ኢትዮጵያ በቀጠናው ጎልታ ትወጣለች በሚል ስጋት የውስጥ ግጭቶችን እያባባሱ ናቸው።

«ከለፉት አምስት አመታት ወዲህ ‘ነጻ አውጭ ነን፣ የህዝብ ጥያቄ ተሸክመናል’ እያሉ ወደ ውጊያ የገቡ ኃይሎች በተጨባጭ እያስፈጸሙ ያሉት የውጭ ጠላቶቻችን ተልእኮ” ነው ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ይህን የማይገነዘብ ኢትዮጵያዊ “የሀገራችንን ሁኔታ ያልገነዘበ መሆን አለበት።» ሲሉ ተናግረዋል።

ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ “በትጥቅ እና በሚዲያ የሚደገፉ ታጣቂ ኃይሎች” በተለያዩ ቦታዎች አሳት በመለኮስ የመከላከያ ሰራዊት በስምሪት እንዲወጠር እና እንዲዳከም ሰርተዋል ብለዋል።

«ታጣቂ ቡድኖቹ መከላከያው  የውጭ  ጠላት ቢመጣ  መከላከል እንዳይችል ለማድረግ ሰርተዋል ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ‘እንታገልለታለን።»የሚሉትን ህዝብም ለችግር ዳርገዋል ብለዋል።

በአሁኑ ጊዜ የታጣቂ ቡድኖቹ ዋና ኃይላቸው  መደምሰሱን የገለጹት ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ «በቅርብ ጊዜ ግብአተ መሬታቸው  ይፈጸማል»ሲሉ ተናግረዋል።

«አዲስ አበባን በጥቂት ቀናት እንቆጣጠራን ያሉ ህልመኞችም” እንቅስቃሴም በመከላከያ እና በጸጥታ ኃይሎች መምከኑን ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ተናግረዋል።

ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ለውጭ ኃይሎች የተገዙ «ባንዳ» ሲሉ የጠሯቸው ታጣቂ ቡድኖች የትኞቹ እንደሆኑ በስም አልጠቀሱም።

ነገርግን በአሁኑ ወቅት መከላከያ ሰራዊት፣ የፌደራል መንግስት በሽብር ከፈረጀው ‘ከኦነግ ሸኔ’ እና ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር የትጥቅ ግጭት እያካሄደ ይገኛል።

በተለይም በአማራ ክልል ባለፈው አመት ሚያዝያ ወር ከክልል ልዩ ኃይሎች መፍረስ ጋር በተያያዘ የተነሳው የትጥቅ ግጭት የፌደራል መንግስትን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲያውጅ አስገድዶታል።

መንግስት ባለፈው ሀምሌ ወር የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጥር መጨረሻ ጊዜው ሲጠናቀቅ “የሚቀሩ ስራዎች” እንዳሉ በመጥቀስ ለተጨማሪ አራት ወራት አራዝሞታል።

በግጭቱ የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች በንጹሃን ላይ በርካታ ግድያ መፈጸማቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን እና ሌሎች የመብት ተቋማት ተደጋጋሚ ሪፖርት አውጥተዋል።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከወራት በፊት በመንግስት መገናኛ ብዘኻን በተላለፈ ቃለ መጠይቅ ሰላማዊ ሰዎችን በማይጎዱበት ሁኔታ በድሮን ጭምር ጥቃቱ እንደሚቀጥል መናገራቸው ይታወሳል።

ትጥቅ ማስፈታት።

 ወደ 250,000 የሚጠጉ ወታደሮች ለህወሓት የሚዋጉ አሉ።  ሁሉም  መከላከያ ውስጥ  ትጥቃቸውን አልፈቱም  ? ይህ በአማራ አዋሳኝ የይገባኛል ጥያቄ ያነሳው ህወሓት እንዲህም ባድሜ በጭራሽ ለኤርትራ አይሰጥም ያለው ህወሓት ከኤርትራ ጋር ጦርነት ወደፊት ይግጠም ወይም አይግጠም የሚታወቅ ነገር የለም።ምናልባትም በሰላማዊ መንገድ ሊፈታ ይችላል።ይህ በሰላማዊ መንገድ ከተፈታ ቀጣዩ የሚሆነው ምንድን ነው ብለን ስንጠይቅ  የህወሓት ታጣቂዎች  የሲቪል ሕይወት በመመለስ ደስተኛ  ህይወት ይመሩ  ይሆን? ወይስ ከመከላከያ ጋር ይቀላቀሉ ይሆን ? ይህ  የሚታወቅ ነገር አይደለም።

 እነዚህ ድንገተኛ ሁኔታዎች ፈጣን ትጥቅ የማስፈታት እድል እንዳይኖራቸው ያደርጉታል። ትግራይን የሚያስተዳድሩት  አቶ ጌታቸው ረዳ ትጥቅ ለማስፈታት አመታት ሊወስድ እንደሚችል በይፋ  መናገራቸው  አይዘነጋም።

ኢትዮጵያን በአንድነት ማቆየት።

 በመሰረቱ የትግራይ ብሄርተኝነት ለህወሓት ማለት ትግራይ የኢትዮጵያን መንግስትና ፖሊሲዋን ይቀርፃል ወይም ተነጥሎ ይኑር ማለት ነው።  አማራው ና ኦሮሞው  ስለ ብሄር ብሄረሰቡና ስለክልላቸው ተመሳሳይ ስሜት አላቸው።  የህወሓት አመራር አሁን ከዶክተር ዐብይ ጋር መልካም የሆነ ግንኙነት ላይ ያሉ ይመስላል።ፕሬዝዳንቷም በ128 ኛው የአድዋ በዓል ላይ በመገኘት ልብ በሚነካ መልኩ የጦርነትን አስከፊነት እምባ እየተናነቃቸው አውርተዋል።በተለይም አንዲት እናትንበትምህርት ቤት እርዳታ ጣቢያ  አናግረው   ትንሽ ዕቃ ነገር ሲሰጧት ብለው አልፈልግም በማለቷ ምክንያቱን ጠይቀው የአንቺ ዕቃ ጠላ እየሸጥኩ ያሳደጉት ሁለት ልጆቼን አይመልስም እንዳለችው ገልፀዋል።ስለዚህ ጦርነት መቆም እንዳለበት ተናግረዋል።  በፕሪቶሪያ ስምምነት ላይ የተፈራረሙት ቀለም ከመድረቁ በፊት በኦሮሚያ በወለጋ ያለው ሁኔታ ጉዳይ እንደ ትግራይ ሆኖ ብዙ ብጥብጥና መፈናቀል በክልሉ አስከትሏል።  በኦሮሚያ ያለው ተጨማሪ አመጽ በዚሁ ከቀጠለ የኢትዮጵያን ውድቀት ሊያስከትል ይችላል የሚል ፍራቻ ቢኖርም  ዋና አዛዡ   ከላይ እንደተጠቆመው በቅርቡ  ወደ መቃብር እንልካቸዋል ጦርነቱን በድል እንደሚጠናቀቅ  በልበ ሙልነት ተናግረዋል ።  አዲስ አበባም ሆነ ፊንፊኔ (የኦሮሞ ብሔርተኞች እንደሚሉት) የባለቤትነት ትግል እይታ ውስጥ  ወድቃለች።  በአሁኑ ወቅት ፌደራሊዝም የበለስ ቅጠል ሆኗልና። ኢትዮጵያ ውስጥ  ያሉ ክልሎች ይህንን ሁኔታ  ነባራዊ እያደረጉት ይገኛሉ ።

 ለተለያዩ የጥፋት መስመሮች መፍትሄ ካልተገኘ፣ ኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ መፈራረስ  ላይ ልትወድቅ የምትችል ኢምፓየር ልትሆን ትችላለች።  በርግጠኝነት ዶክተር አብይ የወረሷት ኢትዮጵያ በብሄር ብጥብጥና በስራ እጦት ምክንያት  ህዝቦቿ እየተናወጡ ይገኛሉ። ዶክተር ዐብይ እንደ ቤዛ፣ የለውጥ ወኪልና የኖቤል የሰላም ሽልማት እንዳልተቀበሉና እንዳልታዩ ዛሬ በህዝቦቿ ዘንድ ዓይንክ ላፈር መባል ጀምረዋል ።  የብሄር ግጭት በኢትዮጵያ የዘውትር ጥያቄ ቢሆንም  ለዚህ  ሁሉ ምንስሄ የቀድሞ  የኢትዮጵያና የህወሓት መሪ የአቶ መለስ የጆሴፍ ስታይል አመለካከት ማንፀባረቃቸው ነው።ዶክተር አብይ በአጭር የስልጣን ዘመናቸው ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ደም መፋሰስ ውስጥ ሀገሪቷ ገብታለች። በዚህም የተነሳ ኢትዮጵያን አጣብቂኝ ውስጥ  ከቷታል።

 እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች መንግሥት በተጨቃጨቀባቸው አገሮች ከባህላዊ ሞዴሎች በላይ ማሰብ ያስፈልጋል።  በክልልና በጎሳ ባለስልጣናት መካከል ያለውን ክፍፍል የበለጠ ማሰስ ያስፈልጋል።የፖለቲካ ተሀድሶ ኢትዮጵያ በህይወት መኖር ከፈለገች ባህላዊ የመንግስት መዋቅሮችን ከመጫን ይልቅ እንደ ልቅ ኮንፌዴሬሽን ያሉ አዳዲስ አቀራረቦችን መመርመር ይኖርበታል።

ዓለም አቀፍ  እይታዎች

 የኢትዮጵያ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ እና ጂኦፖለቲካል አቋም እነዚህ ችግሮች ካልተፈቱ ዓለም አቀፍ አንድምታ ይኖራቸዋል ማለት ነው።

 በኢትዮጵያ ያለው ትርምስ የአሜሪካንና የቻይና ጦር ሰፈርን የምታስተናግድ እና ቀድሞውንም በገዢው ኢሳ ላይ የአፋር አመጽ ያላት ጅቡቲን ጨምሮ ጎረቤት ሀገራት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ይኖረዋል።  ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የአፋር ህዝቦች በኤርትራ እና በኢትዮጵያ ይኖራሉ።  ጅቡቲ በኤርትራ ድንበር አቅራቢያ ወታደሮችንና ታንኮችን እያሰባሰበች ሳለ አልሸባብ ወታደራዊ ወረራ ፈጽሟል።  ሱዳን በአል ፋሽጋ ትሪያንግል ውስጥ ያለውን አወዛጋቢ ግዛት በመያዝ በኢትዮጵያ የተፈጠረውን ትርምስ ተጠቅማለች።  በተስፋፋ አለመረጋጋት፣ ብዙ የታጠቁ ቡድኖችና ስደተኞች  በአሁኑ ወቅት  በአካባቢው  ይኖራሉ።ከሱማሌላንድ ጋር የተደረገው  የወደብ ስምምነት  ከሙቃዲሾ ጋር ሌላ ውዝግብ አንስቷል።

የመጨረሻው ጨዋታ?

 በፖለቲካው ጨዋታ የትግራዩ ህወሓት በአሁኑ ወቅት  የአንበሳውን ድርሻ ይዟል ።ነገር ግን መላ አገሪቱ በአሁኑ ጊዜ ማስተዳደር  ባይኖርበትም የህወሓት ባለስልጣኖች  ዳግመኛ ወደ ስልጣን መምጣቸው አይቀርም።በተለይም  የኢትዮጵያን የተበላሸ አካሄድ ለማስተካከል ዶክተር ዐብይ የህወሓትን ቁልፍ ሰዎች ለሚፈልጉት ቁልፍ ቦታዎች  መምረጣቸው አይቀርም።ሌላው ቀርቶ በውጊያ ልምድ ያለው ሰራዊቱ ሳይቀር በአሁኑ ወቅት አስፈላጊ መሆኑን ይረዳሉ። በአብዛኛው ኢትዮጵያውያን ላለፉት 27 አመታት ሀገሪቱን በመሩበት ወቅት በፈፀሙት ብልሹ አመራር በህዝቡ ዘንድ ክፉኛ የተጠላው ህወሓት አሁን እየተናፈቀ  መምጣቱ ላያስገርመን ይችል ይሆናል።ዶክተር  አብይ በወለጋ፣ በቤኒሻንጉል፣ በቦረና፣ በባሌ፣ በአሩሲ፣ በአፋር፣ በሶማሌ እንዲሁም  በአማራ ክልል ሌሎች ጦርነቶች አሉባቸው።  በኢትዮጵያ ውስጥ ጦርነትና ብስጭት  ሀገሪቷን እንደ ምሶሶ ላይ እንዳለ ገመድ ተወጥሮ ተይዟል።እናም  ህወሓት  ወደ ቀድሞ  አመራር ሙሉ ለሙሉ ባይመጣም  ያለው  ሠራዊትና ጠንካራ አመራሮቹ ወደ ቁልፍ  ቦታዎች  መምጣታቸው አይቀሬ ነው።ይህ ደግሞ  የሀገሪቱን ሰላም በማምጣት በኩል ጉሉ ሚና መጫወት ይችላል ወይ የሚለው ጥ ያቄ ወደ ፊት የሚታይ ይሆናል።ይሁንና ግን ህወሓት በተለይም በሀገሪቱ  ላይ ሰላም  በማምጣት፤እንዲሁም  የተዝረከረከ አስተዳደር እንደአሁኑ  እንዳልነበረ ባለፉት 27 አመታት  አሳይተውናል።ይህን መካድ የለብንም

 ያም ሆነ ይህ ግን መካድ የሌለብን  የአ

ኢትዮጵያችን ውስጥ ወታደራዊ መፍትሄ ይገኛል ብሎ ለመገመት አስቸጋሪ ነው።በመመካከርና በመተሳሰብ ችግሮችን በሰላም መፍታት ከተማሩ ወገኖች የሚጠበቅ ነው። በተለይም የትግራይ ሃይሎች የገቡበትን ከበባ መስበር ባይችሉም ለዶክተር አብይም ሆነ ለማንኛውም የኤርትራና የኢትዮጵያ ሃይሎች በቆራጥነት እስከመጨረሻ መታግል እንደሚችሉ አሳይተውናል።  መጪው የኢትዮጵያ  እጣ ፋንታ ምን ይሆን ?  

አሁን ሁላችንም  መልሱን መጠበቅ ያለብን ጥያቄ  ቢሆን ይህ ብቻ ነው።አበቃው ! ክብረት ይስጥልኝ።