በባሕር ዳር ከተማ “በከባድ መሳሪያ” የታገዘ ውጊያ ተካሄደ


በአማራ ክልል ዋና ከተማ ባሕር ዳር ዛሬ አርብ የካቲት 22፤ 2016 ዓ/ም በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተኩስ ልውውጥ መካሄዱን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።

በከተማዋ ሦስት ቀበሌዎች ላይ አርብ ማለዳ 12፡00 ሰዓት ላይ ውጊያው መጀመሩን የተናገሩት አራት ነዋሪዎች፤ የከባድ መሳሪያ ድምጾችንም መስማታቸውን ተናግረዋል።

ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት ነዋሪዎቹ በከተማዋ ቀበሌ 14 አቡነ ሃራ እና ልደታ በሚባሉ የመኖሪያ ሰፈሮች፤ እንዲሁም ቀበሌ 11 አባይ ማዶ እየተባለ በሚጠራ ሰፈር እና ቀበሌ 13 ባታ ቤተ ክርስቲያን ወይም ወይራሚት አካባቢ በሁለቱ ተዋጊዎች መካከል ውጊያ መደረጉን ተናግረዋል።

አንድ የከተማዋ ነዋሪ “. . . ከጠዋቱ 12፡20 ጀምሮ ውጊያ ነበር። የእጅ ለእጅ፤ የቅርብ ለቅርብ የሚመስል የክላሽ ድምጽ ነበር። እስከ 1፡30፤ 1፡40 አካባቢ ድረስ የቀጠለ [ነበር]። እየቀጠለ ግን የከባድ መሳሪያ፤ ትልልቅ መሳሪያዎች ድምጽ ይሰሙ ነበር” ብለዋል።

አባይ ማዶ በተባለው አካባቢ ከሦስት ቀናት በፊት ጀምሮ የተኩስ ልውውጦች እንደነበሩ የተናገሩት ሌላ ነዋሪ፤ አየር ጤና በተባለው ሰፈር “ሌሊቱን ሙሉ” በሁለቱ ወገኖች መሃል ውጊያ እንደነበር ተናግረዋል።

በመኖሪያ ሰፈሮች አካባቢ ተደርጓል የተባለው የዛሬው ውጊያ ለአንድ ሰዓት ያህል ተጋግሎ መደረጉንና ማለዳ 3፡00 ሰዓት አካባቢ መብረዱን ነዋሪዎች ገልጸዋል። ረፋድ አካባቢም አልፎ አልፎ የተኩስ ድምጾች ይሰሙ ነበር ብለዋል።

ትናንት ሐሙስ ምሽት ላይ ‘ውጊያ ሊኖር ይችላል ተጠንቀቁ’ የሚል መረጃ እንደሰሙ የተናገሩት አንድ የመንግሥት ሰራተኛ ጥዋት 12፡00 ሰዓት አካባቢ የተኩስ ድምጽ መስማታቸውን ተናግረዋል።

የተኩስ ልውውጡ በተደረገበት አንደኛው ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑም፤ የተኩስ ልውውጡ በ“ከባድ መሳሪያ” የታገዘ ነበር ብለዋል።

ውጊያ የመኖሪያ ሰፈሮች አካባቢ ላይ ቢደረግም እስካሁን ሰላማዊ ሠዎች ላይ ጉዳት ይድረስ አይድረስ ለማወቅ እንዳልቻሉ የተናገሩት ነዋሪዎች፤ በከተማዋ “ምንም አይነት እንቅስቃሴ የለም” ብለዋል።

“ትምህርት ቤት የሚሄዱ ልጆች ነበሩ። ምግባቸውን አዘጋጅተን ነበር [ትምህርት ቤት] ለመላክ። ግን 12፡00 ሰዓት አካባቢ ተኩሱ ሲጀመር ልጆቹን መላክ ስላልቻልን አስቀረናቸው። እኛም ስራ አልሄድንም” ሲሉ አሁናዊ የከተማዋን ሁኔታውን ገልጸዋል።

የፋኖ ታጣቂዎች ሳይሆኑ አይቀሩም ያሏቸው “ታጣቂዎች” በሰፈራቸው ከተማዋን ለቀው መውጣታቸውን መመልከታቸውን ጠቅሰው ውጊያው የረገበው “ለዚህ ይመስላል” ብለዋል።

“ከተማዋ ጸጥ ረጭ ብላለች” ያሉት ሌላ ነዋሪ፤ “ምን እንደተፈጠረ ማወቅ አልቻልንም” ሲሉ እንቅስቃሴ እንደሌለ ተናግረዋል።

“ምንም አይነት የትራንስፖርት እንቅስቃሴ የለም። ሱቆች፤ ሆቴሎች ሁሉም ተዘግተዋል። ሰው በመኖሪያ ሰፈሩ አካባቢ በር ላይ ብቻ ነው ቆሞ የሚታየው” ብለዋል።

የልጆች አባት እንደሆኑ የተናገሩ አንድ ነዋሪ ስጋት ውስጥ መሆናቸውን ተናግረው፤ “የንጹኃን እልቂት” ይደርሳል የሚል ፍርሃት እንዳላቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ ወደ ባሕር እና ከባሕር ዳር አዲስ አበባ የተያዙ በርካታ በረራዎች ለመሰረዝ መገደዱን ቢቢሲ አረጋግጧል።

ለዛሬ አርብ የተያዙ ስድስት የሚደርሱ በረራዎች መሰረዛቸው የታወቀ ሲሆን፤ በረራው መቼ ሊጀመር እንደሚችል “ማወቅ አይቻልም” ተብሏል።

ዛሬ ረፋድ ላይ መግለጫ ያወጣው የአማራ ክልል መንግሥት በባሕር ዳሩ ዙሪያ “ሰርጎ ገቦችን” መዋጋቱን ገልጾ፤ በውጊያ የበላይነትን መቀናጀቱን ጠቁሟል።

በአሁኑ ሰዓት ሙሉ በሙሉ የባህር ዳር ከተማ እና አካባቢው “ጽንፈኛ” ሲል ከጠራው ቡድን እንደጸዳና በተጨማሪም የፋኖ አባላትን እያሰሰ መሆኑንም አስታውቋል።

“የሸሹ እና እየተደበቁ ያለትን ጽንፈኛ ሀይሎች በያሉበት እያሰሰ ከተደበቁበት ጉሬ እያወጣ የክልላችን ሰላም ሙሉ በሙሉ ወደነበረበት ለመመለስ” እየሰራ ነው ብሏል።

መንግሥት በመግለጫው “ሕግ ማስከበር” ላለው እርምጃ ማሕበረሰቡን ከጎኔ በመቆም ‘ለሰላም ዘብ ልትሆኑ ይገባል” ብሏል።

በባሕር ዳር ከተማ በመንግሥትና በፋኖ ኃይሎች መካከል ውጊያ ሲደረግ የዛሬው የመጀመሪያ አይደለም።

በክልሉ ጦርነቱ በተቀሰቀሰበት የመጀመሪያ ወራት በተፋላሚዎች መካከል ውጊያ መደረጉን ተከትሎ የመንግሥት ኃይሎች ሰላማዊ ሠዎችን መግደላቸውን አምነስቲ ኢንተርናሽናል በምርመራው ማረጋገጡን ከሰሞኑን ይፋ አድርጓል።

ይህኑ ግድያ በማስታወስ አንድ የከተማዋ ነዋሪ “ባለፈውም እንደሆነው ንጹኃን ያልቃሉ ብለን ያሳስበናል፤ የሚያሳስበን ነገር እሱ ነው” ሲል ተናግረዋል።

“. . . [የመንግሥት ኃይሎች] ‘እናንተ [የፋኖ] መደበቂያ ናችሁ፤ እናንተ ናችሁ እንደዚህ እንዲሆን የምታደርጉት’ ስለሚሉ ሠው ይፈራል። ለዚህ ይመስለኛል ሁሉም ነገር ጸጥ ያለው” በማለት ግድያ ይፈጸማል የሚል ስጋት እንዳለ ጠቁመዋል።

ሌላ ነዋሪም “የመንግሥት ኃይሎች “ፋኖን ትደግፋላችሁ” በሚል ሌላ አካባቢ እርምጃ ስለወሰዱ እኛ ላይም ይከሰታል የሚል ስጋት ሕዝቡ ላይ አለ” ሲሉ አስጊ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ካለፈው ሳምንት መገባደጃ ጀምሮ በአማራ ክልል በመንግሥት ኃይሎችና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ውጊያ ማገርሸቱ ታውቋል።

በተለይም በጎጃምና በሸዋ አካባቢዎች “ከባድ ውጊያዎች” እተደረጉ መሆኑን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ ከደብረ ብርሃን ወደ ደሴ የሚወስደው መንገድ ከቅዳሜ፣ የካቲት 16/ 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ መዘጋቱን የማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት መወሰኑን ማስታወቁ ይታወሳል።