ከአክሱም እስከ አባይ !


ከወሰንሰገድ መርሻ ደምሴ

( ጮራ ዘ አራዳ) 

(ደራሲ፣ጋዜጠኛና ማህብራዊ ሃያሲ)

ኢትዮጵያን በተለያየ ጊዜ ሊቀራምቷት የሚፈልጉ  በርካታ የባዕዳን ኃይሎች አንድነቷንና ነፃነቷን ለመግፈፍ ያደረጉት ወረራ በጀግኖች አባቶቻችን ተጋድሎ አልተሳካለቸውም። 

 ቀደምት አባቶቻችንና እናቶቻችን ይቺን አገር ለዚህ ትውልድ ያስረከቡን እንደ ዶሮ ብልቶቿ ሳትከፋፈልና ሳትቆራረጥ ነበር።እኛ ግን አደራችንን መወጣት እንኳን ያልቻልን ራስ ወዳድ የሆንን ከርሳሞች  ነን።

  ከአገር አንድነትና ነፃነት ክብር ይልቅ ለከርሳችንና ለቆርቆሮ አሊያም  ለተንጣለል ቤት የምናስብ፤ሌሎች ወገኖቻችን እየተራቡና እየታረዙ ፥እኛ ግን የራሳችንን ከርስና ፍላጎት ለማሟለት የምንሯሯጥ  ትውልድ  ነን።ሌላው ቀርቶ ልብስ ሳይቀይር ያስተማረንን ድሀ ገበሬና በጡረታ ላይ ያሉ ወላጆቻችንን ከመርዳት ይልቅ  በሰላም ወጥቶ በሰላም  እንዳይገባ  በጥይትና በድሮን እያደናበርነው  እንገኛለን።ይህ ብቻ አይደለም  ከቤተሰብ ጭምር አልፈን ለሀገራችን ጭምር ሸክሞች  የሆንን ወገኖች  በርካቶች  ነን ።ለዚህ ደግሞ  ተጠያቂዎች  እከሌ  ከእከሌ  ሳይባል ሁላችንም  ኢትዮጵያዊ  የተባልን ነን።

  በኢትዮጵያ ከአክሱም  ስልጣኔ መዳከም  በኋላ   ፥ በአገሪቱ ውስጥ የተከሰተው  የፊውዳል ስርዓት  ፥ ያስከተለው  የርስ በርስ ጦርነት  ፥ ለብዙ  ጊዜ  ይመኟት ለነበሩ የውጭ  ወራሪ ሀይሎች  ፥ አመቺ ሁኔታ ሲፈጥር ታይቷል ።

  የፖርቹጋል መንግስትና በመካከለኛው  ምስራቅ  የበላይ ሆኖ የቆየው  ፥ የኦቶማን ቱርኮች ኃይል የዓለምን የባህር ንግድ በቁጥጥራቸው  ሥር ለማድረግ  ፥ በአስራ ስድስተኛው  መቶ ክፍለ ዘመን እንቅስቃሴ  ባደረጉበት ወቅት  ፥በኢትዮጵያ ውስጥ  ጣልቃ ለመግባት የቻሉትም  በዚህ የፊውዳሎች  የእርስ በርስ መባላትና ጦርነት  ፥ የተፈጠረውን አጋጣሚ  በመጠቀም  እንደነበር ይነገራል። ሌላኛው  ምክንያት ደግሞ  በሃይማኖት ሽፋን የካቶሊክ ኅይማኖትን እናስፋፋለን በሚል ሰበብ  ወደ ኢትዮጵያችን ገብተው ነበር።

  ቱርኮች በኢትዮጵያ ላይ ወረራ የጀመሩት በ1557 ዓ.ም  ምፅዋንና አርጊጎን በመያዝ ነበር።በወቅቱ አፄ ሰርፀ ድንግል ቱርኮችን ለማስወጣት ወደ ቦታው  ዘመቱ። በጦርነት ወቅት ግን  በጊዜው የተሰለፈው የቱርኮች ሠራዊት ከፍተኛ ስለነበር ማስለቀቅ ሳይችሉ ቀሩ።ስለሆነም  ቱርኮች ለጊዜው  ሁለቱን ቦታዎች እንደያዙ ቆዩ።

 ሆኖም  በጊዜው  የነበረው  የቱርኮች የጦር ኃይል እየተዳከመ ሄደ።ቱርክ በኃይል የያዛቸውን  ፥ የምፅዋንና አርጌጎን በወኪልነት  ሁለቱን ከተሞች እንዲጠብቁላቸው  ፥በአካባቢው ለነበሩት የጎሳ ተጠሪዎች ሰጥተው  ቦታውን ለቀው   ወጡ ።

  በአውሮፓ በወቅቱ  ኃያል የነበረችው  ፥ ፖርቹጋልም  የካቶሊክ ኃይማኖትን ሽፋን አድርጋ ወደ ኢትዮጵያ ገባች።በዚህም 

ኢትዮጵያን ለመያዝ ያደረገችው  ጥረት ተሳክቶላት አፄ ሠርፀ ድንግልንና አፄ ሶሱኒዮስን የካቶሊክ  ኃይማኖች አማኞች አድርጋ ጥሩ ግኑኝነት ልትመሰርት ቻለች።አብዛኛው  የኢትዮጵያ ሕዝብ የኦርቶዶክስ ኃይማኖት ተከታዮች በመሆናቸው  ፥ በአፄ ሶሱንዮስ ላይ የሕዝብ  ተቃውሞ ተቀስቅሶ ዙፋኑን በኃይል እንዲለቅ ተደረገ ።ፖርቹጋልም  ያሰበችው  ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት የመያዝ   ሕልሟ

ሳይሳካላት  ቀረ ።

  የቱርክና  የፖርቹጋል ኢምፓየር ኢትዮጵያን ለመያዝ  ያደረጉት ሙከራ  ፥ በዚህ ዓይነት በእንጭጩ  ከተቀጨ  በኋላ  ፥ ሌላዋ አፍሪካዊቷ አገር  ፥ ዛሬም  ድረስ የእኛን ሰላም  የማትፈልገው ግብፅ  ፥ የቀይ ባህርን አዋሳኝ አካባቢና ወደቦች ለመያዝ  ፥ በተለይም  የአባይን ወንዝ  እስከምንጩ   በቁጥጥር ስር ለማድረግ ቆርታ ተነስታ ነበር።

  ግብፅ በሰሜኑ ክፍላችን  የሚገኘውን ሰበር ጉማንና ጉንደትን ከዛም ፀግ አገዘን፣ሠራዬንና ገዳፈለሲን በቁጥጥሯ ሥር በማድረጓ አጼ ዮሐንስ ፬ኛ ጦራቸውን ወደ ሰሜን አዝምተው  ከጦር አዝማቻቸው  ፥ ከራስ አሉላ አባ ነጋ ጋር በመሆን የግብፅን ጦር  ፥ ሁለት ጊዜ ደጋግመው  ድል በማድረግ  ፥ ከአካባቢው  ተጠራርገው  እንዲወጡ ከፊሎችም የአፈር ሲሳይ እንዲሆኑ አደረጓቸው።

  ከግብፅ ወረራ ቀጥሎ  ፥ በኢትዮጵያ ላይ ዓይናቸውን የጣሉት ደግሞ የአውሮፓ ኃይሎች ነበሩ።ከአሥራ ዘጠነኛው  መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ጀምሮ  ፥ ካፒታሊዝም  ከፍተኛ ደረጃ በደረሰበት በዛን ወቅት   ፥ ወደ ውጭ  የሚላኩ  እንዲሁም  ገቢያና ጥሬ ዕቃ ለማግኘት  ፥ የአውሮፓ ኃይሎች አፍሪካውያንና የላቲን አሜሪካ ሕዝቦች  ፥ በቀኝ ግዛትነት ለመያዝ የሚፎካከሩበት ጊዜ ላይ ደረሱ።በዚህም  የተነሳ ጣሊያንና እንግሊዝ ኢትዮጵያን ለመያዝ ከፍተኛ መሯሯጥ  አደረጉ።

 እንግሊዝ  ኢትዮጵያን ለመውረር ሞክራ  በአጼ ዮሐንስ ፬ኛ ክፉኛ የተመታችውን ግብፅን በቅኝ ግዛት ለመያዝ  በቃች። ከዚህም ሌላ ሱዳንንም  ከግብፅ ተረክባ  በቁጥጥሯ ስር  አደረገች።

 እንግሊዞች ፊታቸውን በሰሜን ኢትዮጵያ በማዞር በግብፅ ተይዘው የነበሩትን ቦታዎች  ፥ በተመሳሳይ መንገድ በአስተዳደሯ ስር ለማድረግ ልዩ ልዩ ስልቶችን በመጠቀም ጥረት አድርጋ ሳይሳከለት ቀርቷል። 

  ይህ ብቻ አይደለም   ግብፅ ለኢጣሊያ ምፅዋን በ1885 ዓ.ም እንድትያዝ በቅኝ ግዛት ስር የነበረችው  ፥ ግብፅ እገዛ አደረጋ እንደነበር ነው  ፥ የታሪክ መዛግብት የሚጠቁሙት።

  በሌላ በኩል ግብፅ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ አግራቶች  ፥ ኢትዮጵያን ለመቀራመት  ፥ አሊያም  የሰላም  አየር እንዳንተነፍስ ብዙ ደክመዋል። የሩቁን ትተን የቅርቡን እንኳን ብንመለከት ፥ ለጥቂት አመት ያህል ኢትዮጵያን በስልጣን ይዘው  የነበሩት  ፥ የልጅ  ኢያሱን መንግስት ማንሳት ይበቃል። ልጅ ኢያሱ  መንግስታቸው  የቅኝ ገዢ  ያልሆኑ ሀገሮች ጋር   ፥ አብሮ የመስራት ፍላጎት ስለነበራቸው።ከናዚስም  ሥራዓት ወደ ተላቀቀችው   ወደ ጀርመን  ፊታቸውን በወቅቱ አዙረው  ነበር ።ጀርመናዊያን ካለፈው ስእተታቸው  በመማር ይመስላል።የአካባቢውን ቅኝ ገዥዎች አካሄድን የመሰለ ፖሊሲ  ይዘው  መጓዝን በተለይም አገራቶችን በግዛታዊ ጥቅም ለመያዝ ፍላጎቱ አልነበራትም።በዚህም የተነሳ አገራችን ኢትዮጵያ ጀርመንና የጦር ቃልኪዳኗ ጓደኛዋ  ፥ ቱርክ ጠቃሚ  አጋሮች  መስለው ስለታዩዋት ወዳጅነት መሰረተች።ይሁንና ይህ ጉዳይ በተቃራኒ መልኩ ለተሰለፉትና በተለይም  በኢትዮጵያ ዙሪያ ቅኝ ግዛት ለነበረችው ፈረንሣይ ፣እንግሊዝና ጣሊያን እንቅልፍ የሚነሳ ጉዳይ ነበር።በዚህም  የተነሳ ጥቅማቸው  ስለተነካ  የውስጥ አርበኞችን  ፥ በማስተባበር በእንግሊዝ አስተባባሪነት  ኢያሱን አስነስተው  ፥ የዘውዲቱና የተፈሪ ጣምራ መንግስት እንዲቋቋም አደረጉ።በወቅቱ በኢትዮጵያ ዙሪያ የነበረችው   ሱዳን በእንግሊዝ በቅኝ ሥር ነበረች።በስተሰሜን በኩል ደግሞ ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ስር በአንድ ወቅት የነበረችውን ኤርትራን ቆርሳ ለመውሰድ በቃች።

በስተደቡብ እንግሊዝ ኬንያን ፤በስተደቡብ  ምስራቅ ኢጣሊያ ደቡብን  የሱማሊያን ግዛት ፤በስተምስራቅ  ደግሞ እንግሊዝ ሰሜኑን የሱማሌ ግዛት ፤ፈረንሳይ ደግሞ ጅቡቲን ሸንሽነው  ይዘው  ነበር ።

 ኢትዮጵያን በቅኝ ገዥነት ለመያዝ የፈለጉት ኢጣሊያኖች  ፥ በአድዋ ድል ከተደረጉ በኋላ በውጊያ ሳይሆን ውስጧን በተለያዩ መንገዶች እርስ በእርስ በመከፋፈልና በጦርነት እንድትታመስ አደረጉ።

በዚህም መሠረት በኢትዮጵያ ላይ የኢኮኖሚ  ተፅእኖችን በማድረግ  ያላቸውን ጥቅም እንዲያገኙ አስችሏቸዋል።

   ከአድዋ ድል በኋላ ግን  ፥ የአውሮፓ ሌጋሲዮንና ቆንሲሎች በተከታታይ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲከፍቱ ተደረገ ።የነዚህ አይነተኛ ወኪሎች ተሳትፎ በጦርነት  ፥ የኢትዮጵያ መንግስትን በዲፕሎማቲክ አላዝቦ ዘላቂ ጥቅማቸውን ማረጋገጥ እንዲሁም ለሸቀጣቸው ገበያ ማራገፊያ ማድረግ ዋናው አላማቸው ነበር።

ለነጋዴዎቻቸው ሕጋዊ ድጋፍ በመስጠት  ፥ በፋይናንስ በኩል ትርፍ በማጋበዝ ውጤታማ ለመሆኑ የተሻለ ያሉትን መንገድ መፍጠር አንዱ ዕቅዳቸው ነበር።የንግድና የወዳጅነት ስምምነቶችን  በመዋዋል ከኃይለሥላሴ ዘመነ መንግስት ጀምሮ እስካሁን ድረስ  ፥ የሚፈልጉትን ሲያደርጉም  ቆይተዋል።በተለይም  ይቺው  ደሀዋ ኢትዮጵያች ን ገበያዋን   ፥ ለአውሮፓ ሸቀጦች ገበያ  ፥ በርግዶ በመክፈት  የኢኮኖሚ  ጥገኛ ማድረግ ዋናው  አላማቸው  ስለነበር ከሞላ ጎደል ያሰቡት ተሳክቶላቸዋል ማለት ይቻላል።

  ደረግ ስልጣኑን ከለቀቀ በኋላ ኢትዮጵያን ሲያስተዳድር የነበረው  ፥ ወያኔ ኤርትራን በማስገንጠል በታሪክ ላይ ጥቁር ጥላሸት የጣለ  መንግሥት ነው ።

   እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ግንቦት 13 ቀን 1998 ዓ.ም   የተባበሩት መንግሥታት ጉዳዩን እንዲያጠና የተዋቀረው ኮሚቴ  ፥ ሰፊ ውይይት  አድርጎ  ፥ እንግሊዝ  ከፊሉን ማለትም ምዕራቡን ኤርትራን ከሱዳን ጋር አጣምራ እንድትመራ  ፥ የሚለውን ሀሳብ በመደገፍ ኤርትራ ለሁለት እንድትክፍል የሚል 34 ለ16 በሆነ ድምፅ ውሳኔ አስተላለፈ። ኮሚቴው  ይህን ያስተላለፈውን ውሳኔ  ፥ ለተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ለሊግ ኦፍ ኔሽን አቀረበ።የተባባሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባሄም  ፥ በውሳኔው ሃሳብ  ላይ በተለይም  የኢትዮጵያን በውሳኔው  ላይ ያሰማችውን ቅሬታ  ፥ በማዳመጥ  ተገቢ ውይይት  ካደረገ በኋላ  ፥ የቀድሞ ኢጣሊያ ቅኝ ግዛቶች  ጉዳይ  ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ወሰነ።

ይህንንም ጠቅላላ ጉባሄው  ሲወሰን በአንፃሩ በርማ፣ጓቲማላ፣ደቡብ አፍሪካ፣ፓኪስታን የሚገኙበት የተባበሩት መንግስታት አጣሪ ኮሚሽን እንዲቋቋም  ወስኖ ነበር።ፓኪስታን የኤርትራን መገንጠል ስለምትደግፍ ኢትዮጵያ ደግሞ  ፓኪስታንን   ፥ በአጣሪ ኮሚሽን ውስጥ  መግባቷን ተቃወመች።ይሁንና በጠቅላላው  ጉባሄው  አቤቱታው  ተቀባይነት ሳያገኝ ቀረ።

 የፓኪስታን ዲፕሎማት በዞፍሩላህክን ኒውዮርክ ውስጥ በጎርጎሮሳውያኑ 1949 ዓ/ም የተናገሩት አሲቅኝም አሳዛኝም ነበር በወቅቱብዲፕሎማቱ «ኢትዮጵያ የሃይማኖትና የዘር ጭቆና የሚካሄድባት አገር ስለሆነች፤የሰው  የዘር ልዩነት እንደማይደረግ፤የሰው  ልጅ እኩልነትና መብት ታከብራለች  ተብሎ አይጠበቅም…» በማለት መግለፃቸው  ለኢትዮጵያ ጥሩ አመለካከት ፓኪስታኖች እንደሌላቸው  የሚያሳይ ነበር።

  በወቅቱ የኢትዮጵያ ዲፕሎማት የነበሩት ኤፍሬም  ተወልደመድህን እዛው  ኒውዮርክ ውስጥ በጎርጎሮሳውያኑ 1949 ዓ/ም «በኢትዮጵያ ነፃነትና መብት እንዲከበር፤በነብዩ መሐመድ የተከበረ መሆኑን ፣የፓኪስታን የመልዕክተኞች መሪ ባለማወቃቸው  እናዝናለን…» በማለት በተባበሩት መንግስታት ስብሰባ ላይ አጻፋዊ ምላሽ ሰጡ።

 የአጣሪ ኮሚቴው  ኮሚሽን ከጎርጎሮሳውያኑ የካቲት 14 ቀን እስከ መስከረም 6 ቀን 1949 ዓ.ም በኤርትራ ጠቅላይ ግዛቶች  ፥ በሚገኙ በተለያዩ  አውራጃዎች እየተዘዋወሩ ጥናት ሲያደርግ ቆዩ። በኤርትራና በአካባቢው  አግባብ ካላቸው  ከሚሏቸው  ከእንግሊዝ ፥ከኢጣሊያና ከፈረንሳይ መንግስታት ጋር ጭምር ውይይት አድርገው፤  የጥናቱን ውጤት ለተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ አቀረቡ።

 የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባሄም  ፥ በኤርትራ ጉዳይ ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ  እንግሊዝ በቅኝ ግዛት ከያዘቻቸው ምዕራባዊ ኤርትራ በአስቸኳይ እንድተወጣና ኤርትራ ከናት ሀገሯ ከኢትዮጵያ ጋር ተመልሳ እንድትቀላቀል 

በጎርጎሮሳውያኑ ህዳር 2 ቀን 1950 ዓ.ም 46 በ10 በሆነ ድምፅ ኤርትራ በፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ ጋር እንድትቀላቀል ተወስነ።

  ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ከተቀላቀለች በኋላ ላለፉት 40 አመታት ከኢትዮጵያ ጋር አብራ ስትኖር  ፥ ከቆየች በኋላ ሻዕቢያና ወያኔ ደርግን ከጣሉ በኋላ አንዱ ገንጣይ ሌላው  አስገንጣይ በመሆን ድራማውና ሟቹ አቶ መለስና አቶ ኢሳያስ  ተጫወቱ። 

  ሻዕቢያ ኤርትራን ወያኔ ኢትዮጵያን በመያዝ ድራማዊው ክስተት ቀጠለ።

 ከግብፅ ባልተናነሰ መልኩ የአቶ መለስ አስተዳደር ኤርትራን ከኢትዮጵያ እንድትገነጠል «ነፃነት ወይስ  ባርነት» የሚል ድምፅ እንዲሰጥ በማድረግ ቁልፉን ሚና በመጫወት በጎርጎሮሳውያኑ ህዳር 2 ቀን 1950 ዓ.ም  የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ የወሰነውን ውሳኔ እንደገና እንዲታይና እንዲገለብጥ  ያለ ተቃዋሚ  ተደረገ።

 መቼም  «ከባርነት ነፃነት ይሻለናል!» ብሎ በድምጹ የመረጠ ሕዝብ ።በጢያራ ብቻ ሳይሆን በባህርና በየብስ ከዛም  ፥ አልፎ በእግር ጎረቤት አገሮችን እያቋረጡ  ወደ ስደት አሁን ደግሞ ወደ ኢትዮጵያችን ድረስ እየሄዱ  የፈረንጅና የአፍሪካ ሀገሮች ባሪያ ለመሆን ባልቻሉ ነበር።

ሌላው ቀርቶ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ከ700,000 በላይ ኤርታራውያን ስደተኞች   ፥ ልክ እንደ አገራቸው  ከሌላው  የአገራችን ኅብረተሰብ በተሻለ መልኩ እየኖሩ ይገኛሉ።

  ከስድስት ሚሊዮን ሕዝቧ መካከል ከግማሽ በላይ ሕዝቧ «ከባርነት ነፃነት!» ይሻለናል  ፤ ብሎ የኤርትራውን መንግስት የደገፉት ኤርትራውያን  ስደተኞች  ፥ ከኢትዮጵያ መገንጠልን የሚፈልጉ ከሆነ አሁን የተመኙትን አግኝተዋል ።ለምን አገራቸውን ጥለው በኢትዮጵያና በሌላው አገር ኖሩ? የኢትዮጵያ ሕዝብ የኤርትራውን መሪ በሆታ የተቀበለው እኛና ኤርትራውያን አንድ ነን በማለት  ፥ የሁለቱን አገራት አንድነትና ሰላም ለማይፈልጉ ለዓለም መንግሥታት መልዕክት ጭምር ያስተላለፉበት ነበር ማለት እችላለሁ።

   ወደ አባይ ጉዳይ ልግባ ፤ ኢትዮጵያ ከግብፅና ከሱዳን ጋር በውሃ ሙሊት ዙሪያ  ፥በአፍሪካ ሕብረት አማካይነት ይህን መጣጥፍ እስክ ተጻፈበት ድረስ  ድርድር  ቢያደርጉም  ከስምምነት ላይ ባለመድረሳቸው  ዛሬም እንደ ጥንቱ ፊትና ጀርባ ሆነው  ቀጥለዋል ።

ከታሪክ አንፃር ግብፆችም ሆኑ ሱዳኖች ለኢትዮጵያ የማይተኙ አገሮች ናቸው። ለምሳሌ 

ግብፆች ምፅዋ ከ1825 ዓ/ም እስከ 1885 ዓ/ም ድረስ የግብፅ መንግሥት ይዞት ሆኖ ሲተዳደር ስለነበረ ነው።የአካባቢው ሕዝብ በሙሉ በዘሩ፣በሃይማኖቱን በባሕሉ ከግብፆች የሚመሳሰልና የሚቀራረብ ነው እንጂ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያገናኘው  ነገር የለም» በማለት የግብጽ ንጉሥ  ፋሩክ  ይናገር ነበር።

 በዚህም የተነሳ የግብጽ መንግሥት የፖለቲካ ጨዋታ በቀይ ባሕር አውራጃ የይገባኛል ጥያቄ ብቻ  ሳያቆም ኤርትራን ከኢትዮጵያ ለማስገንጠልና በኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም ውስጥ ቁልፉን ሚና ስትጫወት ቆይታለች።

 በግብፅ ሚሊተሬ አታሼ ቱራቢ አማካይነት በኢትዮጵያ ውስጥ ሰላዮችን በመላክ  በኤርትራና በኦጋዴን እንዲሁም  ከካይሮ የአማርኛ ሬዲዮ በመክፈት ኤርትራ ከኢትዮጵያ ተገንጥላ የዓረብ ሊግ አባል እንድትሆን፤ሶማሊያ ደግሞ  ቶሎ ነፃነቷን ተጎናፅፋ ሱማሊዎችም አሰባስባ የዓረብ ሊግ አባል እንድትሆን 

ከፍተኛ ቅስቀሳ ነበር ሲያደርጉ የቆዩት።

  በ1955 ዓ/ም መጨረሻ አካባቢ በግብፅ የሚመሩት የሙስሊም መንግስታት በሶቪየት  ህብረት እየተረዱ የፕሮፓጋንዳና የሰርጎ ገብ ዘመቻ ያካሂዱ እንደነበር ተጠቁሟል።ከዚህ ሌላ በ1960ዎቹ ዓመታት የአሜሪካ ወታደራዊ እርዳታ መግባት ሶቪየቶች የኢትዮጵያ ጠላት በጦር መሳሪያ ለማጠናከር ምክንያት እንደ ሆነም ተጠቁሟል።

  ግብፃውያ  የኢትዮጵያ ጠላትን በጦር መሳሪያ ለማጠናከር ከፍተኛ ጥረት ያደርጉ ነበር ። በተለይም  ኤርትራን በማስገንጠል ቁልፉን ሚና የተጨወታው  በወቅቱ ከኤርትራ የሄደው  የግብፅ ባንዳ የነበረው ወልደአብ ውልደማርያም  የሚደርስበትን ጥቃት ኢትዮጵያ ውስጥ መቋቋም  ስላልቻለ ሸሽቶ ካይሮ ሄዶ  የደጋው  ህዝብ  ለነፃነቱ እንዲነሳ በሬዲዮ ካይሮ መጠነ ሰፊ ቅስቀሳ ያካሂድ ነበር።ወዲያው የሙስሊም ሊግ ፓርቲ መሪ የነበረው ኢብርሂም ሡልጣንም ወደ ካይሮ ሄዶ ከወልደአብ ውልደማርያም  ጋር ተቀላቀለ።

የግብፅ፤የሶሪያና፤የኢራቅንና የሌሎችንም  የሙስሊም ሀገሮች እርዳታ ማሰባሰብም  ቻሉ።

 የተቃዋሚ  ቢሮዎችን በመክፈት፤የገንዘብ  እርዳታ በመስጠት ፤መሳሪያዎችን በማስታጠቅ የዛሬዎቹ የአባይ ግድብ ተደራዳሪ አፈንጋጮች  ግብፅና ሱዳን በኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም  እንዳይኖር ያልፈነቀሉት ጥረት የለም።

 ግብፅም ሆነ ሱዳን ዘመን የማይሽረው  በየወቅቱና በየሁኔታው የሚያመረቅዝ ቅራኔ በኢትዮጵያ ላይ ያላቸው  አገሮች ናቸው።ሁለቱም አገሮች ለአማፂዎች መሠወሪያቸው ፤ሆስፒታል፤መግቢያ፤መውጪያ፤ማሰልጠኛቸው፤መታወቂያቸው ሰዳን ነች።

 ዛሬ  በእርስ በርስ  ጦርነት የምትታመሰው  ካርቱም  አሊያም ካይሮ ውስጥ  ጽ/ቤት የሌለው  አማጺያን አልነበረም።ሻዕቢያ፣ጀብሀ፣ኢዲዩ፣ሕ.ወ.ሓ.ት፣ኦነግ፣ኢ.ሕ.አ.ፓ ወዘተ.ሁሉም መዝናኛቸው ካርቱምና ካይሮ ነበር።

  ከዚህ አንፃር አሁንም ቢሆን እነዚህ አገሮች ለጥቅማቸው ሲሉ ኢትዮጵያን ከማተራመስ የማይመለሱ አገሮች  መሆናቸውን በግልፅ  ከሱማሌላንድ ጋር  በነበረው ስምምነት ሌላኛውን  ሱማሌ  ወይም የሙቃዲሾ መንግስትን ማበረታትና ሴራ ስትጠነስስ ተመልክተናል።የኤርትራውንም  መሪ ኢሳያስ አፍወርቂን በመጋብዝ ኢትዮጵያ ላይ የተንኮል ድሯን ስታደራብን  እንደ ነበር አይዘነጋም።

በእርግጥ ኢትዮጵያ አሁን ጥሩ የዲፕሎማሲ  ስራ እያካሄደች ነው።በተለይም  ከአረብ አገሮችና ከአሜሪካና ከምዕራባውያን  ሀገሮች  ጋር መልካም  የሆነ ግንኙነት ፈጥራለች።ከዚህ ሌላ ኢትዮጵያ ድርድሩ ተሳካም ወደቧን ለማጠናቀቅ ጫፍ ላይ ደርሳለች። 

  በሌላ በኩል አሜሪካ በኢትዮጵያ  ላይ ለግብፅ አግዛ ጫናዎችን የማድረግ  ሁኔታ አሁን የቆመ ይመስላል።በተለይም በመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ተነስቶ  የዓለምን ትኩረት ከመሳቡ በፊት    ፍልስጢሞችን የሉአላዊነት የሚደርስና ጋዛ የሚባለውን ጠቅልሎ ለእስራኤል የማስገባት ፖሊሲ አሜሪካ አያራመደች ነበር።ይህን ግብፅ ካልደገፈች የሰላም ድርድሩ የእስራኤሎችም እቅድ ስለሚከሽፍ ኢትዮጵያ ላይ ጫና ስታደርግ ብትቆይም እንዳሰበችው አሜሪካ  አልሆነላትም።አሁን ፍልስጤም ወድው ፍርስራሽ ተለውጣለች። በእርግጥ  አሁንም  አሜሪካ 
በፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አማካይነት በጋዛ እስከ ፊታችን ሰኞ ድረስ የተኩስ አቁም እንደሚኖር ተስፋ አደርጋለሁ  በማለት ይፋ አድርገዋል ። 

አስተያየቱን የሰጡት የእስራኤልና የሐማስ ባለስልጣናትን አሳትፏል የተባለው  ቀጥተኛ ያልሆነ ድርድር ላይ መጠነኛ መሻሻል እንዳለ ቢቢሲ በዘገበበት በአሁኑ ወቅት ምን እንደሚፈጠር የታወቀ ነገር የለም።

ይህም እስራኤል በሙሉ ከበባ ውስጥ ባስገባቻት ጋዛ እርዳታ እንዲገና መስከረም 26 የተፈጸመውን የሐማስ ጥቃት ተከትሎ የተወሰዱ ታጋቾችን መልቀቅን ጭምር ያካትታል ተብሏል።

እስራኤል በጉዳዩ ላይ አስተያየት ባትሰጥም የሐማስ ባለስልጣናት ግን ባይደን እንደጠቆሙት ሁለቱ ወገኖች የተኩስ አቁም ስምምነት ለመድረስ ጫፍ ላይ እንዳልደረሱ ጠቁመዋል።

ከግብጽ ጋር ድርድሩን በማካሄድ ላይ የምትገኘው ኳታር ይፋ ሊደረግ የሚችል ምንም አይነት ስምምነት እንደሌለ ተናግራለች።

የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማጅድ አል-አንሷሪ እንዳሉት ዶሃ “የረመዳን ጾም ከመጀመሩ በፊት ጦርነቱ እንዲቆም ታበረታታለች። ሂደቱ ተስፋ ቢኖረውም ብሩህ አይደለም” ብለዋል።

በደቡብ እስራኤል የሐማስ ታጣቂዎች ወደ አንድ ሺህ 200 የሚጠጉ ሰዎችን ከገደሉ በኋላ እስራኤል በጋዛ መጠነ ሰፊና የማያባራ ጥቃት መጀመሯ ይታወሳል።

ጥቃት አድራሾቹ 253 ሰዎችን አግተው የወሰዱ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ የተወሰኑት ተለቀዋል።

በጋዛ እስራኤል እያደረገችው  ባለው የተቀናጀ የአየር፣ የምድር እና የውሃ ላይ ጥቃት ቢያንስ 97 ሺህ 878 ሰዎች ሲገደሉ፤ 70 ሺህ 215 መቁሰላቸውን የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል። በሐማስ አስተዳደር ስር ባለው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር መሰረት ባለፉት 24 ሰዓታት ብቻ 96 ሰዎች መገደላቸውን ገልጿል።ቢቢሲ ሮይተርስ የዜና ወኪልን ጠቅሶ እንደተናገረው ለድርድሩ ቅርብ የሆኑ ስማቸውን ያልገለጸው ምንጭን ጠቅሶ እንደዘገበው ሐማስ በፈረንሣይ የተቀረፀውን ረቂቅ የድርድር ማዕቀፍ በማጥናት ላይ ይገኛል። 

ማዕቀፉ ሁሉም ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ለ40 ቀናት እንዲቋረጡ እና በእስራኤል እስር ቤቶች ውስጥ የሚገኙ ፍልስጤማውያን 1 ለ 10 ስምምነት ከእስራኤላውያን ታጋቾች መለዋወጥን ያካትታል። 

ፕሬዝዳንት ባይደን ሰኞ ዕለት በኒውዮርክ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት “ከጫፍ ደርሰናል። እስካሁን ግን አልተጠናቀቀም። ተስፋዬ እስከሚቀጥለው ሰኞ ድረስ የተኩስ አቁም እናደርጋለን የሚል ነው” ብለዋል።

በኋላም በኤንቢሲ ላይ የቀረቡት ፕሬዚዳንቱ ስምምነቱ ከተደረሰ እስራኤል በረመዳን ጥቃቷን ለማቆም ፈቃደኛ ትሆናለች ብለዋል።

የረመዳን ጾም ከአስር ቀን በኋላ ነው  የሚጀመረው ። 

“ረመዳን እየደረሰ ነው። ታጋቾቹን በሙሉ ለማውጣት እስራኤል ጊዜ ለመስጠት በረመዳንም እንቅስቃሴ እንደማይያደርጉ ስምምነት ተደርሷል” ብለዋል ባይደን።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማቲው ሚለር በበኩላቸው “ንግግሮች ይቀጥላሉ። ከእነዚህ መካከል የአንዳንዶቹ የመጨረሻው ለሐማስ የሚተዉ ይሆናል” ብለዋል ።

ሚለር አክለውም ስለ ድርድሩ ወይም ስለሚሳካበት ጊዜ ተጨማሪ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ ባይሆኑም “በዚህ ሳምንት መጨረሻ ከሆነ እሰየው… ይህንን ስምምነት እንዲደረስ እየሞከርን ነው። የሚሳካም ይመስለናል” ብለዋል።አንድ የሐማስ ባለስልጣን ቀደም ሲል ለቢቢሲ እንደተናገሩት “ሐማስ ቅድሚያ የሚሰጠው እስረኞችን መለዋወጥ ሳይሆን ጦርነቱን ማቆም ነው።”

“ከዚህ ሁሉ የህይወት እና የንብረት ውድመት በኋላ ወደ ሙሉ የተኩስ ማቆም፤ የተፈናቀሉትን መመለስ እና የጋዛን መልሶ ግንባታ የማያመጣ ማንኛውንም ሐሳብ መቀበል ምክንያታዊ አይደለም።”

የእስራኤል ዋና አጋር የሆነችው አሜሪካ ባለፈው ሳምንት የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት በጋዛ አፋጣኝ የተኩስ አቁም እንዲቆም የሚጠይቀውን ውሳኔ በመቃወሟ ከፍተኛ ትችት አስተናግዳለች።

“በተቻለ ፍጥነት” ጊዜያዊ የተኩስ አቁም እንዲደረስም የራሷን የውሳኔ ሃሳብ አቅርባለች። እስራኤል የደቡብ ጋዛዋ ራፋህ ከተማን “አሁን ባለው ሁኔታ” እንዳትወር አስጠንቅቃለች።

እስራኤል 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚጠጉ ፍልስጤማውያን በተጠለሉባት ራፋህ ላይ ጥቃት እንዳትሰነዝር ከፍተኛ የሆነ ዓለም አቀፍ ጫና ገጥሟታል። አብዛኞቹ በግዛቱ ያሉ ሰዎች በስተሰሜን ያለውን ጦርነት ሸሽተው የተጠለሉ ናቸው።

ባይደን በቃለ ምልልሱ ወቅት “በጣም ብዙ ንፁሀን ሰዎች እየተገደሉ ነው። እስራኤል በራፋህ የምታደርሰው ጥቃት ቀንሷል። ራፋህን ከሐማስ ነጻ ከማድረጋቸው በፊት አብዛኛውን ነዋሪ ለማውጣት ለእኔ ቃል ገብተውልኛል” ብለዋል። ያም ሆነ ይህ  በዚህ ምክንያት ባይደን በግብፅ ላይ ያላቸው አመኔታ  እያጡ ይመስላል።

 ዓለም ባንክ ዓለም አቀፋዊ ድርጅት ነው።ባንክ ውስጥ የተለያዩ ዋና ዋና የአክሲዮኖች ባለቤቶች አሉበት። አብዛኞቹ በጉሩፕ 20 (G 20 )አባላት አገራቶች   አሉበት።ትልቁ የአክሲዮን ባለቤት ግን የተባበሩት አሜሪካ ነው።ይህ የሚያሳየው የአሜሪካ መንግሥት ፥ በገሀድ የግብፆችን ደጋፊ ሆኖ እንደ ቆመና በዚህ የግድቡ የውኃ አሞላል ላይ የቴክኒክ ድርድሮች ፥ ውይይቶች በእሱ ብቻ ሳይሆን የሊግ አስፈፃሚ ውይይቶችና ኢትዮጵያ በምታነሳቸው ነጥቦች ላይ የግብፆችን አቋም እንደያዙና ያላቸውን የፋይናንስ አቅም በመጠቀም ፥ ኢትዮጵያን ለመጫን  እየሞከሩ እንዳለ ነው የሚያሳየው።»

ኢትዮጵያ ፣ግብፅና ሱዳን  በታላቁ እዳሴ ግድብ ግንባታ ዙሪያ ከሚያደርጉት ንግግር አሜሪካ እንዲሁም የዓለም ባንክ መውጣት አለባቸው በሚል በአገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሲጠይቁ እንደነበር ይታወሳል።

 ዶክተሩ ደረሰ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ስእተት እንደተሰራና ጥፋት እንደፈጸሙ ይገልጻሉ « አዎ!በኢትዮጵያ በኩል የተደረገ ጥፋት አለ።ጥፋቱም የተደረገው  በጠቅላይ ሚኒስትሩ በዶክተር አብይ አህመድ ዘመን ሳይሆን ፥ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ዘመን ነው።ምንድን ነው የተደረገው ፥  ከዛ በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ዘመን ግብፅ ጋር ያለው ግንኙነት ኢትዮጵያ በኃይል ትገፋ የነበረው ፥  አንደኛ ሁሉንም የተፋሰስ አገሮች ያሰባሰበ የናይል ቤዝ ኢኒሼቲፍ የሚባል ድርጅት ተቋቁሞ ፥ አንዱ ቢሮ ካምፓላ ፥  አንዱ ቢሮ ናይሮቢ ፥  እንዲቋቋም ተደርጎ ፥  በግብፅና ከሱዳን ጋር በሚደረገው ውይይት ፥ አፍሪካ አንድ ቋንቋ  እንዲናገር ፥ ኢትዮጵያ ብቻውን እንዳትናገር ፥ ትልቅ የዲፕሎማሲ ስራ ተሰርቷል።ግብጾች ያንን መቋቋም አቅቷቸዋል።ለረጅም ጊዜ እነሱ እጃቸው ደክሞ ነበር።እንግዲህ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም የመጨረሻዎቹ የስልጣን ወራት ፥ ግብጾች ትልቅ ያገኙት የዲፕሎማሲ ድል ፥ ምንድን ነው ?ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሀገሮች ጋር ትገፋ የነበረውን ዲፕሎማሲ ፥ አውርዳ ቀጥታ ፥  ከሁለቱ አገሮች ጋር ፥  የሦስት ዮሽ ስምምነት አግሪመንት ውስጥ እገባለው ብላ አዲስ ቻናል ከፈተች።በዚያ ምክንያት አሜሪካኖች ማደራደር ጀመሩ ፥  ይህን ድርድር የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ሲመጣ ተቀብሎ ማስኬድ ጀመረ።የተለወጠው ነገር ምንድን ነው።የአሜሪካ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በመካከለኛው ምስራቅ ላይ ተለውጧል።በተለይ የፕሬዝደንቱ አማች የሆነው አቶ ጃረድ ኩሽነር የመካከለኛው ምስራቅ የሰላም አደራዳሪ ሆኖ ፥ ከተሾመ በኋላ ፍልስጢሞችን የሉአላዊነት የሚደርስና ጋዛ የሚባለውን ጠቅልሎ ለእስራኤል የማስገባት ፥ ፖሊሲ አሜሪካ ማራመድ ስለጀመረች።ለእሱ ደግሞ የመካከለኛው ምስራቅ  ሴንቴር ኦፍ ግራቪቲ ዋናዋ አገር የሆነችው ግብፅ  ለመደገፍ  ተቻለ።እናም የፕሬዝዳንት አቡድልፈታ አልሲሲ መንግስት ግብፅ ይህን ካልደገፈች  ያ የሰላም ድርድር የእስራኤሎችም እቅድ ይከሽፋል።ስለዚህ አሜሪካኖቹ በእነዚህ አይነት ምክንያቶች ግብጾችን ለማስደሰት ኢትዮጵያን  የሚደግፉት ፈረንጆቹ በባቡር ሀዲድ አጋጥሞ ለመጉዳት እያደረገ ነው ያሉት።ይህ ደግሞ  ፖለቲካ ነው» በማለት አስተያየታቸውን በመስጠት አጠናቀዋል።በእርግጥ አሁን አሜሪካ ከግብፅ ይልቅ ከኢትዮጵያ ጋር የጠበቀ ቁርኝነት ፈጥራለች።ምክንያቱ ደግሞ  በምስራቅ አፍሪካ ያለው የእርስ በርስ ጦርነትና የጠፋውን ሰላም ለማምጣት ኢትዮጵያ ተመራጭ አድርገው ነው የሚመለከቷት።አሁን ዶክተር ዐብይም ለምክር ቤታቸው ሲናገሩ ከአሜሪካ ጋር ያለን ግንኙነት በተጠናከረ ሁኔታ ይቀጥላል ሲሉ መናገራቸው ከአሜሪካ ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዳላቸው ያሳያል።ግድቡም  ዘንድሮ ይጠነቀቃል።ኢትዮጵያ ወደ ፊት መሄዷን ቀጥላለች ከውጭ ሀገራቶች  ይልቅ የእርስ በእርሱ ጢርነት ፤ዘረኝነት የተናወጥቸው ግለሰቦች ምንም ውስጥ የሌሉ መነኮሳት፣መምህራን፣ገበሬ ወዘተ. የመሳሰሉትን አሳዛኝ በሆነ ሁኔታ በግፍ መግደልና ከቀያቸው እንዲሁም ከአካባቢያቸው ማፈናቀልና እንዲሰደዱ ማድረግ ሌላኛው የሀገሪቱ የሰላም እጦት የእድገታችን ማነቆና እንቅፋት ሆኖ ቀጥሏል። ግን እስከ መቼ ወገኖቼ ? ይህ የሁላችንም ኢትዮጵያዊያን መልስ ያላገኘ ጥያቄ ነው።አበቃው  !ክብረት ይስጥልኝ