ፑቲን ለኪም ሩሲያ ሰራሽ መኪና በስጦታ አበረከቱ


የመኪና ስጦታው የሩሲያ እና ሰሜን ኮሪያ መሪዎች ያላቸውን “ልዩ ግለሰባዊ ወዳጅነት” ያረጋገጠ ነው ብለዋል የኪም እህት ኪም ዮ ጆንግ።

ሩሲያ የመንግስታቱ ድርጅት ለፒዮንግያንግ ምንም አይነት የትራንስፖርት ተሽከርካሪ እንዳይቀርብ ያሳለፈውን ውሳኔ መደገፏ ይታወሳል

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን የመኪና ስጦታ አበረከቱ።

የኪም እህት ኪም ዮ ጆንግም የፑቲን የመኪና ስጦታ ደርሷቸዋል ነው የተባለው።

ሩሲያ ሰራሽ ናቸው የተባሉት ተሽከርካሪዎች ምን አይነት ሞዴል እንዳላቸው ባይገለጽም ኪምና እህታቸው ለግል እንቅስቃሴያቸው እንዲጠቀሙባቸው የተበረከቱ መሆናቸውን የሰሜን ኮሪያው ኬሲኤንኤ ዘግቧል።

“ስጦታው የሰሜን ኮሪያ እና ሩሲያ መሪዎች ያላቸውን የተለየ ግለሰባዊ ወዳጀነት ያመላከተ ነው” ብለዋል ኪም ዮ ጆንግ።

የፑቲን ስጦታ የመንግስታቱ ድርጅት ለፒዮንግያንግ ምንም አይነት የትራንስፖርት ተሽከርካሪ እንዳይቀርብ ያሳለፈውንና ሀገራቸውም የደገፈችውን ውሳኔ የጣሰ ነው ብሏል አሶሼትድ ፕረስ በዘገባው።

የ40 አመቱ የሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ ኡን “መርሰዲስ ማይባች 600”፣ “ሮልስ ሮይስ ፋንተም” እና “ሌክሰስ ኤልኤክስ 570” የተሰኙና ሌሎች ውድ እና ቅንጡ ተሽከርካሪዎች እንዳሏቸው ይነገራል።

በመስከረም ወር 2023 በሩሲያ ጉብኝት ሲያደርጉም ፕሬዝዳንት ፑቲን ከ2018 ጀምሮ የሚጓዙባትን “ኡሩስ” ሊሞዚን እንደወደዷት መግለጻቸውና ፑቲንም ከኋላ ወንበር እንዲቀመጡ ጋብዘዋቸው አብረው ሲጓዙ መታየታቸው ይታወሳል።

ምዕራባውያን ፊታቸውን ያዞሩባቸው ፑቲን እና ኪም በተለይ ሩሲያ በ2022 በዩክሬን ጦርነት ከከፈተች በኋላ ወዳጅነታቸውን ማጠናከራቸው ተገልጿል።

ሞስኮ እና ፒዮንግያንግ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩበትን 75ኛ አመት ባለፈው ጥቅምት ወር ሲያከብሩም ኪም ለፑቲን የአጋርነት ደብዳቤ መላካቸው ይታወሳል።

የሩሲያው ፕሬዝዳንትም በሰሜን ኮሪያ ጉብኝት እንደሚያደርጉ መግለጻቸው አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያን አሳስቧል።

የደቡብ ኮሪያ የስለላ ድርጅት ሰሜን ኮሪያ ለሩሲያ የጦር መሳሪያ ድጋፍ እያደረገች መሆኑንና ፒዮንግያንግ የተሳካ የስለላ ሳተላይት ስታስወነጭፍም ሞስኮ ድጋፍ አድርጋላታለች የሚል መረጃ ማጋራቱ ይታወሳል።