በደብረ ብርሃን ከተማ ተጠልለው የነበሩ ተፈናቃዮች ወደ ኦሮሚያ ክልል መመለስ ጀመሩ


ከኦሮሚያ ክልል ተፈናቅለው በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደብረ ብርሃን ከተማ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ከነበሩ ሰዎች መካከል የተወሰኑት ወደ ምሥራቅ ወለጋ እና ምዕራብ ሸዋ ዞኖች መመለስ ጀመሩ።

ሰኞ የካቲት 11/2016 ዓ.ም. ኦሮሚያ ክልል የደረሱት የመጀመሪያ ዙር ተመላሾች፣ የቀድሞ መኖሪያቸው በሚገኙባቸው ወረዳዎች ውስጥ በተዘጋጁላቸው ጊዜያዊ መጠለያዎች ውስጥ ማረፋቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በደብረ ብርሃን ከተማ ውስጥ የቆዩት ተፈናቃዮዎች ወደ ኦሮሚያ ክልል መመለስ የጀመሩት እሁድ የካቲት 10/2016 ዓ.ም. መሆኑን ሁለት ተመላሾች እና አንድ የተፈናቃዎች አስተባባሪ ለቢቢሲ ተናግረዋል። እሁድ ጠዋት አንድ ሰዓት ገደማ ጉዞ የጀመሩት ተመላሾችን የጫኑ አውቶብሶች ብዛት 14 ገደማ መሆኑን ተመላሾቹ ጠቅሰዋል።

የመጀመሪያው ዙር ተጓዦች በደብረ ብርሃን ከተማ ውስጥ እና በከተማዋ አቅራቢያ ከሚገኙት ቻይና፣ ወይንሸት እና ባቄሎ ከተባሉት መጠለያ ካምፖች የተወጣጡ መሆኑን ቢቢሲ ያነጋገራቸው አምስት ተፈናቃዎች ገልጸዋል።

በቻይና ካምፕ የተፈናቃዮች ተወካይ የሆኑ አንድ ግለሰብ፤ በመጀመሪያው ዙር የተጓጓዙት በምሥራቅ ወለጋ እና ምዕራብ ሸዋ ዞኖች ውስጥ ከሚገኙ ዘጠኝ ወረዳዎች የተፈናቀሉ ነዋሪዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

እንደ ተወካዩ ገለጻ ከሦስቱ ካምፖች ውስጥ በመጀመሪያው ዙር እንዲመለሱ የተመዘገቡት 800 አባውራዎች ሲሆኑ፣ ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ተደርጓል።

ተመላሾቹን ከጫኑት ተሽከርካሪዎች መካከል አብዛኞቹ ወደ ምሥራቅ ወለጋ ዞን መጓዛቸውን የሚገልጹት አቶ ደጉ ተሾመ የተባሉ ተመላሽ፤ ከእነዚህ ውስጥ ብዙዎቹ ተፈናቃዮቹ ሰኞ ዕለት ወደ ቅያቸው መድረሳቸውን አስረድተዋል።

በምሥራቅ ወለጋ ዞን ወደሚገኘው ጎቡ ሰዮ ወረዳ የተመለሱት እኚህ ተፈናቃይ፤ የወረዳው አስተዳደር ሰኞ ሰባት ሰዓት ተኩል ገደማ ወደ አካባቢው ለደረሱት ተመላሾች አቀባበል ማድረጉን ተናግረዋል።

አቶ ደጉ፤ “አንዳንድ ነገሮች እስከሚስተካከሉ ድረስ ወረዳ ላይ ያስቀምጡናል። ከሳምንት በኋላ ወደየቦታችን ነው የምንገባው” ሲሉ ተመላሾቹ ከመፈናቀላቸው በፊት የነበራቸው መሬት ላይ “ትመለሳላችሁ” ተብሎ እንደተነገራቸው አስረድተዋል።

ወደ ጎቡ ሰዮ ወረዳ የተመለሱ ሌላ ተፈናቃይ በበኩላቸው “ለአሁኑ መጋዘን አለ፤ እርሱ ተጠርጎ ነው ለጊዜው እንድንጠለል የተደረገው። ስለ ለወደፊቱ ምንም የተነገረን ነገር የለም” ሲሉ ቀጣይ መዳረሻቸውን በተመለከተ ከወረዳው አመራሮች የሚሰጥን ትዕዛዝ እየተጠባበቁ መሆኑን ገልጸዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ተመላሾች ወደ ቀድሞ መኖሪያቸው የተመለሱት “በፈቃደኝነት” መሆኑን ተናግረዋል።

ወደ ምሥራቅ ወለጋ ጎቡ ሰዮ ወረዳ የተመለሱት ተፈናቃይ እንደሚያስረዱት በአካባቢው ላይ “የፀጥታ ችግር ይኖራል” የሚል ስጋት ቢኖርም፣ ተፈናቃዮቹ የተመለሱት መንግሥት “ኃላፊነቱን እወስዳለሁ” ብሎ ቃል በመግባቱ ነው። “መንግሥት ኃላፊነቱን እወስዳለሁ ስላለ ፈጣሪን እና መንግሥትን አምነን ገብተናል። ዙሪያውን ያለው ስጋት [ግን] አሁንም እንዳለ ነው” ብለዋል።

አቶ ደጉ የተባሉት ተመላሽ በበኩላቸው በአካባቢው ላይ የመከላከያ ሠራዊት ካምፕ በመኖሩ “ስጋት ይኖራል የሚል ጥርጣሬ” እንደሌላቸው ገልጸዋል።

በደብረ ብርሃን ከተማ በሚገኙት ካምፖቹ ውስጥ የሚገኙ ሌሎች ተፈናቃዮች በቀጣይ ዙሮች በሚደረጉ ጉዞዎች ወደ ቅያቸው እንደሚመለሱ እንደተገለጸላቸው በቻይና ካምፕ የተፈናቃዮች ተወካይ የሆኑ ግለሰብ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ተወካዩ እንዳሉት በካምፑ ውስጥ የሚገኙ ተፈናቃዮች ኦሮሚያ ክልል ወደሚገኘው መኖሪያቸው ከመመለሳቸው በፊት የአካባቢው ሰላም እንዲረጋገጥ እና የወደመው መኖሪያቸው እንዲገነባ ይፈልጋሉ።

ተወካዩ፤ “[የተፈናቃዮች] ‘መንግሥት ፀጥታውን ባላረጋጋበት ሁኔታ ሄደን ከአሁን ቀደም የደረሰው አደጋ አሁንም ሊደርስብን ይችላል’ የሚል ስጋት ነበራቸው። ‘ሄደንም [ማረፍ የምንፈልገው] ቤታችን ላይ ነው እንጂ ከመጠለያ ወጥተን ሌላ መጠለያ ላይ ማረፍ አይኖርብንም። በቀጥታ ቤታችን መግባት ነው የምንፈልገው’ ብለው ጥያቄ አንስተዋል” ሲሉ ከመንግሥት ኃላፊዎች ጋር በተደረጉ ውይይቶች ከተፈናቃዮች የተነሱ ጥያቄዎችን ጠቅሰዋል።

ባለፉት ዓመታት በተለያዩ በምዕራብ ኦሮሚያ የተለያዩ ክፍሎች ውስጥ በሚኖሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ ታጣቂዎች በተደጋጋሚ በፈጸሙት ጥቃት በርካቶች መገደላቸውን የመብት ድርጅቶች ሪፖርት ያደረጉ ሲሆን፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ደግሞ ጥቃቱን በመሸሽ ከቀያቸው መፈናቀላቸው ይታወቃል።

ይህንን በሰላማዊ ነዋሪዎች ላይ በተደጋጋሚ ሲፈጸም የቆየውን ጥቃት መንግሥት ሸኔ የሚለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እንደፈጸመው በተደጋጋሚ ቢነገርም፣ ቡድኑ ግን ድርጊቱን አለመፈጸሙን በመግለጽ መንግሥትን ተጠያቂ ሲያደርግ ቆይቷል።

ቤት ንብረታቸውን ትተው የተፈናቀሉት ሰዎች ባለፉት ዓመታት በአዲስ አበባ እና በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች ተጠልለው ቆይተዋል። መንግሥትም ወደ ቀደመ መኖሪያቸው እንደሚመለሱ በተደጋጋሚ ሲገልጽ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሁለት ሳምንት በፊት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ በሰጡበት ጊዜም ይህንኑ ጉዳይ አንስተውት ነበር።

ገዢው ብልጽግና ፓርቲ “ከኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆች ወደ ስፍራቸው መመለስ አለባቸው። በኦሮሚያ መኖር መብታቸው ነው። ይህ መብታቸው መከበር አለበት” ብሎ መወሰኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ ተናግረው ነበር።

“የሁለቱ ክልል አመራሮች የተፈናቀሉበት አካባቢ ድረስ ሄደው፤ የሕዝቡን ዝግጁ መሆን አይተው፤ ቅያቸው መጠበቁን አይተው [ተፈናቃዮቹ] እንዲመለሱ ሥራ ጀምረዋል” ሲሉ የተደረገውን ዝግጅትም ጨምረው ገልጸው ነበር። ይሁንና ተፈናቃዮቹ “ባሉበት እንዲቆዩ እና ለፖለቲካ መሳሪያ እንዲሆኑ ሆስቴጅ ተደርገዋል” ሲሉ በስም ያልጠቀሱትን አካል ሂደቱን በማደናቀፍ ከስሰዋል።

ቢቢሲ፤ ተፈናቃዮችን ወደ ቅያቸው ለመመለስ የተደረገውን ዝግጅት እና ቀጣይ ሂደቶችን በተመለከተ ከአማራ ክልል፣ ከሰሜን ሸዋ ዞን እና ከደብረ ብርሃን ከተማ ኃላፊዎች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።