የተፈረመው ስምምነት ጦርነት ከማወጅ ጋር የሚስተካከል ነው፡ በተመድ የሶማሊያ አምባሳደር


ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችው አወዛጋቢ ስምምነት ጦርነት ከማወጅ ጋር የሚስተካከል ነው ሲሉ በተባባሩት መንግሥታት ድርጅት የሶማሊያ አምባሳደር አስጠነቀቁ።

ሰኞ ምሽት ሶማሊያን በተመለከተ በመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በተካሄደ ስብሰባ ላይ አምባሳደሩ አቡካር ኦስማን ኢትዮጵያ ወታደራዊ ሰፈር ለማቋቋም ስትል የሶማሊያን ግዛት ለመጠቅለል ዕቅድ አላት ሲሉ የመንግሥታቸውን ክስ አሰምተዋል።

በኢትዮጵያ እና በሶማሊላንድ መካከል የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ ይዘት ለሕዝብ ይፋ ባይደረግም፣ ነገር ግን ሶማሊላንድ ለኢትዮጵያ ለንግድ መተላለፊያ የባሕር በር እና የተወሰነውን ደግሞ በኪራይ ለኢትዮጵያ ባሕር ኃይል መቀመጫነት እንደምትሰጥ አሳውቃለች።

በምላሹም ኢትዮጵያ ነጻ አገርነቷን ላወጀችው ሶማሊላንድ የአገርነት እውቅና እንደምትሰጥ ቢነገርም ኢትዮጵያ ይህንን እንደምታደርግ ማረጋገጫ አልሰጠችም።

ከጥቂት ሳምንት በፊት የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ባደረጉት ንግግር ውዝግቡን ለማለዘብ በሚሞክር ሁኔታ፣ አገራቸው ሶማሊያን የመጉዳት ፍላጎት እንደሌላት እና ዕቅዷም አጠቃላይ አካባቢውን የሚጠቅም ነው ብለው ነበር።

በተባበሩት መንግሥታት የሶማሊያ አምባሳደሩ አቡካር ኦስማን ለፀጥታው ምክር ቤት እንደተናገሩት የኢትዮጵያ ድርጊት ጽንፈኛው አልሻባብ እንዲያንሰራራ እና በአፍሪካ ቀንድ የጎሳ ተገንጣይ ቡድኖችን ሊያበረታታ ይችላል።

ጨመረውም ይህ ሁኔታ ተያያዥ ውጤት ስለሚኖረው አካባቢውን በማዳከም ዓለም አቀፍ ንግድን ሊያስተጓጉል እንዲሁም ተጽእኖው በዓለም ዙሪያ ሊሰማ ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

አምባሳደሩ በሶማሊያ የግዛት አንድነት ላይ ኢትዮጵያ የፈጸመችውን ግልጽ ጥሰት ከሁሉ ቀድሞ ሊመለከት አልቻለም ያሉትን አህጉራዊውን ድርጅት የአፍሪካ ኅብረትን ተችተዋል።

በአጠቃላዩ የሶማሊያ ጉዳይ ላይ ውይይት ያካሄደው የፀጥታው ምክር ቤት አባላት በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት እንዳሳሰባቸው እና ሁለቱ አገራት ጉዳዩን በንግግር መፍትሄ እንዲፈልጉለት ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አገራቸው ከሶማሊያ ጋር ግጭት ውስጥ መግባት እንደማትፈልግ በቅርቡ የተናገሩ ቢሆንም፣ አስካሁን ሁለቱ አገራት መቀራረብ እና መነጋገር ስለመጀመራቸው የተባለ ገር የለም።

አንዳንዶች ደግሞ በአገራቱ መካከል የተፈጠረው ውዝግብ ሶማሊያ ከአልቃኢዳ ጋር ግንኙነት ባለው ታጣቂ ቡድን አልሻባብ ላይ ያገኘቸውን የበላይነት ወደ ኋላ እንዳይመልሰው አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ አልሻባብን እየተዋጋ ያለውን የሶማሊያ መንግሥትን በመደገፍ በርካታ ወታደሮቿን በአገሪቱ ውስጥ ካሰማራች ዓመታት ተቆጥረዋል።