በደቡብ ወሎ ዞን የማዕድን ማውጫ ዋሻ የተናደባቸው ሰዎች ከ12 ቀናት በኋላም መፍትሄ አልተገኘላቸውም


ከ12 ቀናት በፊት በአማራ ክልል በደቡብ ወሎ ዞን ደላንታ ወረዳ፤ የኦፓል ማዕድን ለማውጣት ቁፋሮ ላይ እያሉ ዋሻ የተናደባቸው ሰዎች የሚወጡበት መፍትሔ አሁንም ድረስ አለመገኘቱን የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደር እና የከበሩ ማዕድናት አምራቾች ማኅበር ተናገሩ።

የመከላከያ ሠራዊት ትላንት ሰኞ የካቲት 11፤ 2016 ዓ.ም በአካባቢው በመገኘት የዋሻውን የላይኛው ክፍል ለማፍረስ ፈንጂ ቢጠቀምም፤ ሙከራው አለመሳካቱን የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ መኮንን ለቢቢሲ ገልጸዋል። 

በደላንታ ወረዳ "018 አለኋት" ቀበሌ ቆቅ ውኃ በተባለው አካባቢ በሚገኘው ዋሻ ውስጥ የኦፓል ማዕድን በማውጣት ላይ የነበሩት ግለሰቦች ዋሻው የተናደባቸው ጥር 30፤ 2016 ዓ.ም ምሽት ላይ ነበር። 

በዚህ ምሽት ስምንት ሰዎች በዋሻው ውስጥ እንደነበሩ መረጋገጡን ለቢቢሲ የተናገሩት የከበሩ ማዕድናት አምራቾች ማኅበር ሊቀመንበር አቶ ተስፋዬ አጋዥ፤ ሌሎችም ማዕድን አውጪዎች ሊኖሩ ይችላሉ ተብሎ እንደሚገመት አስረድተዋል።

የዋሻው መናድ ከተሰማበት ጊዜ አንስቶ የአካባቢው ነዋሪዎች የተቀበሩትን ሰዎች ለማውጣት ቁፋሮ ሲያካሂዱ የነበረ ሲሆን 80 ሜትር ጥልቀት ያለው አፈር ከተቆፈረ በኋላ ጥረቱ ተቋርጧል። 

አቶ ተስፋዬ እንደሚናገሩት ቁፋሮው እንዲቋረጥ የተደረገው የዋሻው የላይኛው ክፍል ላይ የሚገኘው አፈር ከስር ቁፋሮ የሚያካሂዱት ሰዎች ላይ ተንዶ ተጨማሪ ሰዎች በተመሳሳይ “መውጫ ያጣሉ” የሚል ስጋት በመፈጠሩ ነው።

የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ መኮንን እንደሚናገሩት፤ ሰዎቹን ከዋሻው የማውጣት ጥረቱን አስቸጋሪ ያደረገው ዋነኛው ጉዳይ ዋሻው የሚገኝበት አካበቢ መልካ ምድር ነው።

“[ዋሻው የሚገኘው] ገደል ውስጥ ስለሆነ ሌሎች ማሽነሪዎችን መጠቀም በፍጹም የሚቻልበት ቦታ አይደለም” የሚሉት አቶ አሊ፤ በዚህም ምክንያት የዞኑ አስተዳደር ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በመነጋገር የሠራዊቱ መሀንዲሰዎች ቦታውን እንዲመለከቱት መደረጉን ገልጸዋል። 

የመከላከያ ሠራዊት መሀንዲሶች በአካባቢው ላይ የተሰማሩት የማዕድን አውጪዎች ቤተሰቦች፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ እና የወረዳው አስተዳደር ፈቃድ ከተገኘ በኋላ መሆኑን ጠቅሰዋል። ዋሻው የሚገኝበትን ቦታ የተመለከቱት የመከላከያ መሀንዲሶችም “ፈንጂ እና ድማሚት” በመጠቀም የዋሻው የላይኛው ክፍል ለማፍረስ ሀሳብ ማቅረባቸውን ተናግረዋል። 

ዋና አስተዳዳሪው፤ “የመከላከያ መሀንዲሶች [ያቀረቡት ሀሳብ] የተንጠለጠውን ገደል ለመናድ ‘በፈንጂ እና በድማሚት እንሞክር’ የሚል ነበር። ትናንት ተሞከረ እሱም የሚቻል አልሆነም” ሲሉ ሙከራው አለመሳካቱን ገልጸዋል። 

አቶ አሊ እንደሚያስረዱት ጥቅም ላይ የዋለው ፈንጂ ቢፈነዳም የአካባቢው ነዋሪዎች ቁፋሮ ሲያከናውኑ እንዳይናድባቸው ስጋት የፈጠረውን የዋሻውን ክፍል ማስወገድ ግን አልተቻለም። 

ይህ ሙከራ ከከሸፈ በኋላ እንዲወገድ የሚፈለገውን የዋሻ ክፍል “በታንክ የመምታት” ሀሳብ ከመሀንዲሶቹ በኩል መቅረቡን የከበሩ ማዕድናት አምራቾች ማኅበር ሊቀመንበር አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል። 

“ተስፋ የሚያስቆርጥ አይደለም፤ ያቺ ቦታ ብትመታ ሰዎቹን ቆፍሮ የማውጣት እድል ይኖር ነበር” የሚሉት አቶ ተስፋዬ፤ ይህ ስፍራ ከተናደ በኋላ ነዋሪዎች ቁፋሯቸውን ቀጥለው ማዕድን አውጪዎቹን ማዳን ይችላሉ የሚል እምነታቸውን ገልጸዋል።

ይሁንና “በታንክ መምታት” የሚለው ሀሳብን በተመለከተ እስካሁን ድረስ ውሳኔ ላይ አለመደረሱን ጠቅሰዋል። 

ተመሳሳይ ሀሳብ የሚያነሱት ዋና አስተዳዳሪው አቶ አሊም በበኩላቸው፤ “መፍትሄ መስጠት የሚቻለው ባለሙያዎች አይተውት፤ የተሰነጠቀውን ነገር ሊያወርድ የሚችል ‘ምን አይነት ቴክኖሎጂ እንጠቀም?’ የሚለው እንደገና ተፈትሾ ነው። [በታንክ ቢመታ] የሚል ሀሳብ አለ ግን ‘ሊያወርደው ይችላል ወይ?” የሚለው መረጋገጥ አለበት” ሲሉ የዚህ መፍትሄ አዋጭነት መረጋገጥ እንዳለበት ጠቅሰዋል።

የመከላከያ ሠራዊት አባላት መውጫ ያጡትን የማዕድን ቆፋሪዎች ለማውጣት አሁንም በአካባቢው እንደሚገኙ የሚናገሩት አቶ አሊ፤ “በመንግሥት በኩል ሊወሰድ የሚችል ማንኛውንም አማራጭ ወስዶ ካሉ የልጆቹን ህይወት ለማዳን ወደ ኋላ የሚባል ነገር የለም” ብለዋል። 

በዋሻው ውስጥ መውጫ ካጡ 12 ቀናት ያስቆጠሩት የማዕድን አውጪዎች ያለ ምግብ “እስካሁን መቆየት ይችላሉ?” የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው የከበሩ ማዕድናት አምራቾች ማኅበር ሊቀመንበር አቶ ተስፋዬ፤ አሁንም ተስፋ እንዳላቸውን ተናግረዋል። 

“[ያለ ምግብ] ይኖራሉ። እስከ 15 ቀን ድረስ የመቆየት እድል አላቸው። [ዋሻው] ውስጥ ውሃ ስላለ፤ አፈር በሉ ምንም አሉ ዞሮ ዞሮ የመቆየት እድላቸው አለ” ሲሉ ግለሰቦቹ በህይወት ይገኛሉ የሚል እምነታቸውን ገልጸዋል።