በሶማሌ ክልል ለ265 ሰዎች ሞት ተጠያቂ ናቸው የተባሉ 41 የአልሻባብ አባላት እስከ ዕድሜ ልክ እስር ተፈረደባቸው


በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ውስጥ ለበርካታ ሰዎች ሞት፣ ለአካል ጉዳት እና ለንብረት ውድመት ምክንያት ናቸው የተባሉ የአልሻባብ አባላት ከሁለት ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ እስራት ተፈረደባቸው።

የእስር ቅጣቱ የተላለፈው 265 ሰዎችን ለሞት፣ 323 የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አባላትን እና ሌሎች ንጹሃን ሰዎችን ደግሞ ለጉዳት ዳርገዋል ተብለው የተከሰሱ 41 የአልሻባብ አባላት ላይ ነው።

ከተፈረደባቸው 41 ግለሰቦች መካከል የአልሻባብ “የጦር መሪዎች” እንደሚገኙበት የፌደራል ፖሊስ የካቲት 10/2016 ዓ.ም. በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባሰፈረው መረጃ አስታውቋል።

መቀመጫውን ጎረቤት አገር ሶማሊያ ያደረገው የአልሻባብ አባል ናቸው የተባሉ 41 ግለሰቦች የተከሰሱት፤ በ2014 ዓ.ም. በሶማሌ ክልል አፍዴራ እና ሸበሌ ዞኖች በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች ላይ ጥቃት ፈጽመዋል በሚል ነው።

በጥቃቱም የ265 ዜጎች ሕይወት መጥፋቱን እና 323 ንፁሃንን እና የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት እንዲሁም ሚሊሻዎች ላይ ከከባድ እስከ ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን የዐቃቤ ሕግ ክስ አመልክቷል።

በተጨማሪም ግለሰቦቹ፤ ጥቃት በተፈጸመባቸው ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ ስድስት የሕዝብ ትምህርት ቤቶችን፣ መሠረተ ልማቶችን፣ የግለሰብ ንብረቶችንና ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ 13 ሚሊዮን 550 ሺህ ብር የሚገመቱ ንብረቶችን አውድመዋል ሲል ዐቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሯል።

ዐቃቤ ሕግ፤ ሁለት የጭነት ተሽከርካሪዎች፣ 470 ፍየልና በጎች እንዲሁም 119 ግመሎችን “ዘርፈዋል” ሲልም ተከሳሾቹን ወንጅሏል።

የክስ መዝገቡ እንደሚያስረዳው፤ ግለሰቦቹ ከአልቃኢዳ ጋር ግንኙነት ካለው እና ኢትዮጵያ በሽብር ቡድንነት ከፈረጀችው የሶማሊያው አልሻባብ አባል በመሆን ሥልጠና መውሰድ የጀመሩት ከ2012 ዓ.ም. ጀምሮ ነው። 

በ2014 ዓ.ም. መጨረሻም “ሕዝብን በማሸበር መንግሥትን ለማስገደድ የተሰጣቸውን ተልኮ ተቀብለው” በሶማሌ ክልል አፍዴር ዞን ባሬይ፣ በጎዲጎድ፣ በቆህሌ፣ በሀርዱር እና በሃርጌሌ ወረዳዎች እንዲሁም በሸበሌ ዞን አዳድሌይ፣ በመስታኒል እና በፊርፊር ወረዳዎች በሚገኙ ቀበሌዎች በተከታታይ ጥቃት መፈጸማቸው በክሱ ተመላክቷል።

ይህ የክስ ዝርዝር የቀረበባቸው 41ዱ ግለሰቦች የተመሠረተባቸውን ክስ መከላከል እንዳልቻሉ የገለጸው የፌደራል ፖሊስ፤ ከሁለት ዓመት እስከ እድሜ ልክ በሚደርስ ጽኑ እስራት መቀጣታቸውን የፌደራል ፖሊስ አስታውቋል።

ተከሳሾቹ 1ኛ የአልሻባብ የጦር መሪ ነው የተባለው ሁሴን አልመድ በቅጽል ስሙ (ሁሴን ጋፕ)፣ 2ኛ የአልሻባብ የቡድን መሪ ነው የተባለው ኢብራሂም ጂብሪል ኢብራሂም እንዲሁም ሆሽ አደም ኢብራሒም፣ ረሃዋ ኢብራሂም እና አሊ በሽርን ጨምሮ አጠቃላይ 41 ተከሳሾች ናቸው።

የፍትሕ ሚኒስቴር የተደራጁ እና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ሕግ በኅዳር 27/2015 ዓ.ም. በዋለው ችሎት የ57 የሰው ምስክሮችን የስም ዝርዝር እና እና 396 ገጽ የሠነድ ማስረጃዎችን አካቶ የሽብር ወንጀል ክስ በተከሳሾቹ ላይ አቅርቧል።

በሁለተኛው ክስ ደግሞ የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ በመተላለፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሽብርተኝነት የተፈረጀው አልሻባብ የሽብር ቡድን ድርጅት መሆኑን እያወቁ አባል በመሆን የወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል።

የአልሻባብ የጦር መሪ ነው የተባለው ሁሴን አልመድ በቅጽል ስሙ (ሁሴን ጋፕ) እና የአልሻባብ የቡድን መሪ ነው የተባለው ኢብራሂም ጂብሪል ኢብራሂም በዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተወስኗል።

ሌሎች 37 ተከሳሾች ደግሞ ከ7 እስከ 12 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ፍርድ ቤቱ ወስኗል። 

በእነ ሆሽ አደም ኢብራሒም መዝገብ በተራ ቁጥር 15 እና 21ኛ የተጠቀሱ ሁለት ተከሳሾችን ግን የቡድኑ አባል በመሆን ብቻ በ2 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሰጥቷል።

በሶማሊያ የሚንቀሳቀሰው አልሻባብ በሚፈጽማቸው የሽብር ጥቃቶች የሚታወቅ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ውስጥም በተለያዩ ጊዜያት ጥቃት ለመፈጸም ያደረገው ሙከራ በአገሪቱ የፀጥታ ኃይሎች መክሸፉ በተደጋጋሚ ተዘግቧል።