መሬት ላራሹ፡ የገጠሪቱን ኢትዮጵያ መልክ የቀየረው የተማሪዎች ንቅናቄ


ከወራት ሁሉ የካቲት የኢትዮጵያን ፖለቲካ መልክዓ ምድር ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ የቀየረ ነው።

የፖለቲካ አመጽ፣ አብዮት፣ ድል የተመዘገበው በየካቲት ወር ነው።

የካቲት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ትናንትን አሽቀንጥሮ ጥሎ፣ ዛሬን ለማቀፍ፣ ነገን ደግሞ በተስፋ ለመጠበቅ የተሰየመ ወር ይመስላል።

የካቲት ሥርዓት ለማስቀጠልም፤ ለመቀየርም በአብነት የቆመ ወር ሆኖ የኢትዮጵያን አብዮት አምጦ አዋልዷል።

በአገሪቱ የነበረው የማኅበራዊ ፍትሕ መጓደል፣ አስተዳደራዊ ምስቅልቅል፣ የኢኮኖሚ እና የመሬት ሥሪቱ ፍርደ ገምድልነት፣ በጣም ጥቂት ሰዎች መሬት ይዘው አብዛኛው የአገሪቱ ገበሬ በጭሰኝነት የሚኖርበት ጊዜ ያበቃ ዘንድ ተቃውሞው የተቀጣጠለው በየካቲት ወር ነው፤ የካቲት 1966 ዓ.ም. ነው።

ከገበሬው አብራክ የወጡ፣ ችግሩን በግንባር ቀደምትነት የተመለከቱ፣ የመሬት ሥሪቱ ፍትሃዊ አይደለም ያሉ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች “መሬት ለአራሹ” የሚል መፈክር ይዘው አደባባይ ወጡ።

የጦፈ የተማሪዎች ንቅናቄ፣ የለውጥ ፍላጎቱም በጣም ከፍተኛ ነበር።

ይህ ንቅናቄ በውጭም በአገር ውስጥም የነበሩ ተማሪዎች የተሳተፉበት እና በመጨረሻም የሁለተኛ ደረጃ እና የሙያ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን ጨምሮ፣ ሕብረተሰቡን ሁሉ ያንቀሳቀሰ ሆነ። 

ይህ አብዛኛው ተማሪ የተሳተፈበት አብዮት የመሬት ለአራሹ ጥያቄ፣ መጨረሻ ላይ የሥርዓቱን መሠረት በማናጋት ወታደሩ ጭምር ያመጸበት ነው።

የመሬት ሥሪት በአፄዎቹ ዘመን

የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ከ1950ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ዕጣ ፈንታ ላይ ወሳኝ ሊባል የሚችል ጫና አሳድሯል።

የኢትዮጵያ ተማሪዎች በፖለቲካ ትግላቸው ካነሷቸው ጥያቄዎች መካከል መሠረታዊ ሊባሉ የሚችሉት የመሬት እና የብሔር ጥያቄዎች ናቸው።

የመሬት ሥሪት ተመራማሪ እና የጥናት ባለሙያ የሆኑት አቶ ደሳለኝ ራህመቶ እንደሚሉት፣ በወቅቱ ተማሪዎች ሲያብላሉት እና ሲወያዩበት የነበረውን አንዱ ጥያቄ “መሬት ላራሹ” የሚል ነበር።

አብዛኞቹ ተማሪዎች የመጡት ከገጠሩ የአገሪቱ ክፍል መሆኑ እና በቅርበት የባላባቱ እና የጭሰኛው ኢፍትሃዊ ግንኙነትን ማወቃቸው አንዱ ምክንያት ሆኗቸዋል።

ለዓመታት የተቃውሞ ድምጻቸውን ሲያሰሙ የነበሩት የወቅቱ የሁለተኛ ደረጃ እና የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በተደጋጋሚ የሚያነሱት እና ሕዝቡንም ለትግል የሚያንቀሳቅሱበት ዓይነተኛ መሣርያ መሬት ላራሹ ነበር።

በሃምሳዎቹ እና በስድሳዎቹ “መሬት ላራሹ” ዋና ሕዝባዊ መፈክር ነበር።

በኢትዮጵያ ከ1966 ዓ.ም. በፊት የሰሜኑ እና የደቡቡ የመሬት ስሪት የተለያየ ነበር።

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል መሬት የሌላቸው ጭሰኞች የነበሩ ቢሆንም፣ አብዛኛው የርስት ባህል ያለበት ነው ይላሉ በዘርፉ ላይ በርካታ ጥናት የሠሩት አቶ ደሳለኝ ራህመቶ።

“ወደ ኋላ ተኪዶ ዘር ወይንም ቤተሰብን በመቁጠር፣ . . . ያንን አካባቢ የያዙት ጥንት የሰፈሩት ሰዎች ልጆች፣ የልጅ ልጆች ናቸው ተብሎ መሬቱ የማን እንደሆነ ይወሰናል። እዚያ የተወለደ ሰው ሁሉ በዚያ አካባቢ ያለውን መሬት የመካፈል መብት ይኖረዋል።”

ከ1966 ዓ.ም. በፊት በነበረችው ኢትዮጵያ የመሬት ሥሪት “በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ በአብዛኛው በመሳፍንት እና በመኳንንቶች የተያዘ ነበር።”

በወቅቱ በነበሩ ተማሪዎች እና ምሁራን ዘንድ በኢትዮጵያ የነበረው የመሬት ሥሪት ብዙ ክርክር የተነሳበት ነው ይላሉ አቶ ደሳለኝ ራህመቶ።

የመሬት ሥሪቱ የፊውዳል መሬት ሥሪት ይመስላል የሚለው ሃሳብ ነበር የክርክሩ ማጠንጠኛ።

ለዚህ ደግሞ አንዱ ምክንያት በሰሜን እና በደቡብ ኢትዮጵያ ያለው የመሬት ስሪት የተለያየ መሆኑ ነበር።

የተማሪዎች ንቅናቄ ‘መሬት ላራሹ’ ብሎ ሲነሳ በብዛት ትኩረቱ ደቡብ ላይ ነበር።

“[ደቡብ ኢትዮጵያ] የጭሰኛ መሬት ያለበት፣ የፊውዳል ሥርዓት የሰፈነበት ቦታ ነው። ያ ማለት የባላባት እና የመሳፍንትን ሥልጣን ገፍፎ ለመውሰድ የመሬት መብቱን ማስለቀቅ ወሳኝ ነው። ለዚህ ነው መሬት ለአራሹ ተብሎ የተወሰነው።”

አብዛኛው የደቡብ ኢትዮጵያ ጭሰኛ ገበሬ፣ ከባለመሬቱ መሬት ወስዶ ካረሰ በኋላ በገባው ስምምነት መሠረት ያመረተውን ያካፍላል።

ገበሬውን ያመረተውን ለባላባቱ ሲያካፍል በተጻፈ ስምምነት አልነበረም።

የመሬት ስሪት ተመራማሪው፣ ገበሬ ለባለመሬቱ እንደ ስምምነታቸው “ሲሶ፣ አንድ አራተኛ አልፎ አልፎ ደግሞ የእኩል ወይንም ግማሽ የሚሰጥ ይሆናል” ይላሉ።

በ1960ዎቹ ውስጥ ይህ በወረቀት ላይ ይስፈር፣ በባላባቱ እና በገበሬው መካከል የተጻፈ ስምምነት ይኑር ተብሎ ተሞክሮ ነበር ይላሉ አቶ ደሳለኝ።

ይህንን ሀሳብ ግን ብዙ ባለመሬቶች አምርረው ተቃወሙት።

“በጽሑፍ ስላልሆነ የባለመሬቱ ሥልጣን የጎላ ነበር። በፈለገው ጊዜ ይህን ያህል ነው የምትከፍለኝ ብሎ ሊወስን ይችላል” ይላሉ የመሬት ስሪቱ ምን ይመስል እንደነበር ሲያብራሩ።

ጭሰኛው የሚከፍለው ክፍያ በምርት ላይ የተመሠረተ መሆኑ ሌላው ነገር ነው። 

አራሹ ገበሬ ለራሱ ምንም ያህል ቢለፋ፣ ታታሪ ቢሆን ለባላባቱ የሚያካፍለው እንዳመረተው መጠን እንጂ “በስምምነት ይህን ያህል ትሰጣለህ ተብሎ የተወሰነ አይደለም። ስለዚህ የባለመሬቱ ከፍተኛ ሥልጣን እና ኃይልን በገበሬው ላይ የሚያሳይ ይሆናል” ይላሉ አቶ ደሳለኝ ራህመቶ።

ለአጼ ኃይለ ሥላሴ የቀረበው የመሬት ጥያቄ

ለአጼ ኃይለ ሥላሴ የመሬት ሥሪት ጉዳይ ችግር እንዳለበት ቀርቦላቸዋል እንደነበር የተለያዩ የታሪክ ምሁራን በጥናቶቻቸው ላይ ጽፈዋል።

አቶ ደሳለኝ ራህመቶ የስዊዲን ተራድኦ ድርጅት አርሲ ጭላሎ አካባቢ በወቅቱ ሰፊ ፕሮግራም ነበረው፤ ድርጅቱ በአካባቢው በሚሠራበት ወቅት አንዱ አንቅፋት ሆኖ ያገኘው የመሬት ሥሪቱ ጉዳይ ነው ይላሉ ተመራማሪው።

“ባላባቶች፣ መሳፍንቶች፣ ብዙ ጊዜ ልማት እንዲንቀሳቀስ አይፈልጉም። ልማት ማለት ጭሰኛውን ገበሬ ማነቃቃት እና [የመሬት ሥሪት] ጥያቄ አንዲያነሳ ማድረግ ማለት በመሆኑ ይህንን አይደግፉትም ነበር።”

በዚህም የተነሳ የአካባቢው ባላባቶች የልማት አንቅስቃሴ እንዳይደረግ “ብዙ እንቅፋት” ይፈጥሩ ነበር።

የስዊዲን ተራድኦ ድርጅትም ይህንን ጉዳይ ለአጼ ኃይለ ሥላሴ ማንሳቱን አቶ ደሳለኝ ራህመቶ ይጠቅሳሉ።

አክለውም ከልማት ተራድኦው ብቻ ሳይሆን “የመሬት ጉዳይ መፍትሔ ማግኘት አለበት” የሚሉ ሌሎች እንቅስቃሴዎች ነበሩ።

ይህንንም የምናውቅበት ምክንያት ይላሉ አቶ ደሳለኝ፣ “መንግሥት ቀስ እያለ አንዳንድ ለውጦች ሲያደርግ መመልከታችን ነው።”

የመሬት ይዞታ እና አስተዳደር ሚኒስቴር በ1960ዎቹ መቋቋም ለዚህ አንዱ ማሳያ መሆኑን በአስረጅነት ያነሳሉ።

ይህ ሊሆን የቻለውም የለጋሽ አገራት ተጽዕኖ እና የመሬት ጉዳይ አንድ እልባት ማግኘት አለበት በሚል ውትወታ መሆኑን ይጠቅሳሉ።

ይህ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤትም በወቅቱ አጠራር በየጠቅላይ ግዛቱ (በየክፍለ ሀገሩ) በመዘዋወር ምን ዓይነት የመሬት ስሪት እንደነበር፣ እርሱም ምን ዓይነት ችግር እንደነበረው ዝርዝር ጥናቶች አካሂዷል።

በዚህም ባለሙያዎቹ በጥናታቸው መሠረት አንዳንድ ለውጦች ለማድረግ የሚያስችል ረቂቅ ሃሳቦች በወቅቱ ለነበረው ፓርላማ እንደራሴዎች እና ለንጉሠ ነገሥቱም አቀረቡ።

በወቅቱ ከቀረቡ ሀሳቦች መካከል አንዱ የጭሰኛ እና የባላባት ስምምነት በጽሑፍ ስምምነት ላይ ይመሥረት የሚል ነበር።

በእርግጥ ይህ ሥር ነቀል አብዮታዊ ለውጥ አልነበረም የሚሉት አቶ ደሳለኝ፣ ነገር ግን ለጭሰኛው ትንሽ ፋታ ይሰጣል፤ ጭሰኛውንም ይከላከላል በሚል ነበር ሲሉ ያብራራሉ።

ሁለተኛው በምክረ ሃሳቡ የተካተተው ጭሰኛው ለባለመሬቱ የሚከፍለው ይወሰን የሚለው ሃሳብ ነበር።

ጭሰኛው ለባላበቱ የሚከፍለው በምርት መጠን ሳይሆን፣ “ቁርጥ ያለ የተወሰነ ክፍያ ይሁን፤ ክፍያው በምርት ሳይሆን በጥሬ ገንዘብ ተብሎ ይወሰን” የሚል ምክረ ሃሳብ ቀርቦ እንደነበር አቶ ደሳለኝ ራህመቶ ያስታውሳሉ።

ይህ ሃሳብ ግን በሕዝብ እንደራሴዎች ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞት ውድቅ ተደረገ።

አቶ ደሳለኝ ይህንን በማንሳት “ምፀት ነው፤ ምናልባትም ይህንን የተለሳለሰ ለውጥን ቢቀበሉ ኖሮ [አጼ ኃይለ ሥላሴ] ምናልባትም የመሬት ሥሪት ለውጥ አይኖርም ነበር ለማለት ይቻላል” ሲሉ ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።

የመሬት ሥሪ ጥያቄ የኢኮኖሚ ወይስ የፖለቲካ? 

በእርግጥ የመሬት ላራሹ በውስጡ የኢኮኖሚ ጥያቄ ቢኖርበትም በዋናነት ግን የፖለቲካ ጥያቄ ነው ይላሉ አቶ ደሳለኝ ራህመቶ።

ተማሪዎች እና ከዚያ በኋላ እንቅስቃሴው ላይ የነበሩ ምሑራን ሲያነሱ የነበረው ዋናው የሥልጣን “የፖለቲካ ኃይል ጥያቄ ነው።”

በወቅቱ የነበረው የፖለቲካ ሥልጣን መሬትን በቁጥጥራቸው ስር በማድረግ ላይ የተመሠረተ ነበር የሚሉት አቶ ደሳለኝ፣ “. . .የመሳፍንቱን እና የመኳንንቱን ሥልጣን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ የሚደመስሰው የመሬት ላራሹ ጥያቄ” በመሆኑ የወቅቱ የተማሪዎች ንቅናቄ ዋነኛ መታገያ ሆኖ አገልግሏል።

ከ1966ቱ አብዮት በኋላም ወደ ሥልጣን የመጣው ወታደራዊ መንግሥት፣ በተማሪዎች ንቅናቄ ጥያቄ መሠረት፣ መሬትን ላራሹ መደልደል ብቻ ሳይሆን፣ “ከመሬት ጋር የተሳሰረ ሥልጣንን የመቁረጥ” ውሳኔን ወስኗል።

“መሬትን ላራሹ መስጠቱ የነበረው የመኳንንት፣ የመሳፍንት፣ የባላባት፣ የመሬት ከበርቴ ሥልጣን እንዳይኖር ሙሉ በሙሉ ሽሮታል።

“. . . ያ ሥልጣን ደግሞ የኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ሥልጣን፣ ፍትህ የማግኘት አቅም ሁሉ ያካተተ ነበር። ያ ሲቋረጥ እና ሲሻር የመጣው ሥር ነቀል ለውጥ የሚሆነው ለዚያ ነው።”

ለአቶ ደሳለኝ ራህመቶ ደርግ ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ያወጣው የመሬት አዋጅ “የሥልጣን ሽግግር ብቻ ሳይሆን የብሔረሰብንም ጥያቄ መፍትሄ ያገኘበት ነው።”

ያን ጊዜ ፖለቲካም ሆነ ኢኮኖሚ ብሔረሰብን ማዕከል አድርጎ የሚሽከረከር ባለመሆኑ፣ ደርግ ይህንን አልተገነዘበውም ይላሉ አቶ ደሳለኝ።

ይኹን እንጂ የብሔረሰብ ጭቆና የነበረበት ዋነኛው የመሬት ስሪቱ ነው ይላሉ አቶ ደሳለኝ።

ደርግ ያንን የመሬት ሥሪት መፍትሄ ማምጣት ማለት “አብዛኛው የተገፉ እና የተጨቆኑ ብሔረሰቦችን የሚመለከት እንደሆነ አልተገነዘበውም።”

በተለያዩ የደቡብ ክልሎች ‘መሬት ላራሹ’ ሲባል ከሌላ አካባቢ መጥተው መሬት የያዙ እና አገሬውን ጭሰኛ ያደረጉትን የሚያፈናቅል ነበር።

በዚህም የተነሳ ጥያቄውም ሆነ ቀጥሎ በደርግ መንግሥት አዋጅ የተሰጠው መልስ እነዚህን ለአካባቢው ‘መጤ’ የሆኑ ባላባቶችን፣ የመሬት ከበርቴዎችን የሚያፈናቅል ነበር።

በእርግጥ ደርግ የሠራውን ስራ ተገንዝቦ ቢሆን ኖሮ “የአብዛኛውን የብሔረሰብ ጥያቄ የሚመልስ ነበር” ይላሉ አቶ ደሳለኝ ራሕመቶ።

“ከሌላ አካባቢ መጥቶ መሬት የያዘውን አካል ወይንም ኃይል በማስለቀቅ ለአካባቢው ተወላጅ መሬቱን መስጠት ማለት፣ ያንን የአካባቢውን ሰው ነጻ ማድረግ ማለት ነው።”

መሬት “የአራሹ ከሆነ” በኋላ የመጣው ምስቅልቅል

ፍቅረሥላሴ ወግደረስ 'እኛ እና አብዮቱ' በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ “ደርግ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ሊያከናውን የፈለገው ታሪካዊ እና ወሳኝ ተግባር፣ የተማረው የሕብረተሰብ ክፍል በተለይም ተራማጅ አስተሳሰብ የነበራቸው ግለሰቦች ሲያራምዱት የነበረውን “መሬት ላራሹ መፈክርን በተግባር መተርጎም” እንደነበረ አስፍረዋል።

ከፍተኛ ትምህርት የሚከታተሉ በተደጋጋሚ የሚያነሱት እና ሕዝቡን ለትግል የሚያንቀሳቅሱበት ዓይነተኛ መሳሪያ መሬት ላራሹ የሚለው ጥያቄ ስለነበረ የደርግ ባለሥልጣናት አስቀድመው “የመሬት ጥያቄ ምላሽ ማግኘት አለበት” የሚል ፍላጎት ነበራቸው ይላሉ ፍቅረስላሴ ወግደረስ።

ይህ ፍላጎትም ደርግ ወደ ሥልጣን በወጣ በጥቂት ወራት፣ በየካቲት ወር 1967 ዓ.ም፣ አዋጅ ታውጆ ተግባራዊ ሆነ።

የ1967 የመሬት አዋጅ የኢትዮጵያን የገጠር ገጽታ ሙሉ በሙሉ የለወጠ መሆኑን አቶ ደሳለኝ ታህማቶ ይጠቅሳሉ።

የመሬት አዋጅ ሲታወጅ ሥር ነቀል የሆነ ለውጥ ይመጣል ብለው ጠብቀው እንደነበር፣ ለጥሩ ውጤትም ተስፋ አድርገው እንደነበርም አይዘነጉም።

በእርግጥ የመሬት አዋጁ ሥር ነቀል ለውጥ አምጥቷል። ይህም የመሬት ከበርቴው ሥርዓት የማይመለስበት ሁኔታ መፍጠሩ ነው።

“በኢትዮጵያ ታሪክ የመሬት ከበርቴ፣ መሳፍንት፣ መኳንንት እና ባላባት የሚባሉ የሶሻል ክላስ ሙሉ በሙሉ ጠፍተዋል። ይህ ነው ትልቁ የአብዮቱ ስኬት።”

ደርግ የመሬት ሥሪትን አዋጅ ካወጀ በኋላ በየቦታው መሬት እንዲከፋፈል ተደረገ።

“በበርካታ አካባቢ ያሉ ገበሬዎች ባለህበት እርጋ ዓይነት ነው። የያዙትን እንደያዙ እንዲቀጥሉ [ነው የሆነው]። ብዙ ቦታ ደግሞ እንዲከፋፈሉ፣ . . .መሬት አልባ የሆኑ ሰዎች ባሉበት መሬት እንዲያገኙ ተለቅ ተለቅ ካሉ ባላባቶች የተወሰደ መሬት ተከፋፈለ” ይላሉ አቶ ደሳለኝ።

ይህ ሥር ነቀል ለውጥ ጭሰኛውን ባለመሬት በማድረግ ለዘመናት የነበረውን ሁኔታ በመቀየሩ “ገበሬው በዚህ ተደስቶ ከልቡ ደርግን እንዲደግፍ አድርጎት ነበር” እንደነበር አቶ ደሳለኝ ይጠቅሳሉ።

የመሬት ላራሹ እንዲሆን መወሰኑ እና የመሬት ክፍፍሉ ባመጣው አዎንታዊ ውጤት የተነሳ፣ በዓመቱ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ዓመታዊ የግብርና ምርት መመዝገብ ችሎ ነበር።

ይህ የገበሬዎቹ ደስታ ግን ብዙ አልቆየም።

ደርግ ከዚህ በኋላ በላይ በላይ የተለያዩ ፖሊሲዎችን፣ አዋጆችን፣ ደንቦችን እና ፕሮግራሞችን ያካሄድ ጀመር።

እነዚህ ፕሮግራሞች ደግሞ ገበሬውን የሚያስጨንቁ፣ የሚያሳስቡ እና እንቅፋት የሚሆኑ ነበሩ።

አዋጆቹ እንደታወጁ ያለ ጥናት እና በቂ ዝግጅት በፍጥነት ወደ ሥራ እንዲገቡ ይደረግ እንደነበርም አቶ ደሳለኝ ያስታውሳሉ።

ደርግ ካወጣቸው አዋጆች መካከል የኅብረት ሥራ ማኅበር እንዲቋቋም ማወጁ አንዱ ነው። በዚህም ሁለት ዓይነት የኅብረት ሥራ ማኅበራት ነበሩ ይላሉ አቶ ደሳለኝ።

አንደኛው የአገልግሎት የሚባል ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ የአምራች የሚባሉት ማኅበራት ናቸው። በተለይ የአምራች የኅብረት ሥራ ማኅበር በገበሬው ላይ ከፍተኛ ጫና የነበረው እና ገበሬውም በጭራሽ የማይወደው እንደነበር።

በዚህ በየአምራቾች የኅብረት ሥራ ማኅበር ምክንያት ገበሬዎች መሬታቸውን አንድ ላይ እያረሱ፣ በመጨረሻ ላይ ምርታቸውን እንዲከፋፈሉ መደረጉን “በእውነት ትልቅ ጥፋት ያጠፋ ፕሮግራም ነበር” ይላሉ አቶ ደሳለኝ። 

ሌላው ከመሬት ሥሪት አዋጅ በኋላ የመጣው እና ገበሬው ተነጣጥሎ ስለሚኖር በመንደር እናሰባስብ በሚል የተጀመረው የመንደር ምሥረታ ፕሮግራም ነው።

የመንደር ምሥረታ አዋጁ የታወጀው ትምህርት ቤት፣ ጤና፣ መብራት፣ ውሃ በቀላሉ ለማቅረብ እንችላለን፤ ልማት በቀላሉ ልናመጣ እንችላለን በሚል ነበር።

ይህም ፕሮግራም በችኮላ ገበሬው ለዘመናት ከኖረበት ስፍራ በማንሳት ወደ መንደር ምሥረታው እንዲገባ አደረገ።

“ይህ ሁለተኛው ገበሬው በጭራሽ ያልተቀበለው ፕሮግራም ነው።”

ደርግ በወቅቱ የነበረውን ከፍተኛ የሆነ ድርቅ እና ረሃብ ለመቋቋም በሚል “አገር አቀፍ የሠፈራ ፕሮግራም ያስፈልጋል ብሎ ሠፈራን አወጀ” ይላሉ አቶ ደሳለኝ።

ምንም ጥናት ሳይኖር፣ ሳያታቀድ፣ ምርምር ሳይኖርበት በተለይ የሰሜኑ ሕዝብ ወደ ደቡብ ሄዶ እንዲሰፍር ተደረገ።

በዚህ የሠፈራ ፕሮግራም ስድስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ፣ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ስፍራ ሺዎችን በማንቀሳቀስ ደርግ “የሠፈራ ፕሮግራም አካሂጃለሁ” አለ።

ይህ የሠፈራ ፕሮግራም ብዙ ምስቅልቅል ማምጣቱን በማስታወስ፣ ከምስቅልቅሎቹ መካከል የገጠሩ ምጣኔ ሃብት እንዲጎዳ ማድረጉ አንዱ ነው።

ምርት ቀነሰ፤ አርሶ አደሩ ብቻ ሳይሆን ከተሜውም የምጣኔ ሃብቱ ቀውስ ተጠቂ ሆነ።

የደርግ ባለሥልጣናት ይህንን እንዴት እናሻሽለው ከሚል ምክክር ይልቅ፣ የሚያባብስ ሌላ ውሳኔ ወሰኑ።

አቶ ደሳለኝ “የሶሻሊስት ኢኮኖሚ ነው የምንመሠርተው፤ ግብርናችንም ሶሻሊስት ነው” በሚል ዘይቤ ሌሎችም ጉዳት ያስከተሉ ውሳኔዎች መተላለፋቸውን ይጠቅሳሉ።

እነዚህ ልዩ ልዩ ፕሮግራሞች በሚካሄዱበት ጊዜ በቂ የሆነ የመሬት ክፍፍል አልተደረገም በማለት ብዙ ቦታ ከመጀመሪያው የመሬት ክፍፍል በኋላ ሁለት እና ሦስት ጊዜ የመሬት ክፍፍል ተደርጓል።

ወታደራዊ መንግሥት በየጊዜው የሚያወጣቸው ፕሮግራሞች ገበሬውን የሚያስጨንቁ፣ የሚያስደነግጡ ችግሩን የሚያባብሱ እንደልቡ እንዳይሠራ እንቅፋት ሆነው ተገኙ።

የበፊቱ ጭሰኛ የአሁኑ የመሬት ባለቤት አርሶ አደር የኢኮኖሚ ሁኔታው ቁልቁል እየሄደ የደኅንነት ስሜቱ እየጠፋ ስጋት እየወረረው ሄደ።

በዚህም የተነሳ ገበሬው ተማረረ፤ ደርግ ላይ ጥርሱን ነከሰ።

የደርግ መንግሥት ከመሬት ጋር ተያይዞ ከወሰዳቸው እርምጃዎች መካከል ውጤታማ የነበረው “አንዱ ብቻ እንጂ ሌላው ፍርስርሱ ነው የወጣው” በማለት “ያቺ አንድ የምላት የመሬት ባለቤትነት ላይ የተመሠረተው ሥልጣን እና ኃይል መደምሰሱ ነው” ይላሉ።

በዚህም የተነሳ “ገጠሪቱ ኢትዮጵያ የገበሬው ‘ሶሳይቲ’ ሆነች. . . አንድ መደብ ብቻ ቀረ ማለት ይቻላል” 

በኢኮኖሚው ረገድ ካየነው የገበሬው ይዞታ በየጊዜው እያነሰ፣ እያነሰ መሄዱን ያነሳሉ።

አቶ ደሳለኝም ሆኑ የወቅቱ የተማሪዎች ንቅናቄ አባላት ተስፋ ያደረጉት ሥር ነቀል ለውጥ፣ ከበጎ ጎኑ በባሰ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ እና የከባቢያዊ ጥፋት ያመጣ ሆነ።

ከ50 ዓመት በኋላም መነጋገርያ የሆነው መሬት

ለአቶ ደሳለኝ የኢትዮጵያ አብዮት 50 ዓመት የኢዮቤልዩ በዓል ሲታሰብም የመሬት ጥያቄ መልኩን ቀይሮ አሁንም አለ።

አሁን ያለው የመሬት ጥያቄ የትውልድ ጥያቄ አለበት ይላሉ አቶ ደሳለኝ።

በዚህ ዘመን መሬት የተያዘው በቤተሰብ ነው። ስለዚህም ጥያቄው ያለው በአባት እና በልጆች መካከል ነው። ጥያቄው እማወራዎች እና አባወራዎች ከልጆቻቸው ጋር ነው።

ልጆች ዕድሜያቸው ከፍ እያለ ሲመጣ የድርሻችንን እንካፈል ሲሉ፣ “ግማሽ ሄክታር የሆነችውን መሬት ለሦስት እና ለአራት ቢከፋፈሉት መሀረብ ነው የምትሆነው” ይላሉ አቶ ደሳለኝ።

አሁን ያለው ትልቅ ጥያቄ የይዞታ ማነስ ነው የሚሉት አቶ ደሳለኝ፣ ይህ ደግሞ በቤተሰብ መካከል ግጭት እንዲቀሰቀስ ምክንያት ይሆናል ሲሉ የወቅቱን የመሬት ጥያቄ ያብራራሉ።

ይህ ደግሞ አንዳንድ ቦታ የይዞታ መሬት ስለሚያንስ በፊት ለግጦሽ ብቻ ይውሉ የነበሩ፣ ዳገታማ እና ተዳፋት ቦታዎች እየተሸነሸኑ ተሰጥተው በመታረሳቸው የአካባቢ ደኅንነት እየተጎዳ ነው።

እንደ አቶ ደሳለኝ የዘመኑ የመሬት ጥያቄ የባለቤትነት ብቻ አይደለም። በተጨማሪም የተበጣጠሰ መሬት የያዘ ገበሬ እንዴት ልማት ሊያመጣ ይችላል የሚልም ነው።

በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ያሉ የመሬት ጥያቄዎች ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ ብዛት በመኖሩ የተነሳ ለመመለስ የማይቻል መሆኑን ያስረዳሉ።

ለዚህም እንደ ማሳያ የሚያነሱት ገጠር ውስጥ ለመኖር አስቸጋሪ መሆኑን እና “የገበሬ ልጆች በሕገወጥ ደላሎች እየተመሩ ከአገር በገፍ መውጣታቸው”ን ነው።

የገጠሪቱ ኢትዮጵያን የሕዝብ ብዛት ለመቀነስ የሥራ ፈጠራ ፕሮግራም ተዘጋጅቶ “ቀስ በቀስ ወጣቱ ሥራ እየያዘ ወደ ከተማ ቢሄድ ትልቅ እርምጃ ነው” የሚሉት አቶ ደሳለኝ፣ ይህ ግን በዓመታት ጠንካራ ሥራ ካልተደገፈ መፍትሄው እውን የመሆን ዕድሉ የጠበበ ነው።

የዚህ ዘመን የመሬት ጥያቄ ውስብስብ በመሆኑ “ቁጭ ብሎ ተወያይቶ መፍትሄ ማስቀመጥ” እንደሚያስፈልግ ይመክራሉ።