የኮምላ ዱሞር ሽልማት፡ ቢቢሲ አፍሪካውያን ጋዜጠኞችን የሚሸልምበት የዘንድሮ ውድድር ተጀመረ


ቢቢሲ በመላው አፍሪካ ተስፋ የተጣለባቸውን ጋዜጠኞችን የሚያበረታታበት እና በዕውቁ ጋዜጠኛ ኮምላ ዱሞር የተሰየመውን ሽልማት የዘጠነኛው ዙር ውድድር የማቅረቢያ ማመልከቻ ተከፍቷል።

ብዙም ያልተነገረላቸው ጉዳዮች የሚያነሱ እና ተሰጥዖ ያላቸው ጋዜጠኞች ዕውቅና የሚያገኙበት ይህንን ውድድር ለማሸነፍ በአፍሪካ ዙሪያ ያሉ ጋዜጠኞች ማመለከት ይችላሉ።

የውድድሩ አሸናፊ ለንደን በሚገኘው የቢቢሲ ዋና መስሪያ ቤት ለሶስት ወራት የክህሎት እና ልምድ የሚገኝበት ዕድል ይመቻችለታል።

የማመልከቻ ጊዜው መጋቢት 6/2016 ዓ.ም የሚጠናቀቅ ይሆናል። 

ይህ ሽልማት በ41 ዓመቱ ድንገት ህይወቱን ያጣውን ጋናዊ ዕውቅ ዜና አቅራቢ ኮምላ ዱሞር ለመዘከር ከአስር ዓመት በፊት የተጀመረ ነው።

የአቅራቢው ሚስት ዊዶው፣ በባለቤቷ በቢቢሲ ውስጥ በነበረው ተጽዕኖ ፈጣሪነት እንደምትኮራ ገልጻ ቢቢሲ በሽልማቱ አማካኝነት ባለቤቷን ሁልጊዜም በማሰቡ እንደምታመሰግን ገልጻለች።

ቢቢሲ በመላው አፍሪካ የሚገኙ ጋዜጠኞች ለዚህ ሽልማት እንዲያመለክቱ የሚያበረታታ ሲሆን በአህጉሪቱ ልዩ ተሰጥኦ እና ችሎታ ያላቸውን ጋዜጠኞች ለሽልማት ይፈልጋል።

አሸናፊው/ዋ በለንደን ከሚኖራቸው ቆይታ በተጨማሪ ወደ ተለያዩ የአፍሪካ ሀገሮች በመጓዝ አስቀድመው ጥናት ያደረጉባቸውን ዘገባዎች እንዲሰሩም ያመቻቻል። ዘገባዎች ለቢቢሲ ዓለም አቀፍ ተከታታዮች የሚሰራጩ ይሆናል።

ይህ ሽልማት በስሙ የተሰየመለት ዱሞር የተለያዩ አፍሪካዊ የዘገባ ርዕሰ ጉዳዮችን በማንሳት የጎላ ተጽዕኖ ማሳደር ችልሏል።

ቢቢሲም በአፍሪካ የሚገኙ ያልተነኩ አፍሪካዊ ጉዳዮችን የሚዘግቡ ጋዜጠኞችን በመሸለም እና ዓለም አቀፍ ታዳሚ እንዲያገኙ በመትጋት የአቅራቢውን ስም ሁሌም እንዲታወስ እየሰራ ይገኛል።

ባለፈው ዓመት የተካሄደውን ውድድር የዕውቁ ጋዜጠኛ ኮምላ ዱሞር የሀገር ልጅ የሆነው ጋናዊው የዜና አቅራቢ ፓ ኩዊስ አሳሬ አሸንፏል።

የዓምናው አሸናፊ ወደ ኬንያ ተጉዞ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚጠቀሙ ‘ቦዳ ቦዳ’ የሚሰኙት ሞተር ሳይክሎችን የተመለከተ ዘገባ ሰርቷል።

የቢቢሲ ዓለም አቀፍ ተቆጣጣሪዋ ሊላኔ ላንዶር “ምስጋና ለኮምላ ሽልማት ይሁን እና ልዩ ተሰጥኦ ያለውን ጋዜጠኛ ስላገኘን ደስ ብሎናል” ብላለች።

በኮምላ ዲሞር አሻራ የአፍሪካን የጋዜጠኝነት ብቃት ማሰሳችንን መቀጠል እንፈልጋለን ስትልም አክላለች።

ዱሞር የቢቢሲ የመጀመሪያው አፍሪካውያን ተመልካቾችን ኢላማ ያደረገው ዕለታዊው የእንግሊዝኛ ፕሮግራም ‘ፎከስ ኦን አፍሪካ’ አቅራቢ ነበር።

በተጨማሪም ቢቢሲ የዓለም አቀፍ ዜና አገልግሎት ውስጥ የአውሮፓ የማለዳ ዜና ከመሪ አንባቢዎች ውስጥ ነበር።

ለአስርት ዓመታት በሀገሩ ጋና ጋዜጠኛ ነበረው እና የዓመቱ ጋዜጠኛ ሽልማት ከወሰደ በኃላ በአውሮፓውያኑ 2007 ቢቢሲን ተቀላቅሏል።

ከ2007 እስከ 2009 ‘ኔትወርክ አፍሪካ’ የተሰኘውን የቢቢሲ ዓለም አቀፍ ፕሮግራም ይመራ የነበረ ሲሆን ቀጥሎም ‘ዘ ወር ልድ ቱዴይ’ የተባለውን ፕሮግራም ተቀላቅሏል።

ቀጥሎም በ2009 የቢቢሲ የቢዝነስ ዘገባ የመጀመሪያዊ አፍሪካዊ አቅራቢ ሆኗል።

በዚህም ስራው በአፍሪካ ውስጥ ቁንጮ ስራ ፈጣሪዎችን አግኝቶ ዘገባ የሰራ ሲሆን በአህጉሪቱ ወቅታዊ የተባሉ የኢኮኖሚ እና ቢዝነስ ጉዳዮችን ቃኝቷል።

በ2013 በ ‘ኒው አፍሪካ’ መጽሄት ከ100 የአፍሪካ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች አንዱ መሆን ችሏል።

የዚህ ሽልማት የቀድሞ አሸናፊዎች

በአውሮፓውያኑ 2023፡ ፓ ካዊሲ አሳሬ ከጋና 

2022፡ ዲንጊንዳባ ጆና ቡዮያ ከዛምቢያ

2020፡ ቪክቶሪያ ሩባዲሪ ከኬንያ

2019 ሶሎሞን ሴርዋንጃ ከኡጋንዳ

2018 ዋሂጋ ማውራ ከኬንያ

2017 አሚና ዩጉዳ ከናይጄሪያ

2016 ዲዲ አኪናየሉሬ ከናይጄሪያ

2015፡ ናንሱ ካቹንጊራ ከኡጋንዳ