የብራዚሉ ፕሬዝዳንት አዲስ አበባ ላይ ያደረጉት ንግግር እስራኤልን አስቆጣ


በአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ስብሰባ ላይ የታደሙት የብራዚሉ ፕሬዝዳንት ሉዊዝ ኢናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ ያደረጉት ንግግር እስራኤልን አስቆጣ።

ፕሬዝዳንቱ በአዲስ አበባው የመሪዎች ጎባኤ ላይ ባደረጉትን ንግግር እስራኤል በጋዛ እያካሄደች ያለውን ዘመቻ በአይሁዳውያን ላይ ከተፈጸመው የጅምላ ፍጅት ጋር በማነጻጸር የዘር ማጥፋት ነው ማለታቸውን እስራኤል አውግዛለች።

ፕሬዝዳንት ሉላ የእስራኤልን ወታደራዊ እርምጃ “በከፍተኛ ደረጃ በተዘጋጀ ሠራዊት እና በሴቶች እንዲሁም በህጻናት” መካከል የሚካሄድ ነው ብለዋል።

ይህንን ንግግር ተከትሎ እስራኤል ፕሬዝዳንቱ በአይሁዳውያን ላይ የተፈጸመውን ጅምላ ፍጅት አቃለዋል በማለት የከሰሰች ሲሆን፣ እየወሰደችው ያለው እርምጃም ሐማስን ለማጥፋት እና በታጣቂው ቡድን የታገቱ ሰዎችን ለማስለቀቅ ነው ብላለች።

በብራዚል ውስጥ የሚገኘው ዋነኛው የአይሁዳውያን ድርጅትም የፕሬዝዳንቱን ንግግር ተችቷል።

በአዲስ አበባው የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ ላይ የታደሙት ሉላ “በጋዛ ሰርጥ በሚገኙ ፍልስጤማውያን ላይ እየሆነ ያለው ሂትለር አይሁዳውያንን ለመግደል ከወሰነበት ሁኔታ በስተቀር በታሪክ የሚስተካከለው የለም።

“ይህ በወታደሮች መካከል የሚካሄድ ጦርነት አይደለም፤ በከፍተኛ ሁኔታ በተዘጋጀ ጦር ሠራዊት እና በሴቶች እንዲሁም በህጻናት መካከል የሚካሄድ ጦርነት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

አንጋፈው የግራ ክንፍ የብራዚል ፖለቲከኛው ሉላ ዳ ሲልቫ ሐማስ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት ፈጽሞ ቢያንስ 1,200 ሰዎችን በመግደል 253 የሚሆኑትን ደግሞ አግቶ የወሰደበትን ድርጊት አውግዘዋል።

ነገር ግን ከዚያ በኋላ በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር ባወጣው መረጃ መሠረት አብዛኞቹ ሴቶች እና ህጻናት የሆኑ ከ28,800 የሚልቁ ሰዎች የተገደሉበትን የእስራኤል የአጸፋ እርምጃ አጥብቀው ሲተቹ ቆይተዋል።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ የፕሬዝዳንት ሉላ ንግግር “በአይሁዳውያን ላይ የተፈጸመውን የጅምላ ፍጅት የሚያቃልል፣ የአይሁድ ሕዝቦችን እና የእስራኤልን ራስን የመከላከል መብት የሚጎዳ ነው” ብለዋል።

“እስራኤልን በናዚ እና በሂትለር ከተፈጸመው የጅምላ ፍጅት ጋር ማነጻጸር ቀይ መስመርን መጣስ ነው” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባወጡት መግለጫ የብራዚሉን ፕሬዝዳንት ወቅሰዋል።

በአውሮፓውያኑ በ1930 እና በ1940 ውስጥ ስድስት ሚሊዮን አይሁድ ሕዝቦች በሂትለር የናዚ መንግሥት በተቀናጀ ሁኔታ በጅምላ ተገድለዋል።

ፕሬዝዳንት ሉላ አዲስ አበባ ላይ ያደረጉትን ንግግር ተከትሎ የተቆጣችው እስራኤል በአገሯ ያሉትን የብራዚል አምባሳደር ለስብሰባ ዛሬ ሰኞ ጠርታለች።

የብራዚል እስራኤላውያን ኮንፌዴሬሽን በበኩሉ የሉላ ንግግር የጅምላ ፍጅት ሰለባዎችን እና የቤተሰቦቻቸውን ትውስታ የሚጎዳ ሆን ተብሎ እውነታን ማዛባት ነው” ብሏል።

ከወራት በፊት ደቡብ አፍሪካ የዘር ማጥፋት በመፈጸም እስራኤልን በዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት ክስ ስታቀርብ ፕሬዝዳንት ሉላ ድጋፋቸውን ገልጸዋል።

የፍርድ ቤቱ ዳኞች የደቡብ አፍሪካ ክስ እንዲታይ ከወሰኑ በኋላ ባስተላለፉት ትዕዛዝ እስራአል በዘር ማጥፋት ድርጊትነት ሊታዩ የሚችሉ ተግባራትን ሠራዊቷ እንዳይፈጽም እንድታደረግ፣ የዘር ማጥፋትን ማነሳሳትን እንድትከላከል እና እድትቀጣ እንዲሁም ሰብአዊ እርዳታ ወደ ጋዛ እንዲደርስ እንድታደርግ ወስኗል።

ነገር ግን ፍርድ ቤቱ እስራኤል በጋዛ ውስጥ የምታካሂደውን ወታደራዊ ዘመቻ በአስቸኳይ እንድታቆም የሚያደርግ ውሳኔ ሳያስተላልፍ ቀርቷል።

ብራዚል እና ደቡብ አፍሪካ ኢትዮጵያ በቅርቡ የተቀላቀለችው እና የባለጸጋ አገራትን ተጽእኖ ለመገዳደር ወሳኝ የሆኑ በመልማት ላይ ያሉ አገራት የሚገኙበት ብሪክስ የተባለው ስበስብ አባል ናቸው።