የታንዛንያው የነጻነት ታጋይ ጁሊየስ ኔሬሬ በአዲስ አበባ ሐውልት ቆመላቸው


የታንዛንያው የነጻነት ታጋይ ጁሊየስ ኔሬሬ በአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ አዲስ አበባ ሐውልት ቆመላቸው።

ጁሊየስ ኔሬሬ ታንዛንያ ወይም በቀድሞ አጠራሯ ታንጋኒካ ከብሪታንያ ቅኝ ግዛት ጭቆና እንድትላቀቅ ከፍተኛ ሚና የነበራቸው ታጋይ ነበሩ።

አገራቸው ነጻነቷን ከተቀዳጀችም በኋላ ኔሬሬ ከአውሮፓውያኑ 1961- 1985 ድረስ መርተዋል።

በስዋሂሊ ቋንቋ ምዋሊሙ (መምህር) በመባል የሚታወቁት ኔሬሬ በፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ ላይ በነበራቸው ቁርጠኝነት ታሪክ ያወሳቸዋል።

በደቡብ አፍሪካ ጨቋኙን የነጮች አገዛዝ፣ ወይም አፓርታይድ በመባል የሚታወቀውን ሥርዓት ይታገሉ ለነበሩ የነጻነት ታጋዮችም በታንዛንያ እንዲጠለሉ አድርገዋል።

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታም ላይ ቁልፍ ሚና ከተጫወቱ መሪዎች አንዱ ናቸው።

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት በርካታ የአፍሪካ መሪዎች በተገኙበት ሥነ ስርዓት ላይ ሐውልቱን የመረቁ ሲሆን ለአህጉሪቷ ባደረጉት አስተዋጽኦም ከፍተኛ ምስጋናን ችረዋቸዋል።

በአውሮፓውያኑ 1963 የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲመሰረት ኔሬሬ “አህጉራችን አንድ ናት። ሁላችንም አፍሪካውያን ነን” በማለት የሰጡትንም አስተያየት ሙሳ ፋኪ በመጥቀስ አስታውሰዋቸዋል።

ኔሬሬ በአውሮፓውያኑ 1961 የቀድሞዋ ታንጋኒካ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሆኑም የመጀመሪያ ሥራቸው ከ120 ብሔር በላይ ያቀፈችውን አዲሲቱን አገር አንድ ማድረግ ነበር።

ስዋሂሊ ብሄራዊ ቋንቋ እንዲሆን እንዲሁም ሶሻሊዝምን በአፍሪካዊ እሳቤም በመቃኘት ኡጃማ (ቤተሰብነት) በሚልም ርዕዮተ ዓለም አገሪቱን ወደ አንድነት አምጥተዋል።

በአውሮፓውያኑ 1964 ታንጋኒካ ከራስ ገዟ ዛንዚባርም ጋር ተጣምራ ታንዛንያ ተመሰረተች።

ቅንጡ ሕይወት የላቸውም የሚባሉት ኔሬሬ በብሪታንያ ዩኒቨርስቲ የተማሩ የመጀመሪያው ታንዛንያዊ ናቸው። 

አገራቸው ከውጭ አገር እርዳታ እንዲሁም ኢንቨስትመንት ተላቃ ራሷን የቻለች እንድትሆንም ብዙ ጥረዋል። 

ሁሉንም አካታች የሆነውን የጤና ሥርዓት በመዘርጋት እንዲሁም የትምህርት ሽፋንን በማስፋት ታንዛንያውያን ይዘክሯቸዋል።

ኔሬሬ በ77 ዓመታቸው በአውሮፓውያኑ 1999 ያለፉ ሲሆን የሞቱባት ዕለትም በታንዛንያ የሕዝብ በዓል ናት።

ኔሬሬ በአፍሪካ ኅብረት ሐውልታቸው የቆመላቸው ሦስተኛው መሪ ናቸው። ከዚህ ቀደም የጋና መስራች እና የነጻነት ታጋዩ ክዋሜ ንክሩማህ እንዲሁም የአፍሪካ አባት ተብለው የሚጠሩት አጼ ኃይለ ስላሴ ሐውልቶች ቆመውላቸዋል።