በጥቁር አንበሳ የሕክምና ትምህርታቸውን ተከታትለው ከተመረቁ ከ120 ዶክተሮች መካከል ዘጠኙ ድቁና ተቀበሉ


ማኅበረ ቅዱሳን አዲስ አበባ ማዕከል ከጽርሐ ጽዮን ሐዋርያት ጎላ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ብርሃን ሰ/ት/ ቤት ጋር በመተባበር ያስተማራቸውን ከ120 በላይ የሕክምና ተማሪዎች (ዶክተሮች) አስመረቀ። 

 

ዘጠኝ ተመራቂዎች ማዕረገ ዲቁና ተቀብለዋል። 

 

በጥቁር አንበሳ የሕክምና ትምህርታቸውን ተከታትለው በመጨረስ በትናንትናው ዕለት በዶክትሬት የተመረቁት ተማሪዎቹ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ጎን ለጎን ሲማሩ ቆይተው በማጠናቀቅ ዛሬ የአገልግሎት ተልዕኮ ተሰጥቷቸዋል። 

በምርቃት መርሐግብሩ የተገኙት የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ መምህር ዋሲሁን በላይ ዘመናዊውንና መንፈሳዊውን ትምህርት ተምራችሁ በሁለት ሰይፍ የተሳላችሁ በመሆናችሁ እንዲህ ያለው ዕውቀት አገራችሁንና ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችሁን በቅንነት ለማገልገል ያግዛል ብለን እናምናለን ብለዋል። 

ማኅበረ ቅዱሳን ዘመኑን የሚመጥን አሠራር ለመከተል ተቋማዊ ለውጥ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አምኖ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል ያሉት ዋና ጸሐፊው ተመራቂዎቹ በማኅበሩ የተለያዩ ማዕከላት በመታቀፍ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት አጠናክረው እንዲያስቀጥሉ የአደራ መልእክት አስተላልፈዋል። 

በዕለቱ ለተመራቂዎቹ የአደራ መስቀል የተሰጠ ሲሆን የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ብርሃናት አእምሮ ምስጋና፣ የሰ/ት/ቤቱ አመራር አባላት፣ የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል።