በኤርትራውያን መካከል ኔዘርላንድስ ውስጥ በተከሰተ ግጭት የፖሊስ መኪኖች ተቃጠሉ


ኔዘርላንድስ ሄግ ከተማ ውስጥ በሚገኙ በሁለት ኤርትራውያን ቡድኖች መካከል ቅዳሜ ምሽት በተከሰተ ግጭት የፖሊስ ተሽከርካሪዎች በእሳት መጋየታቸው ተነገረ።

የኤርትራ መንግሥት ደጋፊ እና ተቃዋሚ በሆኑት ቡድኖች መካከል የተፈጠረውን ግጭት ለመቆጣጠር የኔዘርላንድስ ፖሊስ አስለቃሽ ጋዝ መጠቀሙን እና መኪኖች መቃጠላቸውን የዐይን እማኞች ለቢቢሲ ትግርኛ ገልጸዋል።

ግጭቱ በተካሄደበት ስፍራ በርካታ ሰዎች በጎዳና ላይ የታዩ ሲሆን፣ አንዳንዶችም ድንጋይ ሲወረውሩ እንደነበር እና በእሳት የተያያዙ መኮኖችም በታየታቸውን እማኞች ተናግረዋል።

ቢሆንም ግን በግጭቱ ሰዎች ላይ ጉዳት ስለመድረሱ የታወቀ ነገር የለም።

አሲሺየትን ፕሬስ (ኤፒ) የዜና ወኪል የፖሊስ ቃል አቀባይ ክርስቲያን ቫን ብላንከን በብጥብጡ ምክንያት ስለደረሰ ጉዳትም ሆነ በቁጥጥር ስር ስለዋሉ ሰዎች ጠይቆ ወዲያውኑ መረጃ ማግኘት እንዳልቻለ ዘግቧል።

የሄግ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ቃል አቀባይ ሬቢን ሚድል ግጭቱ የተከሰተው የኤርትራ መንግሥት ደጋፊዎች ስብሰባ እያካሄዱ ሳለ ተቃዋሚዎች ወደ ስብሰባው ስፍራ በመሄድ ጥቃት በመፈጸማቸው ነው።

አክለውም “ሁኔታው አሳሳቢ ሆኖ ከቁጥጥር ውጪ ሆኗል” በማለት በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ኤፒ በዘጋባው ውስጥ ጠቅሷል።

እንዲህ ዓይነቱ ግጭት በኤርትራውያን መካከል አውሮፓ ውስጥ ሲከሰት ይህ የመጀመሪያው አይደለም። 

ከወራት በፊት ጀርመን ጊሰን ከተማ ይካሄድ በነበረ የባህል ፌስቲቫል ላይ በተከሰተ ተመሳሳይ ግጭት ተሽከርካሪዎች ተቃጥለው 26 በፖሊሶች ላይ ጉዳት ደርሷል።

ይህንንም ተከትሎ ከ100 በላይ ኤርትራውያን በፖሊስ ቁጥጥር ውለው በርካቶቹ በተፈጠረው ሁከት ምክንያት ክስ ተመስርቶባቸው ነበር።

በተመሳሳይ ዓመታዊው የኤርትራውያን የባህል ፌስቲቫል ወቅት በጀርመን ስቱትጋርት፣ በስዊዲን፣ በካናዳ እና በእስራኤል በኤርትራ መንግሥት ደጋፊዎች እና በተቃዋሚዎች መካከል ግጭቶች ተከስተው ነበር።

በተለይ እስራኤል ውስጥ በተከሰተው ከባድ ግጭት የአንድ ሰው ሕይወት መጥፋቱን ተከትሎ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ በሁከቱ የተሳተፉ ኤርትራውያንን ለማባረር እና አፍሪካውያን ስደተኞችን ከአገራቸው ለማስወጣት ባለሥልጣኖቻቸው ዕቅድ እንዲያወጡ ማዘዛቸው ይታወሳል።

በኤርትራ የሚካሄደውን አስገዳጅ ብሔራዊ አገልግሎት በመሸሽ በርካታ ኤርትራውያን በአደገኛ ሁኔታ ከአገራቸው በመውጣት ወደ አውሮፓ እና አሜሪካ ተሰደዋል።

በኤርትራውያን መካከል ግጭት የሚፈጠረው የመንግሥት ደጋፊዎች የሚያካሂዱት ዓመታዊ የባህል ፌስቲቫሎች ለመንግሥት ድጋፍ የሚሉ ናቸው በማለት ተቃዋሚዎች ዝግጅቶቹን ለማስቆም በሚያደርጉት ጥረት መካከል ነው።

በኤርትራውያኑ ማኅበረሰቦች መካከል የሚከሰቱትን ግጭቶች ለማስወገድ ሲሉ አንዳንድ ከተሞች የባህል ፌስቲቫሉ እንዳይካሄድ ማገዳቸው ይታወቃል።