የትምህርት ማስረጃዎችን ለማጣራት የሚያስችል መተግበሪያ በቅርቡ ሥራ ይጀምራል ተባለ


  • 51 ሺሕ የመንግሥት ሠራተኞችን የትምህርትማስረጃ ማጣራት መጀመሩ ተገልጿል

የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ያበለፀገው የመንግሥት ሠራተኞችን የትምህርት ማስረጃ ማጣራት የሚያስችል መተግበሪያ በቅርቡ ሥራ እንደሚጀምር ተገለጸ፡፡

ኮሚሽኑ የካቲት 6 ቀን 2016 ዓ.ም. የስድስት ወራት አፈጻጸም ሪፖርቱን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለሰው ሀብት ልማት፣ ሥራ ሥምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ  ባቀረበበት ወቅት እንደተገለጸው፣ የትምህርት ማስረጃ ማጣራት ለመንግሥታት ትልቅ ራስ ምታት ሆኖ ቆይቷል፡፡ ይህንን ችግር ለማስቀረት ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በሲስተም የሚያገናኝ የሶፍትዌር አፕሊኬሽን ማበልፀግ አስፈላጊ ነው ተብሏል፡፡

በኮሚሽኑ ‹‹የተቀናጀ የሲቪል ሰርቪስ የማኔጅመንት የመረጃ ሥርዓት (Integrated Civil Service Management Information System)›› ሶፍትዌሩ እንደሚበለፅግ፣ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ (ዶ/ር) ገልጸዋል።

የትምህርት ማስረጃ ለማጣራት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሰብሳቢነት በተዋቀረ ኮሚቴ አማካይነት የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን፣ የትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን፣ እንዲሁም የትምህርት ሚኒስቴር ተካተው በጥራት ምዕራፎች በመክፈል እየተሠራ መሆኑን መኩሪያ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

በመጀመሪያ ምዕራፍ በፌዴራል ተቋማትና በሚኒስቴሮች የተጠሪ ተቋማት፣ በሁለተኛ ምዕራፍ በሕግ አውጪ፣ ተርጓሚና የዴሞክራሲ ተቋማት፣ በሦስተኛ ምዕራፍ በክልል መንግሥታት፣ በአራተኛ ምዕራፍ በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ሠራተኞች ላይ የትምህርት ማስረጃ ማጣራት እንደሚከናወን ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በ51 ሺሕ የመንግሥት ሠራተኞች ላይ የትምህርት ማስረጃ ማጣራት መጀመሩ ተገልጿል፡፡

ተግባራዊ የሚደረገው ሶፍትዌር ዋና ዋና የሲቪል ሰርቪስ ሥራዎችን በመያዝ ከሌሎች ተቋማት ጋር በመናበብ የሚተገበር በመሆኑ፣ ጥራቱንና ደኅንነቱን የመረጃና መረብ ደኅንነት (ኢንሳ) ሁለት ጊዜ ማጣራት በማድረግ አስተማማኝ መሆኑን ማረጋገጫ መስጠቱን ኮሚሽነሩ ተናግዋል፡፡

የትምህርት ማስረጃዎችን ማጣራት የሚደረገው በግል ዩኒቨርሲቲ የተማሩ ሠራተኞችን ከትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን፣ እንዲሁም ከመንግሥት ዩኒቨርሲቲ የተመረቁትን ከትምህርት ሚኒስቴር በሚገኙ መረጃዎች መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም በወረዳ፣ በዞንና በክልል የሚገኙ የሰው ኃይል መረጃዎችን የማግኘት ክፍተት ለመሙላት በኮሚሽኑ ያሉ መረጃዎችን ወደ ዲጂታል ለመቀየር ጥረት እየተደረገ መሆኑን፣ ኮሚሽነር መኩሪያ (ዶ/ር) ሪፖርቱን ባቀረቡበት ወቅት አስረድተዋል፡፡

በኮሚሽኑ የሚገኙ የብቃት ማረጋገጫ፣ የኢንስፔክሽንና ወቅታዊ መረጃዎችን ወደ ዲጂታል ለመቀየር የዳታ ሴንተር ለመገንባት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ በጀት የሚጠይቅ በመሆኑ፣ ይህንን ወጪ ለማስቀረት የአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዳታ ሴንተርን መጠቀም እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡

የሲቪል ሰርቪስ ዘርፉ ለዜጎች የሚጠበቅበትን ውጤታማ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል የፖሊሲ፣ የመመርያና የሪፎርም ሥራዎች ዝግጅት በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ፖሊሲው ሲቪል ሰርቪሱ ገለልተኛ፣ ብቁና አካታች እንዲሆን ያግዛል ያሉት ኮሚሽነሩ የደመወዝ፣ የጥቅማ ጥቅምና የሥራ ዕድገት በአዲሱ ፖሊሲ በውጤታማነት ላይ ተመርኩዞ ይሰጣል ብለዋል።

የመሥሪያ ቤቶችን አገልግሎት ዘመናዊና ቀልጣፋ ማድረግና የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችንና ሠራተኞችን ብቃት ማረጋገጥ፣ በሪፎርሙ የሚዳሰሱ ጉዳዮች መሆናቸው በሪፖርቱ ተገልጿል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ኮሚሽኑ እያከናወነ ያለው የፖሊሲና የመመርያ ዝግጅት የሚበረታታ መሆኑን ገልጸው፣ በአፋጣኝ ፀድቆ ወደ ሥራ መግባት እንደሚገባው አሳስበዋል።

የመንግሥት ሠራተኞች ገቢ ወቅታዊውን የኑሮ ውድነት ከግምት ውስጥ ማስገባት ይገባዋል ያሉት ሰብሳቢው፣ ሪፎርሙ የሥራ ዕድል ፈጠራን እንዳይጎዳ በጥንቃቄ መተግበር ይገባዋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ከ2.5 ሚሊዮን በላይ የመንግስት ሠራተኞች እንዳሉ ገልጸው፣ የሲቪል ሰርቪስ ፖሊሲ በቅርቡ እንደሚፀድቅ እየተጠበቀ ነው ሲሉ ኮሚሽነር መኩሪያ (ዶ/ር) ተናግረዋል።