ኢትዮጵያ የቤት ሠራተኞችን ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ በመላክ ከፊሊፒንስ መብለጧ ተገለጸ


ኢትዮጵያ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ የቤት ውስጥ ሠራተኞችን በመላክ በደቡብ ምሥራቅ እስያዋ ፊሊፒንስ ተይዞ የነበረውን ደረጃ በመቅደም እየመራች መሆኑን፣ የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል ተናገሩ፡፡

ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ለሥራ የሚሰማሩ ወገኖችን ወደ ሳሁዲ ዓረቢያ በመላክ ቅልጥፍና ከፊሊፒንስ ቀጥሎ ሁለተኛ ኢትዮጵያ እንደነበረች፣ አሁን ግን ፊሊፒንስን በመቅደም ኢትዮጵያ እየመራች መሆኑን ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትሯ ይህንን የተናገሩት የሕዝብ ተካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ ሥራ ሥምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የካቲት 6 ቀን 2016 ዓ.ም.  የሥራና ክህሎት ሚኒስቴርና በሥሩ ያሉ ተጠሪ ተቋማት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት የስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ሲገመግም ነው፡፡

‹‹ይህ ደረጃ የሚነግረን አገሪቱ ያላትን የሥልጠና ጥራትና ልጆቻችን ተመራጭ መሆን መጀመራቸውን ነው፡፡ ይህንን የመደራደሪያ አቅም ይዞ የተሻለ ተጠቃሚነት እንዲኖር የበለጠ አበክረን መሥራት አለብን፡፡ በመሆኑም አሁን የሚታዩት አዎንታዊ አመላካች ጉዳዮች የበለጡ ዕድሎችን አሟጦ ለመጠቀም ምቹ ሁኔታ የፈጠሩ መሆናቸውን አሳይተዋል፤›› ብለዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ በአገር ውስጥና በውጭ አገሮች ሥራ ሥምሪት በአጠቃላይ ለ4.4 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የታቀደ ሲሆን፣ በአገር ውስጥ 3.9 ሚሊዮን፣ በውጭ አገሮች ለ500 ሺሕ ዜጎች ሥራ ለመፍጠር በሚል የተያዘ ዕቅድ ነው፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት የአገር ውስጥ የሥራ ዕድል ፈጠራውም ሆነ የውጭ አገር የሥራ ሥምሪቱ በታቀደው ልክ ባለመሄዱ፣ በስድስት ወራት ማሳካት የተቻለው 1.5 ሚሊዮን የሚጠጋ የሥራ ዕድል ብቻ ነው ተብሏል፡፡ በስድስት ወራት ለማሳካት ተይዞ የነበረው 2.1 ሚሊዮን የሥራ ዕድል ነበር፡፡

በውጭ አገሮች በተደረገ የሥራ ሥምሪት ስምምነት መሠረት የ250 ሺሕ ዜጎች ሰነድ የተገመገመ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል ወደ ሥራ የተሰማሩት 181 ሺሕ መሆናቸውን ሚኒስትሯ አስታውቀዋል፡፡ በአውሮፓና በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች በቀሪ ጊዜያት ኢትዮጵያውያንን ለመላክ ሰፊ ዕድል ስለመኖሩ ተገልጿል፡፡ ኢትዮጵያውያን ለሥራ ሲሄዱ የሚረከቡ በውጭ የሚገኙ 4,500 የሥራ ኤጀንሲዎች መኖራቸው ተጠቅሷል፡፡ ሚኒስትሯ በአገር ውስጥ የሥራ ዕድል በታቀደው መጠን እንዳይፈጸም የሰላምና የፀጥታ ችግሮች፣ ከአደረጃጀት ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ጫናዎች መኖራቸውን አስረድተዋል፡፡

ይሁን እንጂ ከሥራ ፈላጊዎች ጋር በተገናኘ የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ባነሱት ጥያቄ፣ ሚኒስቴሩ ለውጭ አገር ሥራ ሥምሪት ዜጎች እንዲመዘገቡ በማኅበራዊ ሚዲያ አስተዋውቆ ከተመዘገቡ በኋላ፣ ተመዝጋቢዎች ቀጣዩን ሒደት እንደማያውቁና መረጃ በስልክም ሆነ በአካል በመሄድ ቢጠይቁ ማግኘት እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰባሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) በበኩላቸው ከውጭ የሚገባ ምርትን መተካት እንደሚባለው ሁሉ፣ አገሪቱ እያደገች በሄደች ቁጥር ለአገር ግንባታ የሚያስፈልጉና ክህሎችና ዕውቀት ያላቸው ባለሙያዎች አገር ውስጥ ማፍራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ በመሆኑም በበርካታ የዓለም ክፍል ኢትዮጵያን ጨምሮ በብዛት እየሠሩ ያሉት የቻይናና የህንድ ዜጎች ዋነኛ መሥፈርት፣ በብቃት መሥራት መቻላቸውን እንደሆነ ጠቅሰው፣ የኢትዮጵያን የውስጥ ችግር ሊፈቱ የሚችሉ ባለሙያዎችን ማፍራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡