የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ወደ አፍሪካ ኅብረት ስብሰባ “እንዳልገባ ለመከልከል ሙከራ ተደርጓል” ማለታቸውን ኢትዮጵያ አስተባበለች


የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼኽ ሞሐሙድ የኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ወደሚካሄድበት ስፍራ “እንዳልገባ ለመከልከል ሞክረዋል” በማለት ያቀረቡትን ክስ የኢትዮጵያ መንግሥት አስተባበለ።

ዛሬ ቅዳሜ የካቲት 11/2016 ዓ.ም. በተጀመረው የአህጉሪቱ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመገኘት ትናንት አርብ አዲስ አበባ የገቡት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት፣ የፀጥታ ኃይሎች ተፈጸመብኝ ባሉት ክልከላ ኢትዮጵያን የኅብረቱ ጉባኤ “ባለማክበር” ከሰዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ለቀረበበት ክስ በሰጠው ምላሽ፣ ለአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ ለሚመጡ የአገራት እና የመንግሥታት መሪዎች እንደሚደረገው ሁሉ ለሶማሊያው ፕሬዝዳንትም በሙሉ ክብር ደማቅ አቀባበል እንደተደረጋለቸው ጠቅሶ፣ በሶማሊያ ልዑክ በኩል ከተለመደው አሠራር የወጣ ሁኔታ መከሰቱን አመልክቷል።

ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼኽ ሞሐሙድ እንዳሉት የመሪዎች ጉባኤ ወደ ሚካሄድበት ስፍራ እንዳይገቡ በኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች ክልከላ ለማድረግ ቢሞክሩም ኋላ ላይ ግን በስብሰባው ለመሳተፍ መቻላቸውን ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንቱ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት ዛሬ ጠዋት በዝግ በሚካሄደው የኅብረቱ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ካረፉበት ሆቴል ለመውጣት በሞከሩበት ጊዜ “ኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች መንገድ ዘግተው ከሆቴሉ እንዳልወጣ አድርገዋል” በማለት ከሰዋል።

ነገር ግን በሌላ አገር ፕሬዝዳንት መኪና ከሆቴሉ ወጥተው ወደ ስብሰባው ቦታ መድረስ ቢችሉም “ጠመንጃ የታጠቁ ወታደሮች ከፊታችን ሆነው ወደ ኅብረቱ ጊቢ እንዳንገባ አግደውን ነበር” ብለዋል።

እንደ አስተናጋጅ አገር በቆይታቸው ለእንግዶቹ ደኅንነት ኃላፊነት እንዳለበት የገለጸው የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የሶማሊያ ልዑካን በመንግሥት የተመደቡላቸውን የፀጥታ ሠራተኞች አንቀበልም ከማለታቸው በላይ፣ ጠባቂዎቻቸውም የጦር መሳሪያ ታጥቀው ወደ አፍሪካ ኅብረት ለመግባት ሲሞክሩ በኅብረቱ የፀጥታ አካላት መከልከላቸውን ገልጿል።

በዚህም የኢትዮጵያ መንግሥት የፕሬዝዳንቱን እና የልዑካኑን ደኅንነት ከመጠበቅ ባሻገር በስብሰባው ላይ እንዳይገኙ እንዳላደናቀፈ እንዲሁም ወደ ኅብረቱ ቅጥር ጊዜ እንዳይገቡ እንዳልከለከለ አሳውቋል።

ይህንን ክስተት በተመለከተ የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ ባወጣው መግለጫ “የኢትዮጵያ መንግሥት የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ልዑካን ቡድን በአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ ላይ እንዳይሳተፍ ለማደናቀፍ ያደረገውን ሙከራን አጥብቆ እንደሚያወግዝ” ገልጿል።

ድርጊቱ የዲፕሎማሲ እና ዓለም አቀፍ ደንብን የሚጥቀስ ከመሆኑ በላይ፣ የአፍሪካ ኅብረትን የቆየ ባህል የሚቃረን በመሆኑ ኅብረቱ ጉዳዩን በገለልተኛነት እንዲመረምር ጥሪ አቅርቧል።

ኢትዮጵያ እራሷን ነጻ አገር አድርጋ ካወጀችው እና ሶማሊያ የግዛቴ አካል ናት ከምትላት ሶማሊላንድ ጋር ከአንድ ወር በፊት የመግባቢያ ስምምነት ከተፈራረመች ወዲህ በሁለቱ አገራት መካከል ውዝግብ መቀስቀሱ ይታወቃል።

በስምምነቱ ሶማሊላንድ ለኢትዮጵያ 20 ኪሎ ሜትር የሚረዝም የባሕር ጠረፍ ለመስጠት ስትስማማ፣ ኢትዮጵያ ደግሞ በምላሹ ለሶማሊላንድ የአገርነት እውቅና እንደምትሰጥ መጠቀሱ ተገልጿል።

ይህ ስምምነትም የአፍሪካ ኅብረትን ደንብ የሚጥስ እና የሶማሊያን ሉዓላዊነት የሚጻረር ነው በማለት ሶማሊያ ጉዳዩን ለአህጉራዊው እና ዓለም አቀፋዊ የመንግሥታቱ ድርጅት አቅርባ ተቃውሞዋን በተደጋጋሚ ገልጻለች።

ከውዝግቡ መቀስቀስ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አዲስ አበባ የመጡት ፕሬዝዳንት ሐሰን ዛሬ ቅዳሜ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችውን ስምምነት “ትክክለኛነት ለማሳየት ባደረገችው ሙከራ” አገራቸው ደስተኛ አለመሆኗን አመልክተዋል።

ፕሬዝዳንቱ ጨምረውም “ኢትዮጵያ ከሶማሊያ መሬት መውሰድ ትፈልጋለች። ይህንንም ለማመቻቸት በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣናት ሶማሊላንድ ውስጥ ይገኛሉ” በማለት የተደረሰውን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው ኢትዮጵያ ውዝግቡን እያባባሰች ነው ሲሉ ከሰዋል።

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት አሁን አዲስ አበባ ላይ የሰነዘሩትን ክስ በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት የሰጠው ምላሽ ባይኖርም፣ ቀደም ሲል ግን ኢትዮጵያ ግዛት የመጠቅለል ፍላጎት አላት የሚለውን የሶማሊያ ክስ በማስተባበል ውድቅ ማድረጓ ይታወሳል።

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት በአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ ዋነኛ አጀንዳቸው የኢትዮጵያ እና የሶማሊላንድ ስምምነት እንደሚሆን የታወቀ ሲሆን፣ በዛሬው የመክፈቻ ስብሰባ ላይም ይህንኑ አንስተዋል።

ጽህፈት ቤታቸው በኤክስ ገጹ ላይ እንዳመለከተውም፣ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼኽ ሞሐሙድ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የደረሰችውን ስምምነት ማውገዛቸውን እና ስምምነቱ “ሕገመንግሥታዊ ያልሆነ፣ ሕገወጥ እና ተቀባይነት የሌለው” በማለት የሌላ አገርን ግዛት የመጠቅለል እርምጃ ነው ብለውታል።

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር እና ነጻ አገርነቷን ያወጀችው የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሶማሊያን ያስቆጣውን የመግባቢያ ሰነድ የፈረሙት ታኅሣሥ 22/2016 ዓ.ም. አዲስ አበባ ላይ ነበር። ስምምነቱን የተቃወሙት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ድጋፍ ለማግኘት የኤርትራ እና ግብፅን ጨምሮ ወደተለያዩ አገራት መጓዛቸው ይታወሳል።

በዚህም ሳቢያ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ውጥረት የሰፈነ ሲሆን፣ ሁለቱ አገራት ወደ ግጭት እንዳይገቡ እና ለጉዳዩ በንግግር መፍትሔ እንዲፈልጉ የአፍሪካ ኅብረት እና ሌሎችም አገራት ጥሪ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያም በበኩሏ ስምምነቱ ሶማሊያን የሚጎዳ እንዳልሆነ በመግለጽ የተፈረመውን ስምምነት ተግባራዊ እንደምታደርግ ያሳወቀች ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር መንግሥታው ከሶማሊያ ጋር ጦርነት ውስጥ የመግባት ፍላጎት እንደሌለው ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም የተፈጠረውን አለመግባባት ተከትሎ በስም ያልጠቀሷቸው “ኃይሎች” ኢትዮጵያን ከሶማሊያ ጋር ለማጋጨት እየሰሩ ነው ሲሉም ክሰዋል።

በአባይ ወንዝ ላይ ኢትዮጵያ ግንባታውን እያጠናቀቀቸው ባለው በታላቁ ሕዳሴ ግድም ምክንያት ከኢትዮጵያ ጋር ውዝግብ ውስጥ ያለቸው የግብፅ ፕሬዝዳንት በይፋ ስምምነቱን ተቃውመው፣ አገራቸው በአስፈላጊው ሁኔታ ሁሉ ከሶማሊያ ጎን እንደምትቆም መግለጻቸው ይታወሳል።