371 ሺህ 971 የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ለማቋቋም በትኩረት እየተሰራ ነው – አምባሳደር ተሾመ ቶጋ


371 ሺህ 971 የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ለማቋቋም ከባለድርሻ አካላት ጋር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ አስታወቁ፡፡

አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ጋር በመተባበር በተዘጋጀ ውይይት ላይ የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ለማቋቋም እየተሰሩ ባሉ ሥራዎች ላይ ገለጻ አድርገዋል፡፡

በውይይቱ የለጋሽ ሀገራት አምባሳደሮች፣ የኢትዮጵያ ወዳጆች እና ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የገንዘብ ሚኒስትር ዴዔታ ሰመሪታ ሰዋሰው፣ የተመድ የኢትዮጵያ ተወካይና የዩኤንዲፒ የኢትዮጵያ ተጠሪ ተገኝተዋል፡፡

አምባሳደር ተሾመ÷ ከሀገር መከላከያና ከሚመለከታቸው ክልሎች ጋር በተደጋጋሚ በተደረጉ ውይይቶች ከመግባባት የተደረሰባቸውን 371ሺህ 971 የቀድሞ ታጣቂዎች መልሶ የማቋቋም ሥራዎች መጠናቀቃቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡

ሥራዎቹን በአራት ምዕራፍ ለማጠናቀቅ የሚያስችል የፕሮግራም፣ ዝርዝር ፕሮጀክቶችና የሃብት ፍላጎት ሰነዶች እንዲሁም ተያያዥ የቅድመ “ዲሞቢላይዜሽን” ሥራዎች ናቸው ብለዋል፡፡

ከልማት አጋሮች፣ ከኢትዮጵያ ወዳጆች እና ከመንግስት የሚጠበቁ የተግባር ምዕራፍ ጉዳዮችን አንስተውም አምባሳደሩ ማብራራታቸውን የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል።

በምክክር መድረኩ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ በቀጥታ የስልክ መስመር በመድረኩ የተሳተፉ ሲሆን ፥ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ለፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ተፈፃሚነት በፅናት መቆሙን ገልጸዋል፡፡

ብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን በሚያወጣው ፕሮግራም እና የአፈፃፀም ቅደም ተከተሎች መሰረት የክልሉ ተዋጊዎች መልሰው ተቋቁመው ወደ ህብረተሰቡ በመቀላቀል ሰላማዊ ህይወት እንዲመሩ በቁርጠኝነት እንደሚሰራም ነው ያረጋገጡት፡፡

የለጋሽ ሀገራት አምባሳደሮችና የተቋማት ከፍተኛ አመራሮች በኮሚሽኑ የእስከአሁን የቅድመ “ዲሞቢላይዜሽን” የዝግጅት ምዕራፍ የተሳካ አፈፃፀምና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ለፕሮግራሙ ስኬት ያለውን ከፍተኛ ተነሳሽነት ከግንዛቤ በማስገባት ሰፊ ምክክር አድርገዋል።

በመጨረሻም ሁሉም የምክክር መድረኩ ተሳታፊ ወገኖች የኮሚሽኑ ተልዕኮ በተቀመጠው የአፈፃፀም ምዕራፍና ቅደም ተከተል እንዲፈፀም የበኩላቸውን ድርሻ በተግባር ለመወጣት ቁርጠኛ መሆናቸውን ነው ያረጋገጡት፡፡