ሲጋራ በእንጀራ ውስጥ በመክተት ተጠርጣሪ ለመጠየቅ ወደ ፖሊስ መምሪያ ይዞ የሄደው ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ


 

ግለሰቡ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 አንበሳ ጋራዥ ጀርባ ወደ ሚገኘው የክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ የሄደው በወንጀል ተጠርጥሮ የታሰረ ሰው ለመጠየቅ ነበር።

ስንቅ ለማቀበል በሚመስል መልኩ በያዘው ሳህን ውስጥ ወደ ተጠርጣሪ ማቆያ ቤት ሲጋራ ለማስገባት ሲሞክር በፖሊስ አባላት በቁጥጥር ስር ውሏል።

በፖሊስ መምሪያው የተጠርጣሪ ማረፊያ ቤት አካባቢ የፍተሻ እና የማረጋገጥ ስራ የሚሰሩ የፖሊስ አባላት በወቅቱ ግለሰቡ ምግብ አስመስሎ የያዘውን ሳህን እንዲከፍት አድርገው ሲመለከቱ 20 ፓኬት ሲጋራ ከላይ በእንጀራ ተሸፍኖ ሊያገኙ መቻላቸውን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

 

በወንጀል ተጠርጥረው በፖሊስ ጣቢያ የተጠርጣሪ ማቆያ ቤት ለሚገኙ ሰዎች ሲጋራ ማስገባት የተከለከለ ሲሆን፤ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በወጣው ደንብ ቁጥር 299/2006 ላይ በተደነገገው መሰረት ትምባሆን በማንኛውም ህዝብ በሚሰበሰብበት ወይም በሚገለገልበት ቦታ ማጨስ ክልክል እንደሆነ ተደንግጎ ይገኛል።