‹‹ሰው ሲራብ ቆሞ መመልከት የሞራልና የፖለቲካ ኪሳራ ነው›› ኦክስፋም ኢንተርናሽናል


ኦክስፋም ኢንተርናሽናል በትግራይ ክልል ጦርነትና የዝናብ እጥረት ያስከተለውን የከፋ የሰብዓዊ ቀውስ ጠቅሶ፣ ‹‹ሰው ሲራብ ቆሞ መመልከት የሞራልና የፖለቲካ ኪሳራ ነው፤›› ሲል አስታወቀ፡፡

ኦክስፋም ጥር 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ በረሃብ የተጠቁ ቤተሰቦች ችግሩን ለማምለጥና በሕይወት ለመትረፍ ሲሉ የመጨረሻ ተስፋ አስቆራጭ ዕርምጃዎችን እየወሰዱ መሆናቸውን አስታውቋል፡፡

በአንድ ትምህርት ቤት ከተጠለሉ ቤተሰቦች መካከል አናገርኳቸው ብሎ ኦክስፋም  በመግለጫው ያሠፈራቸው እናቶች፣ ልጆቻቸው ተርበው ቀኑን በሙሉ የሚያበሏቸው ነገር ማጣታቸውን፣ ልጆቻቸው ረሃቡን ሊቋቋሙ ባለመቻላቸው የረሃብ ሕመምን ለማስታገስ ለረጅም ሰዓታት እንዲተኙ እንደሚያስገድዷቸውና ለእንስሳት የሚሆኑ ሥራ ሥሮችን ለመመገብ መገደዳቸውን መናገራቸውን ገልጿል፡፡ ነፍሰ ጡርና የሚያጠቡ እናቶች በረሃብ እየተሰቃዩ መሆናቸውንም አክሏል፡፡

የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ከአንድ ሳምንት በፊት ባወጣው መግለጫ፣ በፌዴራል ተቋማትና በአማራና በትግራይ ክልሎች የሚመጣው የዕርዳታ ጠባቂዎች መረጃ የተዛባ መሆኑን የሚያመለክት የዳሰሳ ጥናት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

በተቋሙ በወጣው ጥናት በትግራይ ክልል 355 ሰዎች፣ እንዲሁም በአማራ ክልል 23 ሕፃናት በምግብ እጥረት ተገቢውን ዕድገት ባለማግኘታቸው ሞተው ሲወለዱ፣ 21 ሰዎች ድርቁ ባስከተለው ረሃብ መሞታቸውን ገልጾ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ባለፈው ሳምንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ ሲሰጡ ‹‹ድርቅ ለኢትዮጵያውያን ልክ እንደ ባህላችንና እንደ ዓድዋ ድል ለ100 ዓመታት ሲጎበኘን የቆየ ጉዳይ በመሆኑ፣ እንደ አዲስ ሊወራ የሚችል ነገር አይደለም፤›› ብለው ነበር።

‹‹ድርቁን መንግሥት አላመጣውም፣ እንደ ፖለቲካ ማየት የለብንም፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ ችግር አለ፣ ችግኝ እንትከል ሲባል ችግኝ ምን ያደርጋል? ድርቅና ረሃብ አለ ስንዴ እናምርት ሲባል ስንዴ ምን ያደርጋል? ካልን በኋላ ድርቅ መጣ ብለን ብንጮኸ ትርጉም የለውም፤›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡

‹‹ድርቁን ለፖለቲካ መጠቀም ጥፋት ነው፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ባለፉት አራት ወራት 500 ሺሕ ኩንታል ያህል በመንግሥትና በተራድኦ ድርጅቶች ትብብር ለተረጂዎች መላኩን ተናግረዋል፡፡

‹‹ይህ ሀብት በቂ ካልሆነ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት አቅም እያለው በረሃብ የሚሞት ሰው ዓይተን ዝም አንልም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹እስካሁን ባለኝ መረጃ በረሃብ ምክንያት የሚሞት ሰው የለም፤›› ብለው፣ መንግሥት ትናንት እንዳደረገው ዛሬም የሚራብ ሰው ካለ ፕሮጀክት አቁሞ በረሃብ እንዳይሞት ከሕዝቡ፣ ከባለሀብቶችና ከክልል መንግሥት ጋር በመሆን የሚችለውን ሁሉ እንደሚሠራ ገልጸው ነበር፡፡

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ከቀናት በፊት ስለጉዳዩ በሰጡት ማብራሪያ፣ በክልል የከፋ ረሃብ መከሰቱንና ሞትን በዓይናቸው የሚያዩ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰው፣ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የዕርዳታ ጥሪ አቅርበው ነበር፡፡

የኦክስፋም የኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ ‹‹አሁን የሚታየው የችግሩ ጫፍ እንደሆነ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች አስከፊ የሆነ ረሃብ ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉና ዜጎች ቀጣዩን ምግባቸውን ማግኘት ከባድ የሆኑ መንገዶችን እያለፉ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ አስከፊ ከሆኑ የሰብዓዊ ቀውስ ክስተቶች አንዱ ለሆነው የሰሜን ኢትዮጵያ የዕርዳታ አቅርቦት፣ ይጠበቅ ከነበረው አራት ቢሊዮን ዶላር ማግኘት የተቻለው 34 በመቶ ብቻ መሆኑን ኦክስፋም በመግለጫው ጠቁሟል፡፡

አፋጣኝ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ካልተደረገ የበርካታ ዜጎች ሕይወት አደጋ ውስጥ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ በተመሳሳይ ኮንሰርን ወርልድ ዋይድ የተሰኘው ዓለም አቀፍ ድርጅት ዓርብ የካቲት 1 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው ሪፖርት፣ በኢትዮጵያ የተከሰተው ረሃብ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን አስታውቋል፡፡

በአፋር፣ በአማራና በትግራይ ክልሎች የተከሰተው የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ከተሰጣቸው መሰል ክስተቶች እጅግ የላቀ መሆኑን ድርጅቱ በሪፖርቱ አመላክቷል፡፡