ወጣትነት በአትክልቶች መሐል እንዳለ እንደ እንቡጥ ፅጌረዳ ነው !


 

ከወሰንሰገድ መርሻ ደምሴ(ጮራ ዘአራዳ)

«ማንኛውም ሕዝብ ከማንኛውም ዘመን የሚያሳየው አካሄድና እርምጃ የሚታወቀው በወጣቶች አስተሳሰብ ነው።ወጣቶች በሃይማኖት ክፍልም ሆነ በማህበራዊ አቋም።የነገው  አባቶችና የወደፊት ብርሃን ሰጪዎች ናቸው።» ጀርመናዊው  የግጥም ፥የተውኔትና የረዥም  ልቦለድ  ደራሲ ጉቲ የተናገረው  ነው።

 ይህን ለመግቢያነት የተጠቀምኩት ያለምክንያት አይደለም ።በሀገራችን ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት በሚነሱ  ትርምሶችና ብጥብጦች  መንስሄ የሚሆኑትና የጉዳዩ ገፈት ቀማሾች  ወጣቶች ናቸው።አማፂ ኃይልም  ተባለ ነፃ አውጪ  በአብዛኛዎቹ ወጣቶች ናቸው። በመሆኑም  በወጣቶች አካባቢ የታዘብኩትንና  ካላስፈላጊ እራስን መስዋት ከሚያድርጉ  ነገሮች እራሳቸውን እንዴት መጠበቅ እንዳለባቸው  አንድ ለማለትና ለወደፊቱ እራሳቸውን አላስፈላጊ እሳት ውስጥ ላለመክተት  ምን ማድረግ እንዳለባቸው  አንድ ለማለት ፈልጌ ነው።

   በአሁኑ ወቅት ፥ከተለያዩ  የትምህርት ተቋማት የተመረቁ ወጣቶቻችን ሳይቀሩ በሀገራችን ውስጥ  በርካቶች  ሥራ አጥ ሆነዋል።በተለይም  በ፫ ኛው  ዓለም  በሚገኙ ድሀ ሀገሮች  ፥ ደግሞ   የሥራ አጡ  ቁጥር ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ ይገኛል።

ለዚህ ደግሞ ይበልጥ የችግሩ ቀማሽ የሚሆነው  ወጣቱ ትውልድ ነው።

  የሀገራችን ወጣቶችም «እንኳን ዘንቦብሽ እንያውም ጤዛ ነሽ »እንደሚባለው  ፥ እንኳን  በለው  ይዘው  ተብሎ ቀርቶ ለምን  አየኝ ብሎ  በአብዛኛው  ነገር ፈልጎ መጣለት የሚፈልግ  ትውልድ  ነው። በ፫ኛው ዓለም ሀገሮች የሥራ መስክ በብዛት ስለሌለ  ፥ ከሀገር ውጭ ሄዶ የመሥራት ፍላጎታቸውን አንግበው  

በስደት ወደ  ሩቅ ምሥራቅ አገሮች ባህር አቋርጠው  ሥራ ፍለጋ የሄዱ ና የሚሄዱ ወጣቶች በየጊዜው  እየተበራከተ ነው። ጎረቤት ሀገር ኬንያ ፣ጅብቲ ሌላው  ቀርቶ ሰላም  የሌላቸው ሀገሮች ሱማሊያና ሱዳን  ሳይቀር  ለስደት የሚተሙ  ወጣቶቻችን በርካቶች ስለመሆናቸው  የምናየው  እውነታ በመሆኑ እማኝ መቁጠር አይስፈልገኝም።

 በአውሮፓ፣በአሜሪካና በሌሎችም  ሀገሮች  ያሉ ስደተኞች በየጊዜው እየተበራከቱ መሄድ  በውጭ ያለውን  የስደተኞች  የሥራ አጥ ቁጥር እንዲጨምር  በማድረጉ ቤተሰቦቻቸውን ይረዱ የነበሩ ወጣቶች  ፥ አሁን ሥራ አጥ  በመሆናቸው  ፥ ከእነሱ አልፈው የሚረዷቸውም ቤተሰቦቻቸው  ለችግር ተዳርገዋል።

 «ኢትዮጵያ ውስጥ  የሥራ ፈጠራ  ተበራክቷል።ለብዙ ሰዎች  የሥራ እድል ተፈጥሯል ።»መንግሥት ቢልም  የሚታየውና ክዕለት ወደ ዕለት ወደ ውጭ  የሚሰደደው  የስደተኞች ቁጥር  ጨምሯል።በሀገሪቱ ውስጥ ደግሞ  የእርስ በርስ ጦርነት መከሰቱና በአብዛኛው  ሰላም  አለመሆን  ሰው  ለፍቶና ደክሞ  እንዳይኖር ስለሚያደርግ  ከዚህ በፊት በነበረው  በሀገሪቱ የሥራ  ዕጥ ቁጥር ላይ ተደምሮ «በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ » እንደሚባለው  ችግሩን ይብስ ከበፊቱ ከፍ አድርጎታል።በፊት የራሳቸው  ንግድ  የነበራቸው  ወገኖቻችን በሰላም  እጦት ሳቢያ የትውልድ ቀያቸውን እየለቀቁ ወደ ዋናው  ከተማ  መፍለስ ሌላው  ለሥራ አጥ  ቁጥር መጨመር ትልቅ አስተዋጾ አድርጓል።

 ወጣትነት በአትክልቶች መሐል እንዳለ እንደ እንቡጥ ፅጌረዳ ነው።በደንብ  ከተያዘ ይፈካል።ያብባል። ከእራስ አልፎም  ለሌውም  ሽታውም  ደስ ይላል። በደንብ  ካልተያዘ ደግሞ  ፥ አበባው እንደሚጠወልግ ሁሉ  ፥ ብዙ ተሳፋ የተጣለበት ወጣቱም  ትውልድ  መሥራት እየቻለ የሚሰራው  ነገር በማጣቱ ፥ አዕምሮውን መፍትሔ  ባላገኘላቸው  ሐሳቦች  ታጥሮ በየድድ ማስጫው  ፥ በየአደባባዩና ባልባሌ  ሥፍራዎች  ጭምር እየዋለ እንደጠወለገው  አበባ ሲናውዝ ይታያል። ይህ አይነቱ ሁኔታ ድግሞ  ካለሥራ ሲቀመጥ  ፥ የሚበላውና የሚጠጣው ሲያጣ  ፥ አዕምሮው  በጣምና አደገኛ  ወደ ሆነ ምስቅልቅል ወደሆነው የሕይወት ገጠመኞች እንዲገባ ያደርጉታል።

በደፈናው  በአብዛኛውን  ጊዜ  ወጣቶች ያልተስተካከለ ተስፋቢስ ሕይወት ይዘው  በመምራት  ላይ ይገኛሉ።

በዚህም የተነሳ ያለውዴታቸው  ያለግዴታቸው  አጸያፊና አስነዋሪ ድርጊቶች  ላይ እንዲሰማሩ ይደርጋቸዋል።

ወጣቱ ትውልድ ላለፉት አመታት  ፥ ያለውን ተሰጥኦውን መብቱንና ዜግነቱን በነፃነት እንደፈለገበት ሊጠቀምበት አልቻለም ።ይሉቅንም  ለሌሎች ጥቅም ራሱን አሳልፎ በመስጠት  ፥ያለአግባብ ሕይወቱን እስከመገበር ደርሷል።

  በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ስለ ነነትና መብት የታገሉ ወጣቶች ጭድ ሆነው  አልፈዋል።

  በንጉስ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት «መሬት ላራሹ!የፊውዳሎች አገዛዝ ይብቃ! ...»ወዘተ. በማለት ንጉሳዊ የዘውድ አገዛዝ እንዲገረሰስ ያደረገው ወጣቱ ትውልድ ነበር።ይሁንና ወጣቱ የታገለለትና የተዋደቀለት በተለይም «መሬት ለእራሹ !» በማለት የታገሉ ወጣቶች በእነዚሁ ወታደራዊ አምባገነኖች  ፥ የጥይት ራት ሲሆኑ ፥ ከፊሎቹም  ለስደት ተዳረጉ። ከፊሎቹም  እነዚህ ጥቂት ወታደራዊ  አምባ ገነኖች ሥልጣኑን ላለፉት 17 አመታት በመያዝ  መፍትኤ  ለሌለው  የእርስ በእርስ ጦርነት  ፥ በብሄራዊ ውትድርና ሰበብ ሲማገዱት ቆይተዋል። «አንድ ጥይትና አንድ ሰው እስከ ሚቀር ድረስ እንዋጋለን !» ያሉት መሪዎቹ መጨረሻ ላይ ለጅብ ሰጥተውት ጥለዉት ኮበለሉ።

  በረሃ ገብተው  ሲታገሉ  የነበሩትም  ወጣቶች ለስልጣን በቅተው እንኳን  !አብረዋቸው  ሲታገሉለት የነበረውን የወንድሞቻቸውን ፣የገበሬውን ፣የጭቁኑን፣የወዝ አደሩን፣የላብ አደሩን ጥያቄ ከመመለስ ወዘተ.ይልቅ  ፥ አገር በመበታተንና ብሄርን ከብሄር እርስ በርስ በማጋጨትና በማባላት የስልጣን ዕድሜያቸውን ሲያራዝሙ ቆይተዋል። 

  በርካታ ወጣቶች በብልሹ አስተዳደር ምክንያት ሀገር ለቀው ተሰደዋል፣በርካቶች ሞተዋል፣ብዙዎች ለከፋ ሰቆቅ ተዳርገዋል።

ብዙዎቻችንም  የወጣትነት ዕድሜያችንን በአግባቡ እንኳን  ሳናጣጥም  ፥ የፈረንጆች ባሪያ ሆነን አሳልፈናል።

 ላለፉት በርካታ አመታት በወጣት ማህበር ፣በወጣት ሊግ ፣በወጣቶች ፎርም፣በቄሮ፣በፋኖ ወዘተ. እንዲደራጁ በማድረግ ለፖለቲካ አራማጆች መሳሪያ በመሆን በየሰፈሩና በየአካባቢው ሕዝቡን በማተራመስ ፤ድሀው ኅብረተሰብ ሰርቶና ለፍቶ እንዳይድር በችግር ያሳደጉትን እናትና አባቱን ሳይረዳ የውሻ አሟሟት እንዲሞትም ሲያደርጉት ተስተውሏል።ዛሬ ደግሞ  ያለፈው ሥርዓት ወዳጅ የነበሩ ወጣቶች ተገልብጠው  ተቃዋሚ  ሆነው  ብቅ ብለዋል።

  እነዚህ ከየሰፈር ፣ከየመንደሩ የተለቃቀሙ  ወጣቶች ለፖለቲካ አቀንቃኞች  ድብቅ ዓለም  ማስፈፀሚያ የሆኑ፤ በፖለቲካ መዋቅር ተካተው  የታሰሩ የፖለቲካ መሳሪያዎች ናቸው  ማለት ይቻላል።

  አብዛኛው  ለፍቶ ደክሞ  በላቡ የሚኖረውን ወጣት ማስፈራራት፣መንጠቅ ፣የሚሰራበትን ባጃጅ፣ላዳና የሚኒታክሲዎችን፣ታይገሮችን፣የቤትና የጭነት መኪናዎችን ፣የሕዝብ ትራንስፖርት መገልገያዎችንማቃጠል፣መስታወት መሰባበር፣ስቆችን፣ዳቦ ቤቶችን የተለያዩ የተሰሩና የሚሰሩ እንፃዎችን  ፥ መስታወቶችን  ፥ እየሰባበሩ መዝረፍ  በአሁኑ ወቅት ሀገራችን ውስጥ እንደ ባህል  ተቆጥሯል።ሰሞኑን በየማህበረ ሚዲያዎች ጭምር የህዝብ መኪናዎችን  እያቃጠሉ  ትልቅ ጀብዱ  እየፈፀሙ መሆኑን  እያሳዩን ነው። ይህ ብቻ አይደለም

ማቁሰል፣መግደልና ኢሰባአዊ የሆኑ ድርጊቶችን ሲፈፅሙ  መመልከት  ፥ ማሳዘን ብቻ ሳይሆን አንድ ዜጋ ሆነን ስንመለከተው በጣም  ሲበዛ  ያማል ።

 አብዛኛው  ወጣቶች  ማንነታቸው  ሲፈተሽ  ስራ አጥ  የሆኑ ሱሰኞች፥ቀማኛና ዘራፊዎች  ፥ ከፊሎቹም  የቤተሰብ  ሸክም  የነበሩ ናቸው።በእርግጥ ሰራተኞች የነበሩም  እንዳሉ አልዘነጋንም። በእርግጥ  በአብዛኛው  በፎረም ተደራጅተው የነበሩ በተለያይ ምክንያት  ፍርፋሪ  ሲጣልላቸው    ጭራቸውን የሚቆሉ  ፥ የሰፈር አውደልዳዮች  የነበሩ  በርካቶች  እንደነበሩ መዘንጋት  የለብንም

  እነዚህ ወጣቶች ለማንኛውም የፖለቲካ ድብቅ ዓለም ማስፈፀሚያ ወይንም ፈፃሜ በመሆንም ይታወቃሉ።

  እንደነዚህ አይነት  ፥ የወደፊት ተስፋና ራዕይ የሌላቸው ወጣቶች መቃሚያና መጨበሻ  ካገኙ  ፥ አይደለም ሌላ ሰው  የእናታቸውን ልጅንም  ለካራ አሳልፈው  የሚሰጡ ናቸው።

 ጀርመናዊው  የግጥም፥የተውኔትና የረዥም  ልቦለድ ደራሲ ጉቲ እንደሚለው «ማንኛውም ሕዝብ ከማንኛውም ዘመን የሚያሳየው አካሄድና እርምጃ የሚታወቀው በወጣቶች አስተሳሰብ ነው።ወጣቶች በሃይማኖት ክፍልም ሆነ በማህበራዊ አቋም።የነገው አባቶችና የወደፊት ብርሃን ሰጪዎች ናቸው።»

  እንዳለው የነገው አገር ተረካቢ የሚያሳየው ብልሹ አካሄድና ድርጊቶች  ፥ አሁን ያለንበትን ሁኔታ ፍንትው አድርጎ የሚያሳዩ  ፥ የአስተሳሰባቸው  ነጸብራቅ ነው።

  በአገራችን ውስጥ  የሥራ ባህል አለመኖሩ ።ሌላው ቀርቶ ትንሽም ቢሆን ፊደል ከቆጠረ በኋላ ሥራ ቢጠፋ እንኳን  ፥ ወደ ግብርና  ፥ ከብት እርባታ ውስጥ በመግባት  ፥ በሚሰራው ሥራ ላይ ትኩረት ሰጥቶ  ፥ እዛው ያሉበት ሀገር ከመንቀሳቀስ ይልቅ ፤ አብዛኛው ወጣት በአንዴ ለመክበር (ሀብታም)ለመሆን ካለው ፍላጎት አንፃር ፥ በአቋራጭ ስልጣን ላይ የመቆናጠጥ ፍላጎት ስላላቸው  ፥ ወይ ፖለቲከኛ መሆንን ይመርጣሉ  ፥ ወይንም  ወደ ከተማ በመጉረፍ ብሄራቸውን በመጠቀም እያስፈራሩ መኖርን ሲመርጡ   ከፊሎችም ጥገኝነት ማግኘት ብጥብጥ በማንሳት እየመሰላቸው  እሳት ለኩሰው ሲሰደዱ ይስተወላሉ።

 ከዚህ ሌላ እርስ በእርስ በርዕዮት ዓለም ተለያይቶ እንዲጨፋጨፍ ጦርነት እንዲካፈል ማድረጉ ሳይንስ በዜግነቱ  እንዳይሰራና አዕምሮው  እንዲላሽቅ ከሀገሩ ይልቅ ሌላውን ሀገር ናፋቂ ሲያደርጉትም  ተስተውሏል።

   የሀገራችን ወጣቶች ንቃተ ህሊናቸውን  ፥ እንዲያዳብሩ መገፋፋት እንጂ  ፥ተረት ተረት እያወሩ ፥ያልሆነ አመለካከት ይዘው እንዲጎዙ የሚያደርጉ የመገናኛ ብዙሐን አካሎችም ፥ሆኑ ማህበራዊ ሚዲያዎች የእኔ ወንድም ወይም እህት ብትሆንስ ብሎ በእነሱ ቦታ አስቀምጠው እራሳቸውን ሊፈትሹና  ከእዚህ አድራጎታቸው  ሊቆጠቡ  ይገባቸዋል ባይ ነኝ።

የአገር አንድነትን የሚያናጉ፤ብሄርን ከብሄር የሚያጣሉ ወገኖች ላይ መንግስት እየወሰደ ያለው እርምጃ  ብቻ ተገቢነት ያለው  ነው ልንል እንችላለን።ይሁንና መንግሥት እርምጃዎችን በዘፈቀድ ብቻ በስመ  ወጣት ላይ ተመርኩዞ መውሰዱ «ሊበሏት ያሰቧትን ...» እንደሚባለው ካለፉት ጊዜያት  ተመኩራችን  በመመርኮዝ ንጹሐን የሆኑ ወገኖቻችን የእስሩ ሰለባ እንዳይሆኑ ፍራቻችን ላቅ ያለ ነው።እንዲያውም በርካታ  ከብጥብጡ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የሌላቸው ወጣቶች የእስር ሰለባ እንደሆኑም እየሰማን ነው ።ይህ ተገቢ ካለመሆኑም ባሻገር በእሳት ላይ ቢንዚን እንደመጨመር ስለሚቆጠር የሰላም ጥሪው በይበልጥ ሊበረታታና ሊደገፍ ይገባል ባይ ነኝ።

 በአንፃሩ ቂቤ በጠጣ ዱላቸው የሰው መስታወት የሰባበሩ ወጣቶች ከተማ ውስጥ በሚነሱ ብጥብጦች እያየን  ማንም  የነካቸው እንደ ሌለ ስናይ ዘረኝነትን እንደ ማበረታታት ስለሚቆጠር መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይም ትኩረት ማድረግ እንደሚኖርበት ሳናሳስብ  አናልፍም። 

አምባገነኑ (dictatorship)ለመሆኑ ማነው  ወጣቱ ወይስ …?

ከአዲስ አበባ ውጪ  ጭምር ፥በተለያዩ ክልሎች የታየው ብጥብጥና ትርምስ ፤ በተለይም  በአማራና በኦሮሚያ ክልል   ሰው  የለፋበትንና የደከመበትን ቤት ንብረት እስከ ሰበአዊ ፍጡር ከሆነው የሰው ልጅ ጋር ጭምር እንደናዚዎች እስከ ነፍሳቸው  ያቃጠለው  ይህ አሳዛኝ የሆነው ወጣቱ ትውልድ ነው።

ዘርፈውና ሰርቀው የሚበሉ ወጣቶች እንዳሉ ሁሉ፤በኅብረት ተሰባስበው  ሀገራቸውን የሚያገለግሉ ወጣቶች እንዳሉም አልዘነጋውም። ፣

አሁንም በበጎ ሥራ ላይ የተሰማሩ በርካታ ወጣቶች  አሉ።

 በየክልሉ ያሉ ወጣቶች ከአዲስ አበባ ወጣቶች ብዙ የሚማሩት ይኖራል ባይ ነኝ።በአንድ ወቅት  በአገራችን ውስጥ ተከስቶ በነበረው ብጥብጥ

አብዛኛውን የአዲስ አበባ ወጣቶችን እንዳየሁት « ሌባ» እያሉ የሰው ንብረት የሚዘርፉትን ፤የሚሰባብሩትና አስመሳይና አድርባይ አጭበርባሪዎችን  አደብ ሲያስገዙ ተመልክቻለው።ይህ በክልል ወጣቶች ላይም መታየት ያለበት ጉዳይ ነው።

 በባንዲራና በሀገሩ የማይደራደረው  የአዲስ አበባ ወጣቶች  የብሄር ፖለቲካ አንግበው አንዱን ብሄር ከሌላው ብሄር ለማጣላት ሳይሆን ተነስተው  የነበረው  በወቅቱ  ሌባና ዘራፊዎችን ማስቆም  ነበር ዋናው  አላማቸው። 

  በአሁኑ ወቅት የጠቅላይ ሚኒስትራችን የዶክተር አብይን  የለውጥ ሂደት  ፥ የአዲስ አበባ ወጣቶች እንደበፊቱ መቶ በመቶ ባይቀበሉም ሌላው  ቢቀር ሃምሳ  በመቶ አሁንም እንደሚደግፏቸው ከአብዛኛው ወጣቶች ለመረዳት ችያለው።

በእርግጥ ባለፉት ጊዜያት መቶ በመቶ  ነበር ለምን ግማሽ ኃይሉ ከበፊት አቋሙ አፈገፈገ ብሎ መጠየቅም ያስፈልጋል  ። ሰኔ አስራ ስድስት ቀን  ለዶክተር አብይ አህመድ መስቀል አደባባይ ለተደረገው የድጋፍ ሰልፍ፤ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አቀባበል ሲደረግ፤ አክቲቪስትና አርቲስት ታማኝ በየነ ወደ ሀገር ቤት  ሲገባ፤ ለአርበኞች ግንቦት ሰባት አቀባበል ሲደረግ፤ለኦነግ አመራሮች አቀባበል ሲደረግ፤የእነዚህ ወጣቶች ሚና ጉልህ ድርሻ ነበራቸው።

በየወረዳው አምሳያዎቻቸውን በመሰብሰብ የሰልፉ ወይንም የአስተሳሰቡ  ፊት አውራሪ በመሆንም ትልቅ ሚና ተጫውተዋል

 ለምን በየክልሉ ያሉ  ወጣቶች አሁን አሁን ከብሄር ጋር ለምን እንደሚፈረጁ አልገባኝም።

ለዶክተር አብይና አመራራቸው ልዩ አክብሮትና አድናቆት ያላቸው ፥እነዚህ ወጣቶች ፥ ለምን በፋኖ ስምና በኦነግ ሸኔ ስም ደጋፊ ናችሁ እየተባሉ  የሚታሰሩበት  ምክንያት  አሁንም  አልገባኝም።ይህ ሁኔታ ነው በእሳት ላይ ቤንዚል እንደ ሚጨመር  ስለሚቆጠር ጥንቃቄ ማድረግ  ይገባልም  ያልኩት።

አንዳንዴ  «አህያውን ፈርቶ ዳውሎውን !» እንደሚባለው ይሆን? ከዚህ ሁኔታ መንግሥታችን ትምህርት ሊወስድ ይገባል ባይ ነኝ።በእርግጥ የሰፈር ቡድን መስርተው  ሰላማዊ ወገኖቻችን ላይ ችግር የሚፈጥሩ ወጣቶች ላይ መንግሥት ዝም ብሎ ይመልከት አላልኩም።

  ማንም አካል ባለስልጣኖቻችንም ቢሆኑ ለሕግ ተገዥ  መሆን እንዳለባቸው  እርግጥ  ነው።

 ሚዲያዎቻችን  የመንግሥት ዓይኖች ናቸው ።መንግሥት ያላየውን ድክመቱንና ጉድፉን አብጠርጥረው  የሚያሳዩት ከማንም ወገን ያልወገኑ  ሚዲያዎቻችን ናቸው።

በኅብረተሰቡ ውስጥ ያሉ አመለካከቶችና የተለያዩ አስተያየቶች የሚንፀባርቅበት ነው  ሚዲያ። ባለስልጣኖቻችን 

ከደህንነት ሰራተኞቻቸው ከሚያገኙት መረጃ በተሻለ መልኩ  ፥ በሚዲያ ላይ የሚሰራጨው  ፥ ከኅብረተሰቡ  የሚሰራጩ  አስተሳሰቦችና ወሬዎች የተሻለ መሆኑን ባለሙያተኞች ይናገራሉ።

ይሁንና ባለስልጣኖቻችን ሚዲያዎችን ማስፈራራትና ኢንተርኔቶችን ማፈን  ፤የመናገርና የመጻፍ  የፕሬስ ነፃነት በአገራችን ውስጥ  አለመኖሩንና ሚዲያው  አደጋ ላይ ስለሆነ ለወደፊቱ  እንዲታሰብበት  ከወዲሁ  መልክቴ ነው።

በአገራችን ውስጥ  እየታየ ያለው  የዲሞክራሲ ጭላንጭልም እንደ ጎረቤታችን

ኤርትራ ገደል እንዳይገባም  በብልጽግና ፓርቲ ስም የተሰገሰጉትን የቀድሞ የወያኔ ጭንብል ያጠለቁ እንክርዳዶችን በመልቀሙ  በኩል የሚመለከታቸው ወገኖች ፤በረጋ መንፈስ ሊያስቡበት ይገባል ባይ ነኝ 

ሌላው  ቀርቶ በአሁን ወቅት ያሉ ሚዲያዎች  ፥ አናሳ ናቸው።በተለይም የፕሪንቲንግ  ሚዲያዎች እንደ አጀማመራቸው  አይደለም ። በእትመት ብዛትም ሆነ ገበያ ላይ ያሉት በጣም አነስተኛ ብቻ ሳይሆኑ ከገበያ እንደሌሎቹ ላለመውጣት  በኪሳራ እያሳተሙ  ለገቢያ  በማቅረብ በመንፈራገጥ ላይ የሚገኙ ናቸው።

  በፕሪንቲንግ ሚዲያው ዘርፍ

ደብዛቸው  ጥፍቶ በዓለም አቀፍ መድረክ ከወዳጃችን ከኤርትራ ጎን  ፥ እንዳንመደብ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል መልዕክቴ ነው።አንድ መጽሐፍ ላይ It is not the human who are bad here in west,it is the society

(በሰለጠነው በምዕራቡ ዓለም መጥፎው ግለሰቡ ሳይሆን ማህበረሰቡ ነው )የሚል ነገር

አንብቤአለሁ ።

ኢትዮጵያ ውስጥ በፊት እንደ ችግር ይታይ የነበረው የግለሰቦች ምቀኝነትና ክፍት ብቻ  ነበር አሁን ግን ምቀኝነቱና ክፍቱ እንዳለ ሆኖ ማህበረሰቡ ወይም መስተጋብራዊ ኑሮው የተበላሸ ሆኖ በበኩሌ አግኝቸዋለሁ ! ስለዚህ ሊታረም ይገባዋል።እያልኩ መልዕክቴን ቋጨው ክብረት ይስጥልኝ።