የጃፓን የቁንጅና ውድድር አሸናፊ ከውስልትና ጋር በተያያዘ ዘውዷን መለሰች


የጃፓን የቁንጅና ውድድር አሸናፊ ከባለትዳር ጋር ግንኙነት አላት የሚል ዘገባ መውጣቱን ተከትሎ የአሸናፊነቷን ዘውድ መለሰች።

የዩክሬን ተወላጇ የቁንጅና ውድድር አሸናፊ አወዛጋቢው ዘገባ መውጣቱን ተከትሎ በፈቃዷ ከአሸናፊነቷ ራሷን አግልላች።

የ26 አመቷ ካሮሊና ሺኖ ከሁለት ሳምንታት በፊት ‘ሚስ ጃፓን’ ተብላ መሰየሟን ተከትሎ ከዩክሬን ትውልዷ ጋር ተያይዞ ውዝግብም ተነስቶ ነበር።

ጃፓናዊ ዜግነት እስካላት ድረስ አሸናፊነቷን በመልካም ያዩት የኖሩትን ያህል ሌሎች ደግሞ የጃፓን ባህላዊ የውበት እሴቶችን አትወክልም በሚል መከራከሪያም ሆና ነበር።

በዚህም ክርክር ውስጥ እያለ ነው አንድ የአገሪቱ መጽሄት ከአንድ ባለትዳር ጋር መወስለቷን የሚያጋልጥ ዘገባ ይዞ የወጣው።

ሹካን ቡንሸን በተባለው መጽሄት ዘገባ መሰረት የቁንጅና ተወዳዳሪዋ ባለትዳር ከሆነው ዶክተር እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰው ጋር ግንኙነት እንደነበራት ነው።

ግለሰቡ በዚህ ዘገባ ላይ ምንም አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።

ዘገባው በወጣ በሳምንቱ የቁንጅና ውድድሩ አዘጋጆች በሰጡት የመጀመሪያ ምላሽ ሺኖ ግለሰቡ ማግባቱን አታውቅም ነበር ሲሉም ተከላክለዋት ነበር።

ነገር ግን በትናንትናው ዕለት በድጋሜ በሰጡት መግለጫ ግለሰቡ ባለትዳር መሆኑን እንዲሁም ቤተሰብ መመስረቱን ታውቅ እንደነበር አምና ተናዛለች ሲሉም ተናግረዋል።

አሸናፊዋ ለሰራችው ጥፋት ይቅርታ ጠይቃም ከአሸናፊነቷም ራሷን ማግለሏንና ይህም በአዘጋጆቹ ዘንድ ተቀባይነት እንዳገኘ የሚስ ጃፓን ማህበር አስታውቋል።

ሺኖም ሰኞ ዕለት ባወጣችው መግለጫ ዘገባው መጀመሪያ ሲወጣ ፍርሃትና እና ድንጋጤ ስለተሰማት የሰጠችው ምላሽ እንደሆነ በመናገር አድናቂዎቿን እንዲሁም ህዝቡን ይቅርታ ጠይቃለች።

“በፈጠርኩት ከባድ ችግር እንዲሁም የደገፉኝን በመክዳቴ ይቅርታ እጠይቃለሁ” ብላለች።

የአሸናፊነቱም ስፍራ ለዓመት ያህል ክፍት ሆኖ እንደሚቆይም ተገልጿል።

ካሮሊና ሺኖ በጃፓን ታሪክ የአውሮፓዊ ዝርያ ያላት የመጀመሪያ የቁንጅና ውድድር አሸናፊ ነበረች።

ከዩክሬናዊ ቤተሰቦች የተወለደችው ካሮሊና ከእናቷም ጋር በአምስት አመቷ ነው ወደ ጃፓን የሄደችው። መጠሪያዋም ጃፓናዊ በሆነው የእንጀሯ አባቷ ስም ነው። የጃፓንን ቋንቋ አቀላጥፋ መናገርም ሆነ መጻፍ የምትችል ሲሆን ከዓመት በፊት ነው ጃፓናዊ ዜግነቷን የተቀበለችው።

ዜግነቷንም ካገኘች በኋላ በሰጠችው አስተያየት “በርካታ ጊዜያት ጃፓናዊ መሆኔ ተቀባይነት አላገኘም ነበር በዛሬዋ ዕለት ጃፓናዊ መሆኔ ዕውቅና ማግኘቱ አስደስቶኛል” ብላለች።