ዓይነ ስውሯ ወጌሻ


 

ወደዚህ ሙያ ከመግባቷ በፊት መወልወያ እና መጥረጊያ እያዞረች ትሸጥ ነበር

 

ብሌን ሰለሞን ትባላለች፡፡ ገና የ3ኛ ክፍል ተማሪ እያለች አስተማሪዋ በማስመሪያ ትመታታለች፡፡ በወቅቱ የደረሰባትን ጉዳት ተከትሎ ህክምና ለማግኘት ወደ ጤና ተቋም አመራች፤ ግን እንዳሰበችው አልሆነም፡፡ በተፈጠረ የህክምና ስህተት ብሌን ሁለቱንም የዓይን ብርሃኗን እንዳጣች ትናገራለች፡፡ 

 

ልበ ብርሀኗ ብሌን ግን ይህ አልሰበራትም፡፡ ወላጅ እናቷ ካረፈች በኋላ በእናቷ ጓደኛ እጅ ያደገች ሲሆን የማሳጅ ሙያን ታስተምራታለች፡፡ ትምህርቷን ከእናቷ ጓደኛ እስከ ተቋም አሳድጋውም በማሳጅ ቴራፒ ሰርተፊኬት አግኝታለች፡፡ 

 

አሁን ብሌን በዚሁ ሙያ ከ12 አመት በላይ መስራት የቻለች ሲሆን ለማሳጅ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ይዛ ቤት ለቤት አገልግሎት እየሰጠች ነው፡፡ 

 

ወደዚህ ሙያ ከመግባቷ በፊት መወልወያ እና መጥረጊያ እያዞረች ትሸጥ ነበር፡፡ የብሌን እናት ጓደኛ ገነት ከበደ ስለ ብሌን ሲያወሩ መቀመጥ የማትወድ፣ ከሰው እጅ መጠበቅ የማትፈልግ ጠንካራ መሆኗን ይናገራሉ፡፡ ትልቅ ደረጃ እንደምትደርስም ያላቸውን ተስፋ ይገልፃሉ፡፡  

 

ብሌን በበኩሏ ከሰው እጅ መጠበቅ አስፈላጊ አይደለም የምትል ሲሆን በሚችሉት ነገር ሁሉ ተንቀሳቅሶ መስራት እንደሚገባ ትገልፃለች፡፡ 

 

ለወደፊትም ደረጃውን የጠበቀ የራሷ ማሳጅ ቤት እንዲኖራት እንደምትፈልግም ለአዲስ ዋልታ ተናግራለች፡፡