በሰው አንጎል ውስጥ የሚገጠመው ‘ቺፕ’ ምንድነው? ለምንስ ዓላማ ይውላል?


የዓለማችን ቁጥር አንድ ባለጸጋ እና የበርካታ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ባለቤት የሆነው ኢላን መስክ ንብረት የሆነው ኒውራሊንክ የተባለው ኩባንያ በሰው ልጅ አንጎል ውስጥ ‘ቺፕ’ መግጠሙን ይፋ አድርጓል።

የመስክ ኩባንያ በሰው አንጎል ውስጥ ቺፕ መግጠም ያስፈለገው የሰው ልጆችን አእምሮ ገመድ አልባ በሆነ መንግድ ከኮምፒዩተር ጋር ለማስተሳሰር ነው።

ይህ የኮምፒዩተር ቺፕ መረጃ የሚያስተላልፉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ትራንዚዝተርስ ከሚባሉ የኤሌክትሮኒክ ቁሶች ጋር እንዲገናኝ ይደረጋል።

ኒውራሊንክ የተባለው ኩባንያ የጤና መቃወስ ባለበት ግለሰብ አንጎል ውስጥ የኮምፒየተር ቺፕ መግጠሙን ያመለከተ ሲሆን፣ ግለሰቡ ቺፕ አእምሮ ውስጥ ከተገጠመ በኋላ “ተስፋ ሰጪ” ለውጦች ማሳየቱን እንዲሁም በእንጎል ውስጥ እንቅስቃሴ መፈጠሩን መስክ በኤክስ ገጹ አመልክቷል።

መጠናቸው ከአንድ የፀጉር ዘለላ እጅግ በጣም የቀጠነ ቺፕ በሰው አንጎል ውስጥ መግጠም ከነርቭ ጋር የተያየዘ ውስብስብ የጤና ችግርን (ኒውሮሎጂካል) ለመፍታት እንደሚያስችል ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

ኒውራሊንክ በሰው ልጅ አንጎል ውስጥ ቺፕ የገጠመው ከአሜሪካ የምግብ እና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን (ኤፍዲኤ) ይሁንታን ካገኘ በኋላ ነው።

በለንድን ኪንግስ ኮሌጅ መምህርት የሆኑት አን ቫንሆስተንበርግ ከዚህ ቀደም ሌሎች ኩባንያዎች ተመሳሳይ በሰው አንጎል ውስጥ ቺፕ የመግጠም ሙከራ ማድረጋቸውን ገልጸው፣ የዚህ ቴክኖሎጂ ውጤታማነት መታየት ያለበት በረዥም ጊዜ ሂደት ነው ይላሉ።

ከዚህ ቀደም አንድ የስዊትዘርላንድ ኩባንያ የሰውነት ልምሻ አጋጥሞት በነበረ ግለሰብ አንጎል ውስጥ ቺፕ ከገጠመ በኋላ ግለሰቡ ለመራመድ በማሰቡ ብቻ መራመድ ችሎ ነበር።

በብስክሌት አደጋ ምክንያት ሽባ ሆኖ መራመድ አቅቶት የነበረው የ40 ዓመቱ ግሬት ጃን ኦስካም አንጎሉ እና በኅብለ ሰረሰሩ ውስጥ በተዘረጋ ቺፕ አማካይነት የመራመድ ፍላጎቱ ከአእምሮ ወደ እግሮቹ ከተላከ በኋላ መራመድ ችሏል።

በስዊትዘርላንዱ ኢኮል ፖሊቴክኒክ የተደረገውን ጥናት የመሩት ፕሮፌሰር ብሎች የምርምራቸው ውጤት እጅግ አስደናቂ ቢሆንም፣ የሰውነት ልምሻ አጋጥሟቸው ለሚገኙ በሽተኞች እንደ ሕክምና አማራጭ አድርጎ ለማቅረብ ገና ዓመታት ሊወስድ እንደሚችል ተናግረዋል።

ግሬት ጃን ኦሳካም የብስክሌት አደጋ ሲያጋጥመው የሰውነት እንቅስቃሴን የሚቆጣጠር የአንጎሉ ክፍሉ ተጎድቶ ነበር። ተመራማሪዎቹም የታካሚው ጭንቅላት ውስጥ ያስገቧቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች ከአእምሮ መልዕክት በመቀበል ወደ እግሮቹ እና የእግር ጡንቻዎቹ ይልካሉ። 

የዚህ የጥናት ዝርዝር ግኝት ግንቦት 2015 ዓ.ም. በታተመው ኔቸር መጽሔት ላይ ወጥቶ ነበር።

ኒውራሊንካም እንዲሁም ተመሳሳይነት ያለው ሙከራን አድርጊያለሁ ቢልም፣ የተደረገው ሙከራ ውጤትን የተመለከተ ዝርዝር መረጃ ግን ይፋ አልተደረገም።

ኒውራሊንክ ከዚህ ቀደም በእንስሳት ላይ ባደረጋቸው ሙከራዎች ብዙ ወቀሳዎች ሲቀርቡበት ነበር።

ሮይተርስ የዜና ወኪል ከአንድ ዓመት በፊት ባወጣው ዘገባ፣ ኩባንያው መሰል ምርምሮችን በእንስሳት ላይ አድርጎ በጎች፣ ጦጣዎች እና አሳማዎችን ጨምሮ 1500 እንስሳት ሞተዋል ብሎ ነበር።

የእንስሳት አያያዝን የሚቆጣጠረው የአሜሪካ ግብርና ቢሮ ግን ኩባንያው ለምርምር ሥራዎች እንስሳትን የተጠቀመበት ሁኔታ ስህተት ሆኖ አላገኘሁትም ብሏል።

ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ኩባንያው ስድስት ዓመታት ጥናት ሲያደርግበት የቆየው የምርምር ሥራው በሰዎች ላይ ሙከራውን እንዲያደርግ ፍቃድ ተሰጥቶ ነበር።

በዚህም መሠረት ቀዶ ሕክምና በሚያደርግ ሮቦት አማካይነት ከፀጉር የቀጠኑ እና መተጣጠፍ የሚችሉ 64 ቺፖች “እንቅስቃሴ በሚቆጣጠተው” የአንጎል ክፍል ጋር እንዲተሳስሩ ተደርጓል።

ኩባንያው እንደሚለው እኚህ ቀጫጭን ዘለላዎች ቻርጅ የሚደረጉት ገመድ አልባ በሆነ ቴክኖሎጂ ነው።

64ቱ ዘለላዎች ምንም ገመድ ሳይጠቀሙ ከአንጎል የሚገኙ መረጃዎችን (ሲግናል) ወደ አንድ መተግበሪያ ይልካሉ። መተግበሪያው ደግሞ አንድ ሰው ምን ዓይነት እንቅስቃሴ ለማድረግ እንዳሰበ መረዳት ይችላል።

በቀድሞው ትዊተር በአሁኑ ኤክስ ገፁ ላይ መልዕክት ያሰፈረው ኢላን መስክ፣ አዲሱ ቴክኖሎጂ መጠሪያው ቴሌፓቲ ነው ብሏል።

ቴሌፓቲ የተሰኘው ስም የተሰጠው ቴክኖሎጂ “ስልካችሁን አሊያም ኮምፒውተራችሁን ይቆጣጠራል፤ ከዚያ በማሰብ ብቻ የትኛውንም ነገር ማድረግ ትችላላችሁ” ይላል መስክ።

አንጎል ውስጥ የሚገባው ቺፕ ደኅንነቱ የተጠበቀ ነው?

ባለሙያዎችን ይህን መመለስ የሚቻለው በሦስት መንገዶች ነው ይላሉ። በአጭር እና በረዥም ጊዜ ሊከሰት የሚችል አካላዊ አደጋዎች እና እንዲሁም ሥነ ምግባራዊ ጉዳዮችን መመልከት ይኖርብናል ይላሉ።

የቢቢሲ የቴክኖሎጂ ዘጋቢ ሿን ማክካለም “የአንጎል ቀዶ ሕክምናዎች መቼም ቢሆን አደጋ ይዘው ሊመጡ ይችላሉ” ትላለች።

ከዚህ ቀደም ይህ ቴክኖሎጂ ሙከራ የተደረገባቸው ከአንድ ሺህ በላይ እንስሳት ሕይወታቸው አልፏል።

ይሁን እንጂ በጊዜ ሂደት እና ዓመታትን ከፈጀው ጥናት በኋላ የአሜሪካ የምግብ እና መድኃኒት ተቆጣጠሪ ድርጅት ሙከራው በሰው ልጆች ላይ እንዲደረግ መፍቀዱ፣ ተያይዞ ሊመጣ የሚችል ጉዳት ዝቅተኛ ሊሆን የሚችል መሆኑን ያመለክታል ትላለች ሿን።

እስካሁን ግን በግልጽ ማወቅ ከባድ የሚሆነው ቺፕ አንጎል ውስጥ መቅበር በረዥም ጊዜ ሊያመጣው የሚችለውን ጉዳት ነው።

ይሁን እንጂ እስካሁን ድረስ ይህ ቺፕ አንጎል ውስጥ ለረዥም ጊዜ ቢቀመጥ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል የሚጠቁም ምንም አይነት ማስረጃ የለም።

ከተፈጥሮ እና ከሕክምና ሥነ ምግባር ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጉዳዮች ግን እንደ ሰዎች አረዳድ የተለያየ አቋም ሊያዝበት ይችላል።

ይህን ቴክኖሎጂ ከማበልጸግ ጋር ተያይዞ የመረጃ አያያዝ፣ ቴክኖሎጂው እንዴት ጥቅም ላይ ሊውል እንደሚችል እና የሰው ልጅ አእምሮን አቅም ከተፈጥሮ ውጪ ከፍ ያደርጋል የሚለው ብዙ ሊያነጋግር ይችላል ትላለች ሿን።

ይህ ቺፕን በሰው አንጎል ውስጥ ማስቀመጥ ለጤና የሚኖረው ከፍተኛ ጠቀሜታን በመጥቀስ ካደነቁት ባሻገር በርካታ ምክንያቶችን በመጥቀስ በጥርጣሬ የሚያዩት በርካቶች ናቸው።

ቢሆንም ግን ውጤታማነቱ እና ሊያስከትል የሚችለው አሉታዊ ተጽእኖ ገና በሂደት የሚፈተሽ እና የታይ በመሆኑ፣ ለቴክኖሎጂው የሚሰጠው አጠቃላይ ድጋፍም ሆነ የሚገጥመው ተቃውሞው ወደፊት የሚታይ ይሆናል።