‹‹ያልተናበበ የተጎጂዎች ልየታና የዕርዳታ አቅርቦት ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አመኔታ እንዲያጡ አድርጓቸዋል›› የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም


በአማራና በትግራይ ክልሎች ያልተናበበ የተጎጂዎች ልየታና ድጋፍ በተገቢው መንገድ ለተጎጂ ወገኖች መድረሱ የሚረጋግጥበት የቁጥጥር ዘዴ ደካማ መሆኑ፣ የዓለም አቀፍ ረድኤት ድርጅቶች አመኔታ እንዳይኖራቸው ማድረጉን የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አስታወቀ፡፡

ዕንባ ጠባቂ ተቋሙ በትግራይና በአማራ ክልሎች በመንግሥት፣ መንግሥታዊ ባልሆኑ የዕርዳታ ድርጅቶችና በኅብረተሰቡ የሚደረገውን ድጋፍ በማስመልከት የባለሙያዎች ቡድን በመላክ፣ ድርቅ ያስከተለውን ጉዳትና በሰብዓዊ ዕርዳታ ረገድ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ላይ አከናወንኩ ያለውን የዳሰሳ ጥናት ማክሰኞ ጥር 21 ቀን 2016 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል፡፡
 

ዕንባ ጠባቂ ተቋም ይፋ ያደረገው የዳሰሳ ጥናት እንደሚያሳየው፣ በፌዴራል የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽንና በትግራይ ክልል በኩል የተረጂዎች ቁጥር ልየታ ላይ የሰፋ ልዩነት አለ፡፡

የአደጋ ሥጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን በትግራይ ክልል ተፈናቃዮችን ጨምሮ 2.2 ሚሊዮን ዜጎች ተረጂዎች እንዳሉ ሲገልጽ፣ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በበኩሉ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ጨምሮ 4.2 ሚሊዮን መሆናቸውን ማስታወቁን አመላክቷል፡፡

እየወጣ ያለው መረጃ ወጥ አለመሆኑን የገለጸው ዕንባ ጠባቂ ተቋም፣ በአማራ ክልልም በተመሳሳይ በክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተቋም፣ በዞንና ወረዳዎች የተጎጂዎች ልየታ ጋር ያልተናበበ በመሆኑ፣ በዕርዳታ ሥርጭትና አቅርቦት ላይ ክፍተት የሚፈጥር መሆኑን አስታውቋል፡፡

በትግራይ ክልል በድርቁ ምክንያት የተጎዱት እንስሳት ከመሞታቸው በፊት በርካሽ ዋጋ እንዲሸጡ፣ በሁለቱም ክልሎች ያልተጎዱ እንስሳትን ወደ አጎራባች ወረዳዎች በማዘዋወር ጉዳት ለመቀነስ የተደረገው ጥረት አበረታች መሆኑ በመልካም ጎኑ የሚታይ መሆኑን ገልጿል፡፡

የፌዴራሉም ሆነ የክልሎች የአደጋ ሥጋትና ሥራ አመራር የቅድመ ማስጠንቀቂያ አሠራር በማስቀመጥ ችግሮችን ቀድሞ ለመከላከል፣ ተከስተውም ሲገኙም መፍትሔ ለመፈለግ የሚያስችል የተጠናከረ ሥርዓት እንደሌላቸው ጠቅሶ፣ ቀድሞ መሠራት የነበረበት አደጋ ሥጋት ቅድመ ትንበያ በሚፈለገው ልክና ወጥ በሆነ መንገድ የማይሠራ መሆኑን በዳሰሳ ጥናቱ አመላክቷል፡፡

በትግራይ ክልል በድርቅ የተጎዱ ወገኖች ባሉበት አካባቢ የዕርዳታ ማዕከላት ባለመኖራቸው ምክንያት፣ ማኅበረሰቡ በእግሩ ረዥም ርቀት በመጓዝ ላልተፈለገ እንግልት መዳረጉ ተገልጿል፡፡

በትግራይ ክልል በደቡብ ምሥራቅ አበርገሌ ወረዳና በማዕከላዊ ዞን ኢስራ ወአዲ ወጅራት ወረዳ የተፈናቀሉ የዜጎች ቁጥር 15,565 የሟቾች ቁጥር ደግሞ 355 መሆኑን አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡

በድርቁ ምክንያት በሁለቱ ወረዳዎች ከተመዘገቡ በኋላ ከትምህርት ገበታቸው ያቋረጡ ተማሪዎች ቁጥር 3,728 እንደሆነ፣ ዋና ምክንያት ሆኖ የቀረበው የሚበሉትና የትምህርት ቁሳቁስ በማጣታቸው መሆኑን ዕንባ ጠባቂ ተቋም አስታውቋል፡፡

በተመሳሳይ በአማራ ክልል በድርቁ ምክንያት 325 ሺሕ ሔክታር የሰብል ማሳ ሙሉ በሙሉ ከምርት ውጪ በመሆኑ፣ በዘጠኝ ዞኖች በ43 ወረዳዎች በ429 ቀበሌዎች የሚኖሩ 1.8 ሚሊዮን ዜጎች ለኢኮኖሚያዊ፣ ለማኅበራዊና ለሥነ ልቦናዊ ችግሮች መጋለጣቸውን ገልጿል፡፡

ዕንባ ጠባቂ የአማራ ክልል የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ኮሚሽን በኩል በድርቅ ምክንያት የሞተ ሰው እንደሌለ ቢገለጽም፣ 21 ሰዎች ድርቁ ባስከተለው ረሃብ መሞታቸውንና በአልሚ ምግብ እጥረት ምክንያት በበየዳ ወረዳ 23 ሕፃናት ተገቢውን ዕድገት ባለማግኘታቸው ሞተው መወለዳቸው አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡

በክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ኮሚሽን በድርቅ የተፈናቀለና በመጠለያ ካምፕ የሚገኝ ዜጋ የለም ተብሎ በውይይት ቢገለጽም፣ በስልክ ናሙና መረጃ ከተወሰደባቸው ዞኖችና ወረዳዎች አገኘሁት ባለው መረጃ የተባለው መረጃ ስህተት መሆኑን ማረጋገጡን ዕንባ ጠባቂ ተቋም አስታውቋል፡፡

ለአብነትም በዋግኸምራ ዞን በአበርገሌ ወረዳ 12,270፣ በሰሜን ጎንደር ዞን 9,100 በላይ ሰዎች በድርቁ ምክንያት የመኖሪያ ቀዬአቸውን መልቀቃቸውን፣ እንዲሁም ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው በቆርቆሮና በኬንዳ መጠለያ የሚገኙ ተፈናቃዮች አሉ ብሏል፡፡

ከጤና ጋር በተያያዘ ተገቢው ድጋፍ ባለመደረጉ ሰዎች ለልዩ ልዩ ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መጋለጣቸውን፣ ለአብነት መረጃ በተሰበሰበበት ሰሜን ጎንደር ዞን 19,399 ሰዎች በወባ፣ 159 ሰዎች በኮሌራ መጠቃታቸውን አስታውቋል፡፡

በአማራ ክልል የድርቅ ተፈናቃዮችን በተመለከተ የመጠለያ ጣቢያ እንደማያስፈልግ በክልሉ መንግሥት አቅጣጫ በመሰጠቱ ተፈናቃዮችን በመጠለያ ካምፕ በማቆየት አገልግሎት እንዲያገኙ አለመደረጉ፣ የድርቅ ችግር ተጋላጮችን መብት የጣሰ ስለመሆኑ ተቋሙ አብራርቷል፡፡

በነበረው ጦርነትና አሁን ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት በአበርገሌ ወረዳ 12 ቀበሌዎች መንግሥት ገብቶ ድጋፍ ማድረግ ባለመቻሉ፣ በቀበሌዎቹ የሚገኙ ዜጎች ከሰብዓዊና መንግሥታዊ ድጋፍ ውጪ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

በአማራ ክልል የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ኮሚሽን በኩል በክልሉ ረሃብ አልተከሰተም ተብሎ ሪፖርት የቀረበ ቢሆንም፣ ዕንባ ጠባቂ ተቋም መረጃ በሰበሰበባቸው ወረዳዎች የተከሰተው ድርቅ ወደ ረሃብ በመሸጋገር በዜጎች ጤናና ሕይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ መሆኑን አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡

በመሆኑም በፌዴራል የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽንና በክልሎቹ በኩል የተረጂዎች ቁጥር ልየታ ላይ የሰፋ ልዩነት በመኖሩ፣ ልዩነቱን ሊያጠብ በሚችል ሁኔታ እንዲሠሩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትዕዛዝ እንዲሰጥ ተቋሙ ጠይቋል፡፡

የፌዴራል የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሚያደርጋቸውን ድጋፎች በተገቢው መንገድ ለሚመለከታቸው ተጎጂ ወገኖች መድረሱን ሊያረጋግጥ የሚችልበት አሠራር እንዲዘረጋ ድጋፍና ክትትል እንዲያደርግ፣ በትግራይ ክልል በኩል የተረጂዎች ቁጥር ልየታ ላይ የሰፋ ልዩነት በመኖሩ ልዩነቱን ሊያጠብ የሚችል አሠራር እንዲዘረጋ አሳስቧል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለረሃብ የሰጠው ትርጓሜ የሕፃናት ምግብ እጥረት በሽታ ከ30 በመቶ በላይ መሆኑ ሲረጋገጥ ነው የሚል ስምምነት መኖሩን የገለጸው ዕንባ ጠባቂ ተቋም፣ ‹‹ድርቅ ወይስ ረሃብ ከሚለው የቃላት ምልልስ በመውጣት›› የፌዴራል መንግሥት ከክልል መንግሥታት ጋር በመመካከር ችግሩ የከፋ ጉዳት እንዳያመጣ ዕርምጃ እንዲወሰድ አሳስቧል፡፡

የምግብ፣ የንፁህ መጠጥ ውኃ፣ የእንስሳት መኖና የሕክምና አገልግሎት በበቂ ሁኔታ በማቅረብና ለተፈናቃዮች በስታንዳርዱ መሠረት መጠለያ እንዲኖራቸው በማስቻል የሰውና የእንስሳት ሞት፣ መፈናቀል፣ መሰደድ፣ እንዲሁም የጤና ችግር እንዳይከሰት የክልልና የፌዴራል መንግሥታት በተለየ ሁኔታ ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ ተቋሙ ጥሪ አቅርቧል፡፡