ቶዮታ 50 ሺህ በአሜሪካ የሚገኙ ተሸከርካሪዎቹ እንዳይነዱ አስጠነቀቀ


በታካታ የተሠሩ የአደጋ መከላከያ ከረጢቶች (ኤር ባግ) ፈንድተው ሊገድሏቸው ስለሚችሉ በአሜሪካ የሚገኙ 50 ሺህ የአሮጌ ተሽከርካሪ ባለቤቶች አፋጣኝ ጥገና እንዲያደርጉ ቶዮታ አሳስቧል።

"እንዳይነዳ" የሚለው ማሳሰቢያ ከ2003 እስከ 2005 የተሠሩትን አንዳንድ የመኪና ሞዴሎችን ያካትታል።

እአአ ከ2009 ወዲህ በታካታ በተመረተው የአደጋ መከላከያ ከረጢት ምክንያት ከ30 በላይ ሰዎች ህይወታቸው አልፏል።

“ከረጢቱ ከተዘረጋ በውስጡ ያለው ክፍል ፈንድቶ ስለታማ የብረት ቁርጥራጮችን የመተኮስ ዕድሉ ከፍተኛ ነው” ሲል ቶዮታ ገልጿል።

ይህ ችግር የገጠማቸው ተሽከርካሪዎች የ2003-2004 ሞዴል ኮሮላ፣ 2003-2004 ኮሮላ ማትሪክስ እና 2004-2005 ራቭ4 ናቸው።

በታካታ የአደጋ መከላከያ ከረጢቶች ችግር ምክንያት ከ100 ሚሊዮን በላይ መኪናዎች እና ከ20 በላይ መኪና አምራቾች ተሽከርካሪዎቻቸውን ለጥገና እንዲጠሩ አስገድዷቸዋል።

ከአስር ዓመት ተኩል በላይ በውጣ ውረድ እና አሜሪካ ውስጥ በወንጀል ምርመራ ያሳለፈው ታካታ በ2017 ኪሳራ እንደገጠመው አሳውቋል። ንብረቶቹም በቻይናዊ ባለቤትነት ለተያዘው ኪይ ሴፍቲ ሲስተምስ በ1.6 ቢሊዮን ዶላር ሸጧል።

ቶዮታ ባለፉት ወራት የገጠመው ጉዳይ ይህ ብቻ አይደለም።

በዚህ ሳምንት የጃፓኑ ግዙፍ መኪና አምራች ቶዮታ በናፍታ ሞተሮች ላይ በተደረገው የማረጋገጫ ሙከራ ስህተት ምክንያት የአንዳንድ ተሽከርካሪዎችን ማስረከብ አቁሟል።

በተደረገው ምርመራ የቶዮታ ኢንደስትሪ ሠራተኞች የፈረስ ጉልበት ሙከራዎችን ውጤት አሳስተዋል።

ችግር የገጠማቸው ሞተሮች ሂስ ቫን እና ላንድክሩዘር ስፖርት መኪናን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚሸጡ 10 የመኪና ሞዴሎች ጥቅም ላይ ይውላሉ ሲል ቶዮታ ተናግሯል።

ቶዮታ ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ የቆዩ የደህንነት ሙከራዎችን ማጭበርበሩን ካመነ በኋላ በዳይሃትሱ ላይ የደረሰውን የስነምግባር ጉድለት ለመፍታት ጥረት እያደረገ ነው።

ባለፈው ዓመት መገባደጃ ላይ የዳይሃትሱ ዋና መስሪያ ቤት በጃፓን የትራንስፖርት ሚኒስቴር ምርመራ የተከናወነበት ሲሆን የተሽከርካሪዎቹን ለዓለም ገበያ ማቅረብ አቋርጧል። መንግስት የሦስት የዳይሃትሱ ሞዴሎችን የምስክር ወረቀት ሰርዟል።

በቶዮታ ቅርንጫፎች ውስጥ ስላሉት ችግሮች የተጠየቁት ፕሬዝዳንቱ ኮጂ ሳቶ ሠራተኞቹ በጣም ፉክክር ባለበት ኢንዱስትሪ ውስጥ በፍጥነት ለመሥራት ግፊት እንደነበረባቸው አምነዋል ።

"በጥራት ማረጋገጫ ቦታ ላይ ያሉ ሠራተኞች ብቻ ሳይሆኑ አመራሮቹም ስለጥራት ማረጋገጫ ትክክለኛ ግንዛቤ እንዳልነበራቸው እንገነዘባለን” ብለዋል።