አገር የምትበጠብጡ አደብ ግዙ!


ከሪፖርተር ጋዜጣ የተወሰደ 
 

ኢትዮጵያን ሰላም የሚነሱ፣ ሕዝቡን ደግሞ ለችግርና ለደኅንነት ሥጋት የሚዳርጉና በአጠቃላይ ከፋይዳቸው ይልቅ ጥፋታቸው የላቀ ጉዳዮች በመበራከታቸው መላ መፈለግ ይገባል፡፡ ኃላፊነት በጎደላቸው ፖለቲከኞች የተለመደው አገርን ጤና መንሳትና ሕዝብን ተስፋ ማሳጣት፣ በሌሎች ላይም እየተጋባ ችግሩ ሲባባስ በጊዜ መፍትሔ አለመፈለግ የማይወጡት ቀውስ ውስጥ ይከታል፡፡ ከምድራዊ ሕይወት ይልቅ ለሰማያዊ ሕይወት አድረዋል የሚባሉ የእምነት ሰዎች ሳይቀሩ፣ ከፖለቲከኞች ብሰው የበደል ታሪክ ተንታኝ በመሆን ቅራኔ እየዘሩ ነው፡፡ እነሱ ሊመሩበት የሚገባቸውን መንገድ ስተው ተከታይ አማኞቻቸውን ግራ ሲያጋቡ፣ ችግሩ የአንድ ቤተ እምነት ተከታዮች ወይም መሪዎች ተደርጎ ከተወሰደ በጣም ስህተት ነው፡፡ የሃይማኖት ሰዎች ከፖለቲከኞች ባልተናነሰ ሰላም የሚነሱ ድርጊቶች ላይ ሲሰማሩ፣ ሊከተል የሚችለው አደጋ ከበድ እንደሚል መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከውስጥና ከውጭ ተሰንጋ በተያዘችበት በዚህ አሳሳቢ ወቅት በአስተዋይነት መራመድ ካልተቻለ፣ አሁን ያለውም ሆነ የወደፊቱ ትውልድ ዕጣ ፈንታ ከሚታሰበው በላይ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ ወጣቶችን በአርዓያነት መምራት የሚገባቸው አገር ሰላም ሲነሱ ማየት ያሳፍራል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በየዕለቱ የሚፈበረኩ ችግሮች የመብዛታቸውን ያህል ለመፍትሔ ፍለጋ የሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ያበቃለት እየመሰለ ነው፡፡ አብዛኞቹ ፖለቲከኞች ለልዩነት ዕውቅና ሰጥተው በሰጥቶ መቀበል መርህ ከመነጋገር ይልቅ፣ ወደ ደም መፋሰስ የሚያመሩ ትንቅንቆች ላይ መረባረብ ልማዳቸው ከሆነ በጣም ቆይቷል፡፡ ሥልጣነ መንበሩ ላይ ያሉት ተቀናቃኞቻቸውን በአገኙት አጋጣሚ ሁሉ ከመደቆስ አይመለሱም፡፡ ለሥልጣን የሚታገሉትም ከቀናቸው ተመሳሳይ ድርጊት ከመፈጸም ወደኋላ አይሉም፡፡ እነሱ ብቻ ሳይሆኑ ተከታዮቻቸውም በዚህ ቅኝት ነው የሚመሩት፡፡ አሁን ደግሞ የፖለቲከኞችና የአጃቢዎቻቸው አልበቃ ብሎ ችግሩ ወደ ሃይማኖት ሰዎች ዘንድ በፍጥነት እየተንደረደረ ነው፡፡ የሃይማኖት ሰዎች ለምዕመኖቻቸው ማድረግ የሚጠበቅባቸውን ተልዕኮ ስተው፣ ጭልጥ ብለው ፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ገብተው ሲፈተፍቱ ማየት በእጅጉ ያሳዝናል፡፡ በሕግ ሃይማኖትና ፖለቲካ የየራሳቸውን መስመር ተከትለው እንዲጓዙ ድንጋጌ ባለባት አገር ውስጥ፣ ፖለቲከኛና የሃይማኖት ሰውን መለየት የማይቻልበት ሁኔታ በስፋት መስተዋሉ ከማሳዘንም በላይ ያስፈራል፡፡ የፖለቲካው ችግር ተስፋፍቶ ሃይማኖት አካባቢ ማንዣበብ ሲጀምር ሊያስከትለው የሚችለው ጦስ ሊያሳስብ ይገባ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ በአስተዋይነቱ ምክንያት ለአገር አንድነት ቅድሚያ እየሰጠ አገር እዚህ አድርሷል፡፡ ይህንን የመሰለ መልካምና ታላቅ ሕዝብ በሚኖርባት አገር ውስጥ ፖለቲከኞችም ሆኑ ሌሎች የመረረ ጥላቻ ውስጥ ናቸው፡፡ ማንኛውም ዓይነት ልዩነት ያለ፣ የነበረና ወደፊትም የሚኖር መልካም ፀጋ መሆኑ እየተዘነጋ አገሪቱ እየተጎዳች ነው፡፡  ቀናውን ጎዳና በመተው ጠመዝማዛውን መምረጥ ጠቃሚ አይደለም፡፡ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዝብ መልካም እሴቶች ይከበሩ፡፡ ሁለት ፀጉር ያወጡ ፖለቲከኞችም ሆኑ ሃይማኖቶች ውስጥ ያሉ ሳይቀሩ ለእነዚህ መልካም እሴቶች መከበር ይትጉ፡፡ ጎራ ለይቶ እሳት መቆስቆስ ለማንም አይበጅም፡፡ የሕዝባችን የዘመናት የአብሮነት ፀጋዎች አደጋ ለተደቀነበት የኢትዮጵያ ህልውና በመፍትሔነት ይቅረቡ፡፡ በፖለቲካው መንደር ውስጥ የነገሡት ጥላቻዎች፣ አሽሙሮች፣ ሐሜቶችና ቅራኔዎች ሃይማኖት ውስጥ ሲገቡ ይከብዳሉ፡፡ ለጥቅማ ጥቅምና ለሥልጣን ተብሎ አገር ማድማት ይቁም፡፡ በብሔርና በእምነት ማንነት ስም መቀለድና መቆመር ተገቢ አይደለም፡፡ የአገራችን ሕዝብ መልካም እሴቶች አርዓያ ይሁኑ፡፡ ሃይማኖተኞችም ሆኑ ፖለቲከኞች የማኅበረሰባችን ነፀብራቅ ይሆኑ ዘንድ ዓይናቸውን ይክፈቱ፡፡

ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ የሚያስከብሯት የታላላቅ ገድሎች ባለቤት ናት፡፡ ለዘመናት ሲያናጥሩባት ከኖሩት ድህነት፣ በሽታ፣ ኋላቀርነትና ተስፋ መቁረጥ በላይ የምትኮራባቸው ታሪኮች የተከናወኑባት አገር ናት፡፡ አንገት ሲያስደፉ ከቆዩ መከራዎች በላይ፣ ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች ተምሳሌትነትዋ የላቀ ነው፡፡ ኢትዮጵያ እንደ መርግ ይከብዱ ከነበሩ ቀንበሮቿ በላይ፣ ታሪኮቿና ገድሎቿ አንፀባራቂ ናቸው፡፡ በዚህም ክብር የሚገባት ታላቅ አገር ናት፡፡ በአራቱም ማዕዘናት የሚኖረው የኢትዮጵያ ሕዝብ በውስጡ ያሉትን ልዩነቶች ጥበባዊ በሆነ መንገድ ይዟቸው በእርስ በርስ መስተጋብሩ ተምሳሌታዊ አንድነቱን ይዞ በመቆየቱ፣ ለዘመናት የዘለቀው ይኼው ታሪካዊ አብሮነት ዛሬም ቀጥሏል፡፡ በልዩነት ውስጥ አንድነትን አጉልቶ በማውጣት በደስታውም ሆነ በሐዘን አብሮ እየኖረ ነው፡፡ ለአገሩ ቀናዒ የሆነው ሕዝብ በደስታውም ሆነ በመከራው ጊዜ አብሮ በሰላም ኖሯል፡፡ አሁንም ይህንን አስመስጋኝ ልምዱን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ይህ የኢትዮጵያዊነት ክብር መገለጫ ነው፡፡ የነገዋ ኢትዮጵያ ዛሬ በብሔራዊ ወሳኝ ጉዳዮች በሚግባቡ ልጆቿ መገንባት አለባት ሲባል፣ የኢትዮጵያዊነትን የጋራ መገለጫ ባህርይ ማንፀባረቅ ማለት ነው፡፡ 

በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ከቅርብ ብንጀምር በእስራኤልና በሐማስ ጦርነት ሳቢያ በየቀኑ በርካታ ሰዎች ይገደላሉ፡፡ ባለፉት ጥቂት ወራት በጦርነቱ በሺዎች የሚቆጠሩ አልቀዋል፡፡ በሩሲያና በዩክሬን ጦርነት በርካቶች ከማለቃቸውም በላይ ብዙ ሺዎች ለስደት ተዳርገዋል፡፡ በኢትዮጵያም ያለው ችግር ቢብስ እንጂ ያነሰ አይደለም፡፡ ለዓመታት ሲንከባለሉ የነበሩ ችግሮች መፍትሔ ባለማግኘታቸው፣ ንፁኃን በየአገሩ የግጭት ሰለባ እየሆኑ ነው፡፡ በትግራይ ክልል የተካሄደው ጦርነት አማራና አፋር ክልሎችን ከለበለበ በኋላ አሁን ደግሞ አማራና ኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ ችግሩ ፀንቷል፡፡ ሕግና ሥርዓት ሲጠፋ ውጤቱ ቀውስ ነው፡፡ አሁንም በአገራችን የሚታዩ የዘመናት ችግሮች እንዲፈቱ ከፍተኛ የሆነ የአስተሳሰብ ለውጥ ያስፈልጋል፡፡ ከፖለቲከኞች አልፎ ችግሩ ሃይማኖት ውስጥ ሲገባ ደግሞ መመለሻው ከባድ ነው፡፡ በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ችግሮችን አንጥሮ አውጥቶ በግልጽና በኃላፊነት መንፈስ መፍትሔ አለመፈለግ ለአገር ህልውና አደጋ ነው፡፡ ሁሉም ወገኖች ከተያያዙት የጥፋት ጎዳና መለስ ብለው ለመፍትሔ ካልተባበሩ ውጤቱ ኪሳራ ነው፡፡

ግላዊና ቡድናዊ ጥቅሞችን ለማስከበር ሲባል ትርምስ መፍጠር የዚህ ዘመን ፋሽን ሆኗል፡፡ በዚህ የተካኑ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ብሔርን ወይም እምነትን ለግጭት መቀስቀሻነት እየተጠቀሙበት ነው፡፡ በትምህርት፣ በልምድና በክህሎት ብቁ ያልሆኑ የራሳቸውን ኔትወርክ በመመሥረት ሕዝብን መቆሚያ መቀመጫ ካሳጡ በኋላ፣ ያገኙትን ዘርፈው ሹልክ ማለት ሲፈልጉ ትርምስ ይፈጥራሉ፡፡ አንዱን ብሔር በሌላው ብሔር ላይ፣ እንዲሁም በእምነት ተከታዮች ውስጥ ሰርገው በመግባት ፀብ የሚያጭሩና ከራሳቸው ጥቅም በላይ አገራዊው ዘለቄታ ራዕይ የማይታያቸው ወገኖች ከልካይ የሌለባቸው እስኪመስሉ ድረስ ትርምስ መፍጠርን ልማዳቸው አድርገዋል፡፡ ለሕግ የበላይነት ደንታ ስለሌላቸው ሕገወጥነትን እንደ መደበኛ ሥራ ያዩታል፡፡ ሕዝብን ከሕዝብ ለማናቆር የልዩነት አጀንዳዎችን ያራግባሉ፡፡ በአንድነትና በሰላም ተከባብሮ ይኖር የነበረን ሕዝብ ይበጠብጣሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ ከመጠን በላይ እየተለጠጡ የዜጎችን ሕጋዊና ተፈጥሯዊ መብቶች ከመጣስ አልፈው፣ የአገርን ህልውና ጭምር እየተገዳደሩ ነው፡፡ አገር ፀንታ እንድትቆም የሚያስፈልገው ጨዋነት እየጠፋ ነው፡፡ አገር የምትበጠብጡ አደብ ግዙ!