የአቶ ደመቀ ስንብት እና የሁለት አስርታት ሚናቸው


ከአስር ዓመታት በላይ በአገሪቱ የሥልጣን መንበር ላይ ሁለተኛ ሰው ሆነው የቆዩት አቶ ደመቀ መኮንን ኢህአዴግን በማክሰም ካዋለዱት ገዢው ብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንትነት “በክብር መሸኘታቸው” ተገልጿል።

የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ከሆኑት መካከል አንዱ የነበረው የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) አባል ሆነው ወደ አገሪቱ የፖለቲካ መድረክ የመጡት የቀድሞው መምህር አቶ ደመቀ መኮንን በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ቆይተዋል።

በኢህአዴግ እግር የገዢነት መንበሩን የተረከበውን ብልጽግናን ከመሠረቱ ቁልፍ ፖለቲከኞች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ደመቀ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ወደ ሥልጣን ባመጣው ለውጥ ውስጥም ጉልህ ሚና ከተጫወቱት መካከል መሆናቸው ይነገራል።

የኢህአዴግ አስኳል የነበረውን ህወሓትን በመገዳደር ለውጡን የመሩት የቀድሞዎቹ ኦህዴድ እና ብአዴን አመራሮች ውስጥ አንዱ የሆኑት አቶ ደመቀ በይፋ በክብር ከፓርቲው የተሰናበቱ ከፍተኛ ባለሥልጣን ሊባሉ ይችላሉ።

በሕዝባዊ እንቅስቃሴው ወቅት በሁለቱ ፓርቲዎች ሆነው ለውጡን ለማምጣት ወሳኝ ትግል ሲያደርጉ እንደነበሩ ከሚነገርላቸው ጥቂት ሰዎች መካከል የነበሩት አቶ ለማ መገርሳ እና አቶ ገዱ አዳርጋቸው፣ ከአቶ ደመቀ በተለየ ድምጻቸው ሳይሰማ ነበር ከፓርቲ እና ከመንግሥት ሚናቸው የራቁት።

በዚህም የአቶ ደመቀ ከአምስት ዓመት በፊት በመጣው ፖለቲካዊ ለውጥ ውስጥ ከተሳተፉ ጥቂት አንጋፋ የኢህአዴግ ፖለቲከኞች መካከል ከከፍተኛ የፖለቲካው መድረክ በመልቀቅ የመጨረሻው ሊባሉ ይችላሉ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፖለቲካው የአመራር መድረክ የመራቅ ፍላጎት እንዳለቸው ሲነገር የቆየ ሲሆን፣ በ2014 ዓ.ም. ብልጽግና ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤውን ባካሄደበት ወቅትም የመሰናበት ጥያቄ ማቅረባቸው እና ተቀባይነት አለማግኘቱ ተገልጾ ነበር።

በፓርቲ፣ በክልል እና በፌደራል መንግሥት 

አቶ ደመቀ ከ20 ዓመታት ለሚበልጥ ጊዜ በአማራ ክልል እና በፌደራል መንግሥቱ ውስጥ ባሉ በከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ያገለገሉ ሲሆን በአብዛኛው የሥልጣን ዘመናቸው ያገለገሉት በቁልፍ ቦታዎች ላይ በምክትልነት ነው።

የአማራ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት የነበሩት አቶ ደመቀ፣ ወደ ፌደራል መንግሥቱ ከመጡ በኋላ የትምህርት እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ቦታን ቢይዙም ለ11 ዓመታት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን የአገሪቱን ሁለተኛው ከፍተኛ የሥራ አስፈጻሚ ሥልጣን ይዘው ቆይተዋል።

በተጨማሪም ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ላይ የበላይ ሆነው በቆዩት ኢህአዴግ እና በወራሹ ብልጽግና ውስጥም በወሳኝ የአመራር ቦታ ላይ ከመቆየታቸው ባሻገር የፓርቲዎቹ ምክትል ሊቀመንበርነት ቦታ ላይ ነበሩ።

ይህም አቶ ደመቀ መኮንን ለሁለት አስርት ዓመታት በይፋ ጎልቶ ባይታይም በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ በፓርቲ እና በመንግሥት የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ወሳኝ ሚና እንደነበራቸው ይታመናል።

አቶ ደመቀ ከብልጽግና መሸኘታቸውን ተከትሎ የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነቱን እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነቱን ቦታ ስለመልቀቃቸው በይፋ የተባለ ነገር የለም። ነገር ግን ሁለቱንም ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎችን መልቀቃቸው የማይቀር እንደሚሆን ይታመናል።

አቶ ደመቀ ከፓርቲ ኃላፊነት ቢሰናበቱም ከመንግሥት ሥልጣናቸው ስለመልቀቃቸው በይፋ የተባለ ነገር ባይኖርም ለሽኝታቸው በተዘጋጀ ፕሮግራም ላይ ያደረጉት ንግግር፣ ስንብታቸው ከፓርቲ ብቻ ሳይሆን ከመንግሥት ኃላፊነታቸው ጭምር መሆኑን የሚጠቁም ይመስላል።

የአማራ ክልል ቀውስ

ከብልጽግና ፓርቲ የአማራ ቅርንጫፍ የሚወከሉት አቶ ደመቀ የፓርቲ ኃላፊነታቸን የለቀቁት የመጡበት ክልል በከባድ ፖለቲካዊ እና የፀጥታ ችግር እየታመሰ ባለበት ጊዜ ነው።

ትግራይ ውስጥ ተቀስቅሶ ወደ አማራ ክልል ተዛምቶ የነበረው ጦርነት ቢያበቃም የአማራ ክልል በአሁኑ ወቅት በከባድ ቀውስ ውስጥ እንደሚገኝ ይታወቃል። በዚህም ሳቢያ በበርካታ የክልሉ አካባቢዎች ግጭቶች እየተካሄዱ በመሆናቸው የክልሉ አመራር ፈተና ውስጥ ይገኛል።

ስድስት ወራትን ሊያቀስቆጥር በተቃረበ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር በሚገኘው የአማራ ክልል ውስጥ በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የሚካሄደው ግጭት መቋጫ አላገኘም። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም ስለመቀጠሉም ሆነ ስለመነሳቱ እስካሁን በይፋ የታወቀ ነገር የለም።

የታጣቂዎቹ እንቅስቃሴ ከክልሉ አቅም በላይ ሆኖ የፌደራሉ መንግሥት ጣልቃ ገብነት ከተጠየቀ በኋላ የተዋቀረው የክልሉ አዲስ መስተዳደር በሁሉም አካባቢዎች መዋቅሩን ለማጠናከር ካለመቻሉም በላይ ግጭቶቹ ያዝ ለቀቅ በማለት እንደቀጠሉ ናቸው።

ምንም እንኳን አቶ ደመቀ ከክልሉ የወጡ አንጋፋ የገዢው ፓርቲ እና የመንግሥት ባለሥልጣን ቢሆኑም፣ የአማራ ክልልን እያመሰ ስለሚገኘው ቀውስ ባለፉት ስድስት ወራት ለዲፕሎማቶች ከተናጉት ውጪ ያደረጉት ጥረት ስለመኖሩ አይታወቅም።

ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ አቶ ደመቀ ለዲፕሎማቶች በሰጡት ማብራሪያ በአማራ ክልል ውስጥ በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተፈጠረውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረው ነበር።

ነገር ግን እስካሁን ግጭቱ የቀጠለ ሲሆን ሰላም ለማውረድ የተደረገ ጥረት ስለመኖሩ ከአቶ ደመቀም ሆነ ከሌሎች አካላት የተባለ ነገር የለም።

ከስንብታቸው በኋላ በተካሄደ የሽኝት ሥነ ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እያጋጠሙ ያሉ የሰላም መታጣቶች እና ፈርጀ ብዙ ጉዳቶች ያሏቸው “ሞት፣ መፈናቀል፣ ምስቅልቅል ማኅበራዊ መስተጋብር” ልብ የሚሰብር ነው ሲሉ ያለውን ችግር ገልጸዋል።

ሚናቸው እና ክፍተት

አቶ ደመቀ ረጅሙን የፓርቲ እና የመንግሥት የኃፊነት ቦታቸውን ያሳለፉት በምክትልነት ቦታ ላይ በመሆኑ፣ የበላይ አለቆቻቸው ባሉበት ሁኔታ ይህ ነው የሚባል ጉልህ ሚና ሊኖራቸው የሚያስችል አይደለም የሚሉ በርካቶች ናቸው።

በክልል ደረጃም ለረጅም ጊዜ በፌደራል መንግሥት የኃላፊነት ቦታ ላይ በመቆየታቸው በአብዛኛው ግንኙነታቸው ከፓርቲው አመራሮች እና ከማዕከላዊ መንግሥቱ ጋር ስለሚሆን ተጽእኗቸው የጎላ እንዳልነበረ ይነገራል።

ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ሌሎችም የፓርቲያቸው አባላት አቶ ደመቀ መኮንን ለፓርቲውን ሆነ በመንግሥት ሥራቸው ሚናቸው የጎላ መሆኑን ይናገራሉ። በተጨማሪም ኃላፊነት ለመልቀቅ ያቀረቡት ጥያቄም ተቀባይነት ሳያገኝ የቆየው አስተዋጽኦቸው አስፈላጊ በመሆኑ እንደነበር በወቅቱ መገለጹ ይታወሳል።

በተጨማሪ ደግሞ አቶ ደመቀ ከፓርቲ አመራርነት ባሻገር ከጠቅላይ ሚኒስትርነት እና ከውጭ ጉዳይነት የሚለቁ ከሆነ፣ በተለይ በዲፕሎማሲው መስክ አገሪቱ ወሳኝ ሥራ በሚጠብቃት ጊዜ መሆኑ ነው።

በተለይ ከሶማሊላንድ ጋር የተደረሰውን የባሕር በር የማግኘት ስምምነት እና እሱን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ዲፕሎማሲያዊ ወጀብን ለማርገብ እና ሊያስከትል የሚችለውን ጫና ለመቆጣጠር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትከሻ ላይ የወደቀ ኃላፊነት ነው።

ስለዚህም አቶ ደመቀ የጀመሯቸውን ሌሎች ሥራዎችን ለተተኪያቸው ከማስተላለፍ ባሻገር ትኩሱን ውዝግብም ለአዲሱ ሚኒስትር ትተው የሚያልፉት ጉዳይ ነው።

አቶ ደመቀ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ከቆዩበት ኃላፊነት ከፍተኛ የአገሪቱ አመራሮች በተገኙበት በተሸኙ ጊዜ ባደረጉት ንግግር “ሕገ መንግሥትን ከማሻሻል ጀምሮ . . . ለዜጎቿ የተመቸች እና የበለፀገች አገር ለመገንባት” የመረባረብ አስፈላጊነትን አንስተዋል። 

ከአንድ ትውልድ ዕድሜ በላይ በአመራርነት ጉዟቸው በስኬት እና በፈተና ውስጥ እንዳለፉ ያመለከቱት አቶ ደመቀ፣ በዚህ ሂደት ውስጥ “ላጎደልኩት ነገር ሁሉ ይቅርታ እጠይቃለሁ” ብለዋል።