ኢጋድ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በመካከላቸው የተፈጠረውን ውጥረት እንዲያረግቡ ተማጸኑነ


የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) አባል ሃገራት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በመካከላቸው የተፈጠረውን ውጥረት እንዲያረግቡ ተማጸኑ። ትናንት 42ኛውን ልዩ ጉባኤውን በኢንቴቤ ዩጋንዳ ያካሄደው ኢጋድ ምሽቱን ባወጣው መግለጫ በፌደራል ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኢትዮጵያ እና በፌደራል ሪፑብሊክ ሶማሊያ ግንኙነት መካከል ሰሞኑን የተፈጠረው ሁኔታ እጅግ እንዳሳሰበው አመልክቷል። ኢጋድ የፌደራል ሪፑብሊክ ሶማሊያን ሉአላዊነት፤ ሕብረት እና የግዛት አንድነት መርሆዎችን ማክበር ወሳኝ መሆኑንም በድጋሚ አረጋግጧል። አያይዞም ማንኛውም የሚደረግ ስምምነትም ሆነ ዝግጅት የሶማሊያ ፌደራል መንግሥትን ይሁንታ ማግኘት እንደሚኖርበት በማመልከትም ፌደራል ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኢትዮጵያ እና ፌደራል ሪፑብሊክ ሶማሊያ ውጥረቱን በማርገብ ገንቢ ውይይቶችን እንዲያደርጉ ጥሪውን አቅርቧል። ጉባኤውን በሊቀመንበርነት የመሩት የወቅቱ የኢጋድ መሪዎች ሊቀመንበር የሆኑት የጅቡቲ ሪፑብሊክ ፕሬዝደንት ኢስማሊል ኦማር ጉሌህ ናቸው። በስብሰባው ላይ የኬንያ ፕሬዝደንት ዶክተር ዊልያም ሩቶ፣ የሶማሊያው ፕሬዝደንት ዶክተር ሀሰን ሼክ መሀመድ፤ የደቡብ ሱዳን ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት፤ እንዲሁም የዩጋንዳው ፕሬዝደንት ዩዌሪ ካጉታ ሙሴቪኒ ተገኝተዋል። ኢትዮጵያና ሱዳንን ጨምሮ የሦስት ሃገራት መሪዎች ግን በትናንቱ የኢጋድ ስብሰባ አልተገኙም።...

... ከድርጅቱ አባል ሃገራት በተጨማሪም የአፍሪቃ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት፤ የተመድ ዋና ጸሐፊ የሱዳን ልዩ መልእክተኛ ራምታኔ ላማምራ፤ የሳውድ አረቢያ ምክትል ሚኒስትር ኢንጂነር ዋሊድ ኤም አልኩራጂ፤ የተባበሩት አረብ ኤሜሬት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኻሊፋት ሻህኒ አል ማራራት፤ የአውሮጳ ሕብረት የአፍሪቃው ቀንድ ልዩ ልዑክ አኔተ ቬበር፤ የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪቃው ቀንድ ልዩ ልዑክ አምባሳደር ማይክ ሀመር፤ የአረብ ሊግ ምክትል ዋና ጸሐፊ ሆሳም ዛኪ፤ በቱርክየ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የምሥራቅ አፍሪቃ ምክትል ዳይሬክተር ቱትኩ ኢናም፤ እንዲሁም በተመድ የአፍሪቃው ቀንድ ልዩ ጽሕፈት ቤት ባልደረባ የሆኑት ቼክ ኮንዴ እና የኢጋድ ዋና ጸሐፊና ሌሎችም ኃላፊዎች በኢጋድ ልዩ ስብሰባ መሳተፋቸው ተዘርዝሯል። ከኢጋድ በተጨማሪም የአፍሪቃ ሕብረት፤ የአውሮጳ ሕብረት እና ዩናይትድ ስቴትስም ኢትዮጵያ እና ራስ ገዟ ሶማሊላንድ በተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ ምክንያት በመቃዲሹ እና አዲስ አበባ መካከል የተፈጠረው ውጥረት እንዲረግብ ጠይቀዋል።  ጉባኤው የተጠራበት ዋና ዓላማ ወራት ያስቆጠረው የሱዳን ጦርነት የሚያቆምበትን መንገድ ለመፈለግ እና በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል እየተባባሰ የመጣውን ውጥረትን በተመለከተ ሲሆን በሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች መካከል አስቸኳይ ተኩስ አቁም ተደርጎ ሁለቱ ወገኖች ወደ ውይይት እንዲመለሱም ጥሪ አቅርበዋል።