የባህር በር የሌላቸው ሀገራት የህዝባቸውን የልማት ጥያቄ ለመመለስ እየተቸገሩ ነው - ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ


የባህር በር የሌላቸው ሀገራት የህዝባቸውን የልማት ጥያቄ ለመመለስና የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ከፍተኛ የሆነ ፈተና እየተጋፈጡና እየተቸገሩ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና የልዑካን ቡድናቸው በዑጋንዳ ካምፓላ በተካሄደው የገለልተኛ ሀገራት ንቅናቄ ርዕሳነ ብሔር እና ርዕሳነ መንግሥታት 19ኛው ጉባኤ ላይ ተሳትፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር የባህር በር የሌላቸው ሀገራት ያለባቸውን ፈተና በተመለከተ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የባህር በር የሌላቸው ሀገራት የህዝብን የመልማት ጥያቄ ለመመለስ ፈተናዎችን እየተጋፈጡ እንደሆነ ማስገንዘባቸውን በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ አመልክተዋል።

የባህር በር የሌላት ኢትዮጵያም ችግሩን ለመፍታት በሰላማዊና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ መሰረት ጥረት እያደረገች እንደሆነ ማስረዳታቸውን ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል  ዶክተር ዐብይ በማህበራዊ ገጻቸው ከኬንያው ፕሬዝዳንት ጋር ዛሬ መነጋገራቸውን እንዲህ በማለት ገልፀዋል።« ከገለልተኛ ሀገራት ንቅናቄ ጉባኤ ጎን ከፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ ጋር ተገናኝተን በቀጠናዊ እና ሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገናል።» ሲሉ ተናግረዋል።