አምባሳደር ማይክ ሀመር በአማራ እና ኦሮሚያ ባጋጠሙ ችግሮች ዙሪያ ለመምከር ወደ አዲስ አበባ እንደሚመጡ ተገለጸ


አምባሳደር ማይክ ሀመር በአማራ እና ኦሮሚያ ባጋጠሙ ችግሮች ዙሪያ ለመምከር ወደ አዲስ አበባ እንደሚመጡ ተገለጸ

መልዕክተኛው በካምፓላ በተጀመረው የኢጋድ የመሪዎች ስብሰባ ላይ እየተሳተፉ ነው ተብሏል።

ኢትዮጵያ በኢጋድ ስብሰባ ላይ በአምባሳደር ምስጋኑ አርጋ መወከሏ ተገልጿል

አምባሳደር ማይክ ሀመር በአማራ እና ኦሮሚያ ባጋጠሙ ችግሮች ዙሪያ ለመምከር ወደ አዲስ አበባ እንደሚመጡ ተገለጸ።

በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሀመር የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት (ኢጋድ) አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ወደ ኡጋንዳ ማቅናታቸውን መንግስታቸው ገልጿል።

ኢጋድ በዛሬው የካምፓላ ስብሰባው በሱዳን፣ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ጉዳዮች ላይ እየመከረ ይገኛል።

የስቴት ዲፓርትመንት ባወጣው መግለጫ በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ መልዕክተኛ በዚህ ስብሰባ በመካፈል ላይ እንደሆኑ አስታውቋል።

አምባሳደር ማይክ ሐመር ከኢጋድ የመሪዎች ጉባኤ በኋላ ወደ አዲስ አበባ እንደሚጓዙም ተገልጿል።

የአምባሳደር ማይክ ሐመር የአዲስ አበባ ጉዞም በፕሪቶሪያ ሰላም ስምምነት አፈጻጸም ዙሪያ ለመወያየት፣ በሱዳን ሰላም ጉዳዮች እና በተያያዥ አጀንዳዎች ዙሪያ ከኢትዮጵያ እና አፍሪካ ህብረት አመራሮች ጋር እንደሚወያዩ ተገልጿል።

በኢትዮጵያ ይተገበራል የተባለው ተጎጂዎችን ማዕከል ያደረገ የሽግግር ፍትህ ዙሪያም ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚወያዩም በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።

በአማራ እና ኦሮሚያ ክልል ያሉ የፖለቲካብእና ደህንነት ችግሮች ዙሪያ፣ ንጹሀንን ከአደጋ መጠበቅ ስለሚቻልበት እና የሰብዓዊ መብቶች ስለሚከበሩበት ሁኔታ ዙሪያ አምባሳደር ማይክ ሐመር በአዲስ አበባ በሚኖራቸው ቆይታ እንደሚመክሩም ተገልጿል።

ስቴት ዲፓርትመንት በኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የመግባቢያ ስምምነት ዙሪያ ባወጣው መግለጫ አሜሪካ የሶማሊያን የ1960 ግዛት እንደምታከብር አስታውቃለች።

ኢትዮጵያ በ42ኛው የኢጋድ የመሪዎች አስቸኳይ ጉባኤ ላይ በአምባሳደር ምስጋኑ አረጋ መወከሏ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አስታውቋል።