ኢዜማ ከሱማሌላንድ ጋር የተደረገውን የባህር ስምምነት በመደገፍ መግለጫ አዋጣ


ኢዜማ ከሱማሌላንድ ጋር የተደረገውን የባህር ስምምነት በመደገፍ መግለጫ አዋጥቷል ።የመግለጫው ሙሉ ቃል የሚከተለው ነው።


ብሔራዊ ጥቅምን በአግባቡ እና በጥንቃቄ መያዝ ያስፈልጋል!!

 

ሀገራችን ኢትዮጵያ በታሪክ አጋጣሚ በተፈጸመ ከፍተኛ የሆነ ስህተት ወይም የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፎ በሰጠ ገዢ መንግሥት ምክንያት ከ 1985 ዓ.ም ወዲህ ባለው ጊዜ ጥቂት ከሚባሉ የባህር በር ከሌላቸው ሀገራት መሀከል አንዷ እንድትሆን ሆኗል። በመሆኑም ይህ ክስተት በቀንዱ እንደ ኢትዮጵያ ያለች በህዝብ ቁጥር እና በኢኮኖሚው ግዙፍ የሆነች ሀገር ላይ በኢኮኖሚው ረገድ ከፍተኛ ተጽዕኖ ውስጥ ሲከታት በገሀድ እንደሚታየው ከኢኮኖሚያዊ ጥቅም ባሻገር የጸጥታ እና ደኅንነትም ላይ የሚያመጣው ተጽዕኖ ከፍተኛ እየሆነ መጥቷል።

ሀገራችን ከላይ በተጠቀሰው መልኩ የባህር በሯን ያጣች ቢሆንም የተባበሩት መንግሥታት የባህር ህግ ሥምምነት አንቀጽ 125 በግልጽ እንደሚያስቀምጠው ባህር በር አልባ የሆኑ ሀገራት በሥምምነቱ የተጠቀሱ መብቶችን ለመጠቀም የባህር በር የመጠቀም መብት እንዳላቸው ይህም ትራንዚቱን የምትሰጠውን ሃገር ህጋዊ ጥቅም ባልነካ እና ከዚችው ሃገር ጋር በሚደረግ ሥምምነት የሚደረግ እንደሆነ ይደነግጋል። የሃገራችን መንግሥት ባለፉት ጥቂት ወራት ይህን መብት ለመጠቀም እንደሚፈልግ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስተር በተደጋጋሚ ሲናገሩ የተሰማ ሲሆን በቅርብ ቀን ይህንን ለማድረግ የሚያስችል የመግባቢያ ሰንድ (MoU) ከሶማሊላንድ ጋር መፈራረሙንም አሳውቋል። 

 

የዚህን ሥምምነት በተለየ ሁኔታ እንዲታይ ያደረገው በተባበሩት መንግሥታት አባል ሀገራት ለሶማሊላንድ በይፋ ይህ ነው የሚባል ዕውቅና አለመስጠታቸው ሲሆን ነገር ግን ይህቺ እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር 1991 ዓ.ም. ጀምሮ የካይሮን ሥምምነት መሰረት አድርጋ እራሷን ሀገር ብላ ባወጀች ሀገር፤ የአፍሪካ ሕብረት እውነት አፈላላጊ ልዑክ (fact finding mission) እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር በ 2005 ዓ.ም ባደረገው ምልከታ ሃገሪቱ ከብሪታንያ ቅኝ ግዛት ስትወጣ የወረሰችው ዳር ድንበር (territory) ይዛ ያለች መሆኑን፣ ነጻነቷን ካወጀች በኋላ ባሉት ጊዜያት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመተግበር የሚያስችሉ መሰረት የጣለች መሆኑ እና የዘመናዊ ሃገር መገለጫዎች የሆኑ ህገመንግሥት እና መሰል ጉዳዮች እንዳሏት እና ሌሎች ዝርዝሮችን አስቀምጦ ለህብረቱ “ከ 1990 በፊት ከሶማሊ ሪፑብሊክ ጋር የተደረገው ህብረት (union) አለመጽደቁን እና ህብረቱ ተፈጽሞ እስኪያበቃ ውጤታማ አለመሆኑን (malfunctioned) ጠቅሶ የሶማሊላንድ ዕውቅና መሻት በአፍሪካ ፖለቲካ ታሪክ የተለየ እንደሆነ ገልጾ ህብረቱ ጉዳዩን ለሌሎች ችግሮች በር ከፋች አድርጎ ከመመልከት ይልቅ ከተጨባጭ ታሪካዊ ሁኔታ፣ ሞራል እና የህዝቡ ፍላጎት አንጻር ተመልክቶ በተለየ ሁኔታ መፍትሔ ሊያገኝ የሚገባ የተለየ አይነት ሁኔታ እንደሆነ ገልጿል። 

 

ከላይ የተጠቀሰው እንዳለ ሆኖ ምንም እንኳን ከዚህ በታች የተዘረዘሩት እውነቶች ህጋዊ ዕውቅናን ለሶማሊላንድ አጎናጽፈዋል ባይባልም ኢትዮጵያን ጨምሮ ሶስት (3) ሀገራት ቆንጽላ ጽ/ቤት ያላቸው ሲሆን ኬኒያ እና ግብጽን ጨምሮ ስድስት (6) ሀገራት የተወካይ ጽ/ቤቶች ከፍተው በዚህች እራሷን ሀገር ብላ ባወጀች ሀገር ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አድርጌ መርጪያቸዋለሁ ካለቻቸው ፕሬዝደንት ጋር እየተነጋገሩ እና ውል እያሰሩ ግንኙነት ሲያደርጉ ከርመዋል፡፡ በእርግጥ የነዚህን ጽ/ቤቶች መከፈት ሱማሊያ ሉዓላዊነቴን የሚጥስ ነው ስትል በተደጋጋሚ አምርራ በዓለምአቀፍ ሚዲያዎች ስታወግዝም ይታያል።

 

ከዚህ በተጨማሪ ሌላው አሻሚ ነገር በዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ሀገር ለመባል በተባበሩት መንግሥታት አባል ሀገራት እውቅና ማግኘት የማይቀር አስፈላጊ ቅድመሁኔታ ነው ወይስ አይደለም የሚለው ይህ ነው የሚባል ሥምምነት አለመኖር ነው። 

 

ኢዜማ የፓርቲው ፕሮግራም ላይ << ኢዜማ ከጎረቤት ሀገሮች ጋር የሚኖረን ግንኙነት በጋራ ደኅንነትና ጥቅም ላይ በመመስረት በፍጹም መተባበር ላይ እንዲሆን፤ የኢኮኖሚ ትሥሥር በማጠናከር ከፍ ያለ የፖለቲካ ትበብር እንዲኖር የሚሰራ ይሆናል፡፡ መንግሥታት በሥምምነት ያጸደቋቸው ዓለምአቀፍ ህጎችና ሥምምነቶች በሁሉም ሀገራት እንዲፈጸሙ፣ የሀገራችን ሉዓላዊነት እንዳይገሰስ፣ ደካማው በጠንካራው እንዳይጠቃ፣ የተባበሩት መንግሥታት ፍትሃዊ የውሳኔ መስጫ አግባብ እንዲኖረውና እንዲጠናከር፣ የአፍሪካ ሕብረት ድርጅት በሁሉም መስኩ ጎልብቶ ዋንኛው የአፍሪካ ችግር ፈቺ ወሳኝ ኃይል ሆኖ እንዲወጣ የሚያደርግን እንቅስቃሴ በሙሉ የሚደግፍ ይሆናል፡፡>> ሲል ይጠቅሳል።

 

በፕሮግራሙ አንቀፅ 4.2.3 ላይ በግልፅ እንዳስቀመጠው ‹‹ ከዓለም አቀፍ ሕግጋትና ከታሪክ አንጻር አገራችን ራስዋ ባለቤት ሆና የምታስተዳድረው (sovereign ownership) የባህር በር እና መተላለፍያ (ኮሪዶር) የማግኘት መብት ሊኖረን እንደሚገባ ኢዜማ ያምናል፡፡ ከአካባብያችን እና ከሃገራችን ልዩ ሁኔታ አንጻር ሲታይ ደግሞ ይህን መብት የማስከበር ጉዳይ የኢኮኖሚ እድገት ብቻ ሳይሆን የሃገር ደህንነት እና የሃገር ህልውና ጉዳይ ነው ብሎ ያምናል፡፡ ይህን በሠላማዊ፣ ህጋዊና እና ዲፕሎማሲያዊ መስመር ብቻ ተግባራዊ ለማድረግ ይሰራል፡፡ ›› ይላል፡፡

 

በመሆኑም መንግሥት ይህንን መብት ለማረጋገጥ ሌሎች ጎርቤት ሀገራት ጋር በበቂ ሁኔታ እንዲያውቁ መደረጉን ቢገልጽም ጉዳዩ ከፍ ያለ የብሔራዊ ጥቅም በመሆኑ ዜጎች በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግ እና ሥምምነቱ ተፈጸመ ሲባል ከብሔራዊ ጥቅም ይልቅ የፖለቲካ አንድምታ ካላቸው እና ብዥታ ከሚፈጥሩ ዘገባዎች የመንግሥት ሚዲያዎች እንዲቆጠቡ እንጠይቃለን፡፡ በዓለም አቀፍ ቦታዎችም በበቂ ሁኔታ ዕውቀትን፣ ብቃትን እና ወጥነትን በተላበሰ መልኩ የዲፕሎማሲ ሥራ እንዲሰራ ጥሪ እናቀርባለን። በተጨማሪም መንግሥት ሌሎች አማራጭ የባህር በሮችን ለመጠቀም ከሌሎች ሃገራትም ጋር ውይይት ማድረጉን አጠናክሮ እንዲቀጥል እንጠይቃለን። ከዚህ ጋር በተያያዘ በተለይም ክልሎች ሕገመንግሥቱን በጣሰ መልኩ የፌደራል ሥልጣን የሆነውን የውጪ ግንኙነት ጉዳይን በቀጥታ ሲፈጽሙ የሚስተዋል ሲሆን ይህ የሃገሪቱ ሉዓላዊነት ላይ ይዞ የሚመጣው ችግር የከፋ ሊሆን ስለሚችል በቶሎ እርምት እንዲደረግ እንጠይቃለን።

 

ይህን መሰል ጉዳዮች ውጤታማ እንዲሆኑ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራ የሚገባው ዋነኛው ጉዳይ የውስጥ ሰላማችን ጉዳይ ነው፡፡ ሀገራችን በታሪክ ሂደት ብሔራዊ ጥቅሞቿን ማስከበር የተሳናት በውስጣችን ባለ አለመረጋጋት መሆኑን በመረዳት የዜጎችን ሰላምና ደህንነት በማስከበር ሃገሪቱ ውስጥ ያሉ ችግሮችን በትኩረት ቅድሚያ ሰጥቶ በውይይት እና መሰል ሁነቶች ለመፍታት መንግሥት ከፍተኛውን ጥረት ሊያደርግ እንደሚገባ ልናሳስብ እንወዳለን። 

 

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) 

ጥር 09/ 2016 ዓ.ም.