የኢትዮጵያ እና የሶማሊያን ውጥረት ለማርገብ ኦባሳንጆ ንግግር እንዲያስጀምሩ ተጠየቀ


የአፍሪካ ኅብረት የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል ያለውን ውጥረት ለማርገብ ንግግር እንዲያስጀምሩ ጠየቀ።

የኅብረቱ የሰላም እና የፀጥታ ምክር ቤት ረቡዕ ጥር 08/2016 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ ነው ይህን ምክረ ሐሳብ ያቀረበው።

ከሁለት ሳምንት በፊት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የግዛቴ አካል ናት የምትላት ሶማሊላንድ የባሕር በር ለመስጠት እና በምላሹ እንደ አገር ዕውቅና ለማግኘት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ በአፍሪካ ቀንድ ውጥረት መንገሱ ይታወቃል።

ሶማሊያ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የደረሰችው ስምምነት ሉዓላዊነቷን የሚጥስ መሆኑን በመግለጽ ውድቅ ያደረገችው ሲሆን፣ በከፍተኛ ባለሥልጣናቷ በኩልም ዛቻ እና ማስጠንቀቂያ ስትሰነዝር ቆይታለች።

ይህንን ውጥረት በተመለከተ ዛሬ ረቡዕ ስብሰባ ያደረገው የአፍሪካ ኅብረት የሰላም እና የፀጥታ ምክር ቤት የሁለቱን አገራት ተወካዮች አስተያየት ማድመጡን ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

በኅብረቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ተወካይ አምባሳደር አየለ ሊሬ እና የሶማሊያው አቻቸው አምባሳደር አብዱላሊ ዋርፋ ንግግር አሰምተዋል።

ምክር ቤቱ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ነጻ አገርነቷን ያወጀችው የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ የገቡትን ስምምነት ተከትሎ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል የተፈጠረውን ውጥረት በተመለከተ ውይይት አድርጓል።

በሁለቱ አገራት መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ተከትሎ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽነር ሙሳ ፋኪ ማሕማት መግለጫ ማውጣታቸው ይታወሳል።

ኮሚሽነሩ በመግለጫቸው የኢትዮጵያ እና የሶማሊያን ጨምሮ ሁሉም የኅብረቱ አገራት ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት መከበር እንዳለበት ጠቅሰዋል።

ምክር ቤቱ በዛሬው ስብሰባው ኢትዮጵያም ሆነች ሶማሊያ በኅብረቱ እና በዓለም አቀፉ ሕግ መሠረት ውጥረቱን እንዲያረግቡ ጥሪ አቅርቧል።

ምክር ቤቱ ባወጣው መግለጫ አክሎ የውጭ ኃይሎች በሁለቱ የኅብረቱ አባል አገራት መካከል ጣልቃ ከመግባት እንዲቆጠቡም አሳስቧል።

መግለጫው ጨምሮ ሁለቱ አገራት ያላቸውን የጎረቤትነት መንፈስ ከሚያውክ ተጨማሪ ተግበር እንዲቆጠቡ አሳስቦ አለመግባባታቸውን በንግግር እንዲፈቱም መክሯል።

የሰላምና የፀጥታ ምክር ቤቱ የኅብረቱ አፍሪካ ቀንድ ተወካይ የሆኑት የቀድሞው የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት ኦሌሴጉን ኦባሳንጆን በአስቸኳይ እንዲያሰማሩ ለአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ጥያቄ አቅርቧል።

ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ የኅብረቱ ሊቀመንበር የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው በኢትዮጵያ እና በሱዳን ውስጥ ያሉ ግጭቶች መፍትሄ እንዲያገኙ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወቃል።

ኦባሳንጆ በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት የተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት እንዲያበቃ ጉልህ ሚና ከነበራቸው አሸማጋዮች መካከል አንዱ ነበሩ።

የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ ውዝግብ ዙሪያ ለመነጋገር የጠራው አስቸኳይ ስብሰባ ነገ ሐሙስ ጥር 9/2016 ዓ.ም. በኡጋንዳ ካምፓላ ይደረጋል።

ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ባወጣው መግለጫ “በጊዜ መጨናነቅ” ምክንያት በስብሰባው ላይ መሳተፍ እንደማይችል መግለጹ እየተነገረ ነው።

የሶማሊያው ጠቅላይ ሚንስትር ሐምዛ አብዲ ባሬ ባለፈው ቅዳሜ ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት ውስጥ ለመግባት ዝግጁ ነን ሲሉ ተደምጠዋል።

ከዚህ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ሁለት ቀናት በፊት ደግሞ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ኢትዮጵያን የሶማሊያ “ጠላት” ሲሉ ገልጸዋታል።