ኢትዮጵያ አዲስ የታጠቀቻቸው ጄት እና ድሮን አቅማቸው ምን ያህል ነው?


የአገሪቱን ሠራዊት የውጊያ አቅም ይጨምራሉ የተባሉ ተዋጊ የጦር ጄት እና ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) የኢትዮጵያ አየር ኃይል መረከቡን ይፋ ተደርጓል።

አየር ኃይሉ ማክሰኞ ጥር 7/2016 ዓ.ም. የተረከበው ሩሲያ ሰራሹ ሱሆይ ሱ-30 ጦር ጀት እና ቱርክ ሰራሹን ባይራክታር አኪንቺ የተባለ ዘመናዊ ሰው አልባ አውሮፕላን ነው።

በርክክብ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የጦር አውሮፕላኖቹ ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ እንዲሁም የምርቶቹ አቅራቢያዎች እነማን እንደሆኑ በይፋ የተባለ ነገር የለም።

ይሁን አንጂ በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያው የአገሪቱ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች 1 ሱ-30 ተዋጊ ጄት እና 1 ባይራክታር አኪንቺ ድሮን ሲረከቡ ታይተዋል።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ሩሲያ ሰራሹን ሱ-30 ጦር ጄት “ምርጥ ኤርክራፍት” ሲሉ ገልጸውት፤ አየር ኃይል ዘመናዊውን የጦር ጀት መታጠቁ “ኢትዮጵያን በቀላሉ ለመተናኮል የሚፈልጉ ኃይሎች ከጥቃት እንዲቆጠቡ” ያደርጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል አዛዥ ሌ/ጄ ይልማ መርዳሳ፤ ተቋማቸው የተረከባቸው አውሮፕላኖች የመጀመሪያ ዙር መሆናቸውን በመናገር ወደፊት ተጨማሪ አውሮፕላኖች ሊረከቡ እንደሚችሉ አመልክተዋል።

“በከፍተኛ ሁኔታ የአየር ኃይልን የውጊያ አቅም የሚጨምሩ ናቸው። . . . በተመሳሳይ ጊዜ በአየር ላይ ውጊያ እንዲሁም ከአየር ወደ ምድር ዒላማዎቹን በተመሳሳይ ጊዜ ይመታል” ሲሉ ስለ የጦር ጄቱ ተናግረዋል።

ባይራክታር አኪንቺ

ይህ ድሮን ኢትዮጵያን ጨምሮ በዓለም ላይ በስፋት ጥቅም ላይ የዋለው ባይራክታር ቲቢ2ን ተከትሎ ተሻሽሎ የተሠራ ነው።

አምራቹ ባይራክታር እንደሚለው አኪንቺ የተባለው ሰው አልባ አውሮፕላን ተዋጊ ጀቶች መፈጸም የሚችሉት መከወን ይችላል። 

ሰው አልባ አውሮፕላኑ ከሰማይ ላይ ሆኖ በምድር ላይ ያለን ዒላማ ከመምታቱ በተጨማሪ በአየር ላይ ውጊያ አየር ላይ ሆኖ አየር ላያ ያለን ዒላማ የመምታት ብቃት አለው። 

ከባሕር ጠለል በላይ 40 ሺህ ጫማ (14 ኪሎ ሜትር) ከፈታ ላይ መብረር የሚችለው ይህ ድሮን፣ እስከ 24 ሰዓት ያለማቋረጥ አየር ላይ ከመቆየቱ በተጨማሪ እስከ 370 ኪሎ ሜትር በሰዓት ይከንፋል።

ባይራክታር ከሚያመርታቸው ሰው አልባ አውሮፕላኖች መካከል አኪንቺ ትልቁ እና የመጨረሻ ምርቱ ነው። ክንፎቹ 20 ሜትር ርዝመት ሲኖረው፣ ቁመቱ 12 ሜትር፣ ከፍታው ደግሞ 4.1 ሜትር ነው።

ሰው አልባ አውሮፕላኑ በራሱ ከመሬት መነሳት እና ማረፍ እንዲሁም ወደ መቆሚያው በመሄድ ቦታውን መያዝ የሚችል ነው።

ባይራክታር አኪንቺ ዒላማቸውን በትክክል መምተት የሚችሉ በጨረር የሚመሩ ቱርክ ሰራሽ ሚሳኤሎችን እንዲሁም እስከ 450 ኪሎ ግራም የሚመዝኑ ማርክ 83 የተባሉ አሜሪካ ሰራሽ ቦምቦችን ይታጠቃል።

ድሮኑ በነዳጅ የሚንቀሳቀሱ እያንዳንዳቸው 450 የፈረስ ጉልበት ያላቸው ሁለት ሞተሮች ያሉት ሲሆን፣ ያለማቋረጥ 5 ሺህ ኪሎ ሜትር መብረር ይችላል።

ይህ ድሮን እንደ ባይራክታር ቲቢ 2 ጦርነት ላይ ጥቅም ላይ ስለመዋሉ ሪፖርቶች ባይኖሩም የቱርክ ጦር ይህን ሰው አልባ አውሮፕን ከታጠቀ ሁለት ዓመታት አልፈዋል።

ሪፖርቶች እንደሚጠቀሙት ይህ ሰው አልባ አውሮፕላን ከቱርክ አየር ኃይል በተጨማሪ እንደ አዘርባጃን፣ ፓኪስታን እና ኪርጊዝታን ያሉ ጥቂት አገራት ታጥቀዋል።

ሳዑዲ አረቢያ ይህን ድሮን ለመግዛት ውል ስለመግባቷ ከዚህ ቀደም የወጡ ሪፖርቶች አሳይተዋል።

ኢትዮጵያ በሰው አልባ አውሮፕላን ግዢ ከቱርክ እና ከድሮን አምራቹ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጋር መልካም የሚባል ግንኙነት እንዳላት ይታወቃል።

ኢትዮጵያ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የቱርኩን ባይራክታር ቲቢ2 ድሮን ጨምሮ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በትግራይ አማጺያን ላይ መጠቀሟ የኃይል ሚዛን ለውጥ ማምጣቱ እሙን ነው።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል 88ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን ባከበረበት ወቅት ለድሮን አምራቹ ኩባንያ ባይራክታር ዋና ሥራ አስኪያጅ ሃሉክ ባይራክታር የክብር ሜዳሊያ መሸለሟ ይታወሳል።

ሱሆይ ሱ-30

በሶቪዬት ኅብረት መመረት የጀመረው ሱሆይ ሱ-30 የጦር ጄት ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ማሻሻያዎች እየተደረጉለት ጥቅም ላይ ሲውል ቆይቷል። 

ይህ የጦር ጄት ልክ እንደ ሰው አልባው አውሮፕላን ሁሉ በተመሳሳይ ጊዜ በአየር ላይ የጠላት አውሮፕላንን እና በምድር ላይ ያለ ዒላማውን በተመሳሳይ ጊዜ መምታት ይችላል።

ሱ-30 የጦር ጄት የተፈበረከው በቀደመው ሱ-27 ዝርያው ላይ ተመሥርቶ ነው። በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ አየር ኃይል ታጥቆት ከሚገኛቸው መካከል ሱ-27 እና ሩሲያ ሠራሽ ሚግ ጄቶች ተጠቃሽ ናቸው።

ከአሜሪካ ሠራሹ ኤፍ-16 የጦር ጄት ጋር የሚነጻጸረውን ሱ-30 ሁለት ሞተር ያሉት ሲሆን፣ ሁለት አብራሪዎችን ይዞ በየትኛውም የአየር ሁኔታ ውስጥ ተልዕኮውን እንዲወጣ ተደርጎ የተመረተ ነው። 

እነዚህ በጠላት ኃይል ላይ ከፍተኛ የበላይነት የሚሰጡት ሱ-30 ጄቶች ከቀደምቶቹ የሱ ዝርያ ጀቶች ዋና መለያዎች መካከል አንዱ በቀላሉ መገለባበጥ መቻሉ ነው።

ይህን ጄት በስፋት ታጥቀው ከሚገኙ አገራት መካከል ሩሲያ ቀዳሚዋ ናት። እየተካሄደ ባለው በዩክሬን ጦርነት ላይ ሞስኮ ሱ-30 አውሮፕላኖችን በስፋት አሰማርታለች።

ዩክሬን በዚህ ጦርነት ካርኪቭ ግዛት ውስጥ የሩሲያን ሱ-30 የጦር ጄት መትታ መጣሏን በተደጋጋሚ ገልጻለች።