በመርሐቤቴ ወረዳ ከትምህርት ቤት አቅራቢያ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ሁለት ሰዎች ተገደሉ


 

በአማራ ክልል መርሐቤቴ ወረዳ ከአንድ ትምህርት ቤት አቅራቢያ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ሁለት ሰዎች ሲገደሉ ቢያንስ አራት ሰዎች እንደቆሰሉ ነዋሪዎች እና የትምህርት ቤቱ አስተዳደር ለቢቢሲ ገለጹ።

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በምትገኘው መርሐቤቴ ወረዳ ዓለም ከተማ የድሮን ጥቃቱ የተፈጸመው ባለፈው ሳምንት አርብ ጥር 3/2016 ዓ.ም. መሆኑን ሦስት ነዋሪዎች እና የትምህርት ቤቱ አስረድተዋል። 

ከቀኑ ሰባት ሰዓት ገደማ የተፈጸመው ጥቃት ያረፈው አርበኞች አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መግቢያ አካባቢ መሆኑ የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አቶ አሻግሬ አበበ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ በተፈጸመው በዚህ የድሮን ጥቃት የተደናገጡት የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ባደረባቸው ስጋት ምክንያት በዛሬው ዕለት ሰኞ ወደ ትምህርት ቤት አለመመለሳቸውን ርዕሰ መምህሩ ጨምረው አረጋግጠዋል።

ከዘጠኝ እስከ 12ተኛ ክፍል የሚያስተምረው ትምህርት ቤቱ በዚህ ዓመት ከ2,600 በላይ ተማሪዎችን እንደተቀበለ ርዕሰ መምህሩ ገልጸዋል። 

ርዕሰ መምህሩ እና ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሁለት የከተማዋ ነዋሪዎች እንደሚያስረዱት በትምህርት ቤቱ አቅራቢያ ጥቃቱ የተፈጸመው በአካባቢው በሚገኘው “ካርል” የተባለ መናፈሻ ውስጥ የፋኖ ታጣቂዎች ይገኛሉ በሚል ነው።

ከትምህርት ቤቱ በ20 ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ይህ መናፈሻ የፋኖ ኃይሎች “ለሬሽን እና ሎጂስቲክስ አቅርቦት የሚጠቀሙበት” መሆኑን አንድ የትምህርት ቤቱ መምህር ለቢቢሲ ገልጸዋል። መምህሩ፤ “[በትምህርት ቤቱ እና መናፈሻው] መሃል ያለው አንድ አገር አቋራጭ መንገድ ነው። [ጥቃት የተፈጸመው] እነሱ ላይ እርምጃ እወስዳለሁ በሚል እሳቤ ነው። እርምጃው ወደ ተማሪውም ጭምር ያነጣጠረ ነው” ብለዋል።

እንደ ነዋሪዎቹ ገለጻ በዚህ የድሮን ጥቃት ሁለት የፋኖ አባላት የተገደሉ ሲሆን፣ በመንገድ ላይ የነበሩ ቢያንስ አራት ንጹሃንም ጉዳት ደርሶባቸዋል። ጥቃቱ በተፈጸመበት ሰዓት የሁለተኛ ፈረቃ ተማሪዎች በትምህርት ላይ እንደነበሩ የገለጹት ርዕሰ መምህሩ አቶ አሻግሬ፤ ተማሪዎች ላይ የተፈጠረው ድንጋጤ “ከልክ በላይ” የሚባል አይነት መሆኑን ገልጸዋል።

 

ርዕሰ መምህሩ፤ “አንዳንድ ተማሪዎች በአጥር ዘለው ሊወጡ ሲሉ እጃቸውን ቆርቆሮ የቆረጣቸው አሉ። [ጥቃቱ] የነበረው በፊት ለፊት በኩል ስለነበር [እና ጥቃቱ] ይደገማል ተብሎ ስለታሰበ በየአጥሩ እንዲወጡ ነው የተደረገው” ሲሉ ተማሪዎች ከትምህርት ቤቱ ቅጥር እንዲወጡ የተደረገበትን መንገድ አስረድተዋል።

አንድ የትምህርት ቤቱ መምህር በበኩላቸው፤ “የድሮን ጥቃቱ ሲፈጸም አካባቢው በጭስ እና በፍንጥርጣሪ በመታፈኑ ተማሪዎች በተፈጸመባቸው ረብሻ የተወሰኑ ተማሪዎች መስታወት በመስበር በመስኮት ለመውጣት [ሲሞክሩ] መጠነኛ የመቁሰል፣ የመውደቅ፣ የመሰበር አደጋ ደርሶባቸዋል” ሲሉ ተመሳሳይ ሃሳብ አንስተዋል።

በሳምንቱ የመጨረሻ የትምህርት ቀን የተፈጸመውን የድሮን ጥቃት ተከትሎ የተቋረጠው ትምህርት በዛሬው ዕለት አለመጀመሩን ርዕሰ መምህሩ እና ሌላ መምህር አስረድተዋል። ርዕሰ መምህሩ አቶ አሻግሬ፤ “ዛሬ [ወደ ትምህርት ቤት] ገብቼ ነበር። ነገር ግን አንድም ተማሪ ሳይመጣ ቀረ። እኔም ወጣሁ” በማለት ተማሪዎች ላይ ስጋት መፈጠሩን አመልክዋል።

“ትምህርት ቤት አካባቢ እንደዚህ ጥቃት መፈጸሙ ትምህርት እንዲቋረጥ የሚያደርግ ነው። አሁን የትኛው ተማሪ መጥቶልን እንደምናስተምር አናውቅም” ያሉት አቶ አሻግሬ፤ ጥቃቱ የመማር ማስተማር ሥራው ላይ ተጽእኖ ያደርሳል የሚል ስጋታቸውን ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ቢሮ በኅዳር ወር ላይ ባወጣው መግለጫ በአማራ ክልል ፋኖ ታታቂዎች እና በመንግሥት ኃይሎች የሚያደርጉትን ውጊያ ተከትሎ በሚፈጸሙ የድሮን ጥቃቶች ንጹሃን እየተገደሉ መሆኑን አስታውቆ ነበር።

በክልሉ በሰሜን ሸዋ ዋደራ ወረዳ ውስጥ በሚገኝ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህር ቤት ላይ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ሦስት መምህራንን ጨምሮ ሰባት ሰዎች እንደተገደሉ በመግለጫው ላይ ተጠቅሶ ነበር።

የፋኖ ታጣቂዎች በሚንቀሳቀሱበት በመርሐቤቴ ወረዳ ዓለም ከተማም የድሮን ጥቃት ሲፈጸም ይህ የመጀመሪያው አይደለም። በኅዳር ወር መጨረሻ ላይ “ገምሹ” በሚባል ካምፕ ላይ በተፈጸመ ጥቃት ሁለት ሰዎች እንደተገደሉ አንድ የከተማዋ ነዋሪ አስታውሰዋል። በዚህ ጥቃት “በርካታ ሰዎች” ጉዳት እንደደረሰባቸው የሚናገሩት ነዋሪው፤ በወቅቱ ጉዳት የደሰረባቸው “ንጹሃን” እንደነበሩ ጠቅሰዋል።

ቢቢሲ አርብ ዕለት በዓለም ከተማ ስለተፈጸመው ጥቃት ከመከላከያ ሠራዊት እና ከክልሉ ባለሥልጣናት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም። ይሁንና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ታኅሣሥ ወር ላይ ለመንግሥት ቅርበት ባለው ፋና ቴሌቪዥን በሰጡት ቃለ መጠይቅ በእነዚህ ጥቃቶች ንጹሃን እየተገደሉ ነው መባሉን አስተባብለዋል።

የመከላከያ ሠራዊት የድሮን ጥቃት የሚፈጽመው የፋኖ ታጣቂዎች “ስብስብ ዒላማ” ላይ መሆኑን የተናገሩት ኤታማዦር ሹም ብርሃኑ፤ “ሕዝብ ላይ ድሮን አይጣልም፤ አይተኮስም። መንደር ላይ እንኳ አይተኮስም። የጠላት ስብስብ ሲገኝ ግን ይተኮሳል” ብለው ነበር።

በክልሉ በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተለያዩ አካባቢዎች ለወራት እየተካሄደ ባለው ግጭት በርካታ ሰዎች መገደላቸው እና ያለ ፍርድ ግድያን ጨምሮ ከፍተኛ የመብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እና ሌሎችም ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወቃል።

መንግሥት የክልል ልዩ ኃይልን በማፍረስ መልሶ ለማደራጀት እና ሌሎች ታጣቂዎችን ትጥቅ ለማስፈታት መወሰኑን ተከትሎ ካለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ጀምሮ በአማራ ክልል የተከሰተው ውጥረት ተባብሶ ሐምሌ ወር መጨረሻ ላይ ወደለየለት ግጭት መግባቱ ይታወሳል።

በተለያዩ ጊዜያት መንግሥት የክልሉ አካባቢዎች ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እየተመለሱ መሆናቸውን ቢገልጽም፣ አሁንም በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች ውጊያ እንዳለ ይሰማል።

የተለያዩ የአገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች ወደ ድርድር እንዲመጡ እና በውይይት ችግራቸውን እንዲፈቱ ጥሪ እያቀረቡ ቢሆንም፣ እስካሁን የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች ስለመኖራቸው የሚጠቁሙ መረጃዎች የሉም።