ዝነኛው ፓስተር ጆሽዋ ሚሊዮን ተከታዮቹን ያታለለባቸው 6 ‘’የተአምራዊ ፈውስ’’ ዘዴዎች


ቢቢሲ ገናና የነበረውን ፓስተር ጆሽዋን እና በሴቶች ላይ መድፈርን ጨምሮ ያደርስ የነበረውን ስቃይ በምርመራ ጋዜጠኝነት ማጋለጡ ይታወሳል።

ፓስተር ጆሽዋ ሚሊዮን ተከታዮቹን የ‘’ተአምራት’’ ድርጊትን እፈጽማለሁ በማለት ሲያታልል ኖሯል።

ለ20 ዓመታት ሚሊዮኖችን እንዴት ሊያታልል ቻለ?

'ሽባዎችን' ከዊልቸራቸው ተነስተው እንዲዘሉ ያደርግ የነበረው እንዴት ነው?

ሙታንን አስነሳሁ ያለውስ ምን ዘዴ ተጠቅሞ ነው?

በ2004 የናይጄሪያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን እነዚህ ‘ተአምራት’ በቴሌቪዥን ለሕዝብ እንዳይተላለፉ አግዶ ነበር። በዚህን ጊዜ ነበር ዝነኛው ፓስተር ጆሽዋ ኢማኑኤል ቲቪን ከሳተላይት ማሰራጨት የጀመረው።

ይህ ዓለም አቀፍ የቴሌቪዥን የስብከትና ተአምራት ቴሌቪዥኑ በዓለም ላይ እጅግ ስኬታማ ከሚባሉት አንዱ ነበር።

ፓስተር ጆሽዋ ‘’ተአምራቱን’’ በዚህ ጣቢያ ለዓለም ሲያሰራጭ ከሩቅ ምሥረቅ እስከ አውሮፓ፣ ከሰሜን አሜሪካ እስከ ደቡብ ሚሊዮኖችን መድረስ ችሎ ነበር።

በመቶ ሚሊዮኖች መታየት የቻሉለት ተአምራቱ ለፖስተር ጆሽዋ አይነኬ እንዲሆን ምክንያት ነበሩ።

በ2021 ዓ/ም በ57 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ፓስተር ጆሽዋ የተዋጣለት 'አጭበርባሪ' ነበር።

የቢቢሲ ምርመራ እንዳጋለጠው ይህ የማጭበርበር ጥበቡ ከናይጄሪያ አልፎ በዩኬ፣ ጋና፣ ደቡብ አፍሪካ፣ አሜሪካና ጀርመን ጭምር የተቀነባበረ ነበር።

የሚከተሉት 6 የጆሽዋ ማጭበርበሪያ ስልቶችን እናስተዋውቃችሁ።

1- የድንገተኛ አደጋ ክፍል

በቤተ ክርስቲያኑ የድንገተኛ አደጋ ክፍል የሚባል አለ። የዚህ ክፍል ዋና ሥራው ሐሰተኛ ተአምራቱ እውነተኛ እንዲመስሉ ማስቻል ነው። 

ይህ ክፍል ታመው የሚመጡ የሚለዩበትና ለጆሽዋ ጸሎት የሚዘጋጁበት ነው።

ለ10 ዓመታት ይህን ክፍል የመራው አጎሞህ ፖል ለቢቢሲ እንደተናገረው የዚህ ክፍል አባላት በሕክምና የሰለጠኑ ዶክተሮች ናቸው።

ለምሳሌ እውነተኛ ካንሰር ያለበት ሰው ይባረራል። ሆኖም ግን የሚድን መለስተኛ ቁስል ያለበት ግን በካንሰር ስም ተማሚ ተደርጎ ይመዘገብና ወደ ጆሽዋ ክፍል ይተላለፋል።

ለታማሚዎቹ ልዩ ኮድ ይሰጣቸዋል። ለጆሽዋ ፍጹም ታማኝ የሆኑ ሰዎች ብቻ ናቸው እዚህ ክፍል መግባት የሚችሉት። ከዚያ በቀላሉ መዳን የሚችሉትን ጆሽዋ እንዲያውቃቸው ይነገረዋል። ከዚህ በኋላ ካሜራ እንዲመጣ ይደረጋል። እጁን ይጭንባቸዋል። ከዚያ ዳኑ ተብሎ እልል ይባላል።

“ነገሩ ውስብስብ ሂደት አለው። ጥቂት ምእመናን ብቻ ናቸው የማጭበርበሪያ ስልቱ የሚነገራቸው” ይላል ለ10 ዓመታት ይህን ክፍል የመራው ፓል ለቢቢሲ።

2- በሐኪም የሚታዘዝ መድኃነኒት

ከውጭ አገር ታመምን ብለው የሚመጡ ሰዎች ጆሽዋ ማረፊያ ሲደርሱ የያዟቸውን መድኃኒቶች እንዲጥሉ ይደረጋል።

ከዚያ ሙሉ የበሽታቸውን ሁኔታ የሚገልጽ ፎርም እንዲሞሉ ይደረጋል።

ከእንግዲህ መድኃኒቶቹን በፍጹም እንዳይወስዱ ይነገራቸዋል። ነገር ግን ጆሽዋ ፋርማሲ ባለሙያዎቹን ተመሳሳይ መድኃኒት እንዲያዘጋጁ ያደርጋል።

ከዚያ ተአምራዊ መጠጥ በሚባለው የፈውስ አገልግሎት ውስጥ መድኃኒቶቹ ይሰጧቸዋል። በሽተኞቹ ይህን አያውቁም። የሚያውቁት ጆሽዋ እንደጸለየባቸው ብቻ ነው።

ለምሳሌ በ1990ዎቹ ኤች አይ ቪ በአፍሪካ በከፍተኛ ሁኔታ በሚዛመትበት ዘመን ጆሽዋ ምእመኑን ወደ ቤት ሲመለሱ አንቲቫይራል መድኃኒት እንዳይወስዱ ይነግራቸው ነበር። ለጊዜው የተፈወሱ የሚመስላቸው ምእመናኑ ወደ አገራቸው ከተመሰሉ በኋላ ይሞታሉ።

3- ‘የአእምሮ እጥበት’

የጆሽዋ ዋናው ጥበብ የሰዎችን አስተሳሰብ ማጠብ ነው። የሚያዩትን ነገር እንዳይጠራጠሩ አድርጎ ማታለል። 

ሚስ ፎርድ ስትናገር ‘በዚያ ወቅት የማየውን በሙሉ አምን ነበር። ለምሳሌ ከዊልቸር ተነስቶ ሲዘል ሲራመድ ስመለከት አእምሮዬ በሱ አመነ’ ትላለች።

ይህ በጥንቃቄ የሚዘጋጀው የፈውስ ቴአትር ጆሽዋን ስኬታማ አድርጎታል።

የጆሽዋ ረዳት የነበረ አንድ ግለሰብ ይህን ሲያስረዳ ወደ አደባባይና ወደ ካሜራ ከመውጣታቸው በፊት ፈውስ ፈላጊዎች ችግራቸውን እንዲያጋንኑ ይነገራቸዋል ይላል።

“ችግራችሁን አተልቃችሁ ተናገሩ፤ ፈጣሪ ትልቅ በረከት እንዲሰጣችሁ፤ ፈውሳችሁም ትልቅ እንዲሆን ይረዳል” ተበሎ ይነገራቸዋል።

በዚህ ስሌት መሰረት መጠነኛ ችግር ያለባቸው በተቻለ አቅም ችግራቸውን አጋንነው እንዲያወሩ ይሆናሉ።

የጆሽዋ ቤተ ክርስቲያን የራሱ በቂ የሆኑ ዊልቼሮች አሉት። ተራምደው የመጡ ሰዎች እንኳ ቢሆኑ ዊልቸሩ ላይ ተቀምጠው ወደ መድረክ እንዲወጡ ይደረጋል።

“በዚህ ተአምራዊ ዊልቸር ካልተቀመጣችሁ ጆሽዋ አይጸልይላችሁም፤ ችግራችሁን አይፈታም እንላቸዋለን፤ ከጸለየላቸው በኋላ ደግሞ ዊልቸሩን ጥለው እንዲጮኹ እንነግራቸዋለን” ይላል የጆሽዋ ረዳት።

ቢሶላ የምትባልና 14 ዓመት ለጆሽዋ የሠራች ሴት ስትናገር በአንድ ወቅት በቂ ማጣራት ሳይደረግ የእውነት ሽባ የሆነ ሰው በዊልቸር ወደ ስቴዲየም ገባ። ጆሽዋ ፈውሻችኋለሁ ሲል ለመነሳት ሞክሮ ሲወድቅ አየሁት” ትላለች።

በአንድ ወቅት ጆሽዋ እንዲህ አለኝ ትላለች ቢሶላ፤ “አትጨነቂ ይህን የማደርገው (ለክፋት ሳይሆን) ብዙ ሰዎች ጌታ ላይ እምነት እንዲያሳድሩ ብዬ ነው።”

4- በጉቦ የሚተውኑ ምንዱባን

የጆሽዋ የቀድሞ ምእመናን እና ባልደረቦች ለቢቢሲ ሲናገሩ ራሳቸውን አካለ ስንኩላን መስለው እንዲተውኑ የሚዘጋጁ ሰዎች ጉቦ ይሰጣቸዋል።

ለምሳሌ አዲስ አገር ለፈውስ አግልግሎት ሲኬድ በቅድሚያ ምልመላ ይደረጋል። ምንዱባን የሚኖሩባቸው ሰፈሮች መልማዮች ይላኩና ጠቀም ያለ ገንዘብ ተሰጥቷቸው የሚተውኑ ሰዎች ይዘጋጃሉ።

ከዚያ የመድረክ ተውኔቱ ከመጀመሩ በፊት ለጆሽዋ እነዚህ ምልምል ተዋንያን የለበሱት ልብስና የቱ ጋ እንዳሉ ይነገረዋል። ከዚያ የእውነት ታማሚ ከሆኑ ሰዎች መሀል ይደረደራሉ። 

ጆሽዋ እነሱ ጋ ሲደርስ ያጠኑትን ይተውናሉ። ‘ተፈወስን’ ብለው ይዘላሉ። ለዚህ ጠቀም ያለ ጉቦ ይሰጣቸዋል።

5- ሐሰተኛ የሕክምና ሰርተፍኬት

ለሚሊዮኖች በጥንቃቄ ተሰናድቶ የሚሰራጨው የፈውስ አገልግሎት ብዙውን ጊዜ ኤች አይ ቪ የተያዙ ሰዎችን የመፈወስና ካንሰር የነበረባቸውን የማዳን ተግባር ያካትታል።

ዶክተሮች እነዚህ በሽተኞች መዳናቸውን በምስክርነት እንዲናገሩ ይደረጋል።

በ2000 ዓ/ም አንድ ሶይንካ የተባለ የናይጄሪያ ጋዜጠኛ እነዚህ የሕክምና ሰርተፍኬቶች ሐሰተኛ እንደሆኑ ደርሶባቸው ለማጋለጥ ሞክሮ ነበር። ነገር ግን ጉዳዩ የትም ሳይደርስ ተድበስብሶ ቀረ።

እስከዛሬም ግን ተፈውሰናል ብለው የሚያምኑ ሰዎች በርካታ ናቸው። 

“እውነታው ግን ሁሉም ነገር የተጠና ተውኔት ነው። የተውኔቱ ደራዊና አዘጋጅ ደግሞ ፓስተር ጆሽዋ ነው” ይላል ፖል።

6- ቪዲዮ ቅንብር

ተአምራት የሚባሉ ፈውሶች በሙሉ ይቀረጻሉ። ከዚያ ቪዲዮዎቹ በከፍተኛ ጥንቃቄ ይቀናበራሉ። ፈውሱ ከጆሽዋ ጸሎት በኋላ በቅጽበት የሆነ እንዲመስል ይደረጋል። ይሁንና ታማሚው ምናልባት ጤናው መሻሻል ያሳየው ከዓመት በኋላ ሊሆን ይችላል።

ነገር ግን ታማሚ ሳለና ከዚያ መሻሻል ሲያሳይ የሚቀረጹት ፊልሞች ይቀናበሩና ጆሽዋ ልክ ሲጸልይ ግለሰቡ የዳነ እንዲመስል ይደረጋል። ከዚያ ለሚሊዮኖች ይሰጠራጫል።

ይህን ለቢቢሲ ያጋለጠችው ደግሞ በጆሽዋ ኢማኑኤል ስቱዲዮ ለ5 ዓመታት በአቀናባሪነት ያገለገለችው ቢሶላ ናት።

“እውነተኛውን የቪዲዮ ክፍል ሰዎች እንዳያዩት ቆርጠን እናወጣለን፤ ሚሊዮኖች ያዩት ሁሉ ቅንብር ነው፤ ይህን የምለው ደግሞ እኔም አንዱ አቀናባሪ ስለነበርኩ ነው” ትላለች ቢሶላ።

ቢቢሲ በዚህ ጉዳይ ላይ አሁንም አገልግሎት ላይ ከሚገኘው ቤተ ክርስቲያን ማብራሪያ የጠየቀ ሲሆን ምላሽ አላገኘም።ከዚህ ቀደም ቤተ ክርስቲያኑ ባወጣው መግለጫ "በጆሽዋ ላይ የሚሰነዘሩት ትችቶች መሠረተ ቢስ ናቸው ብሎ ነበር።