ኢጋድ የኢትዮጵያና የሶማሌላንድ የመግባቢያ ስምምነት ተከትሎ በተፈጠረው ውዝግብ ላይ ለመወያየት አስቸኳይ ስብሰባ ጠራ


የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) የወቅቱ ሊቀመንበር የጂቡቲው ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌ፣ ኢትዮጵያና ሶማሌላንድ የተፈራረሙትን የመግባቢያ ስምምነት ተከትሎ፣ በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል በተፈጠረው ውዝግብና በወቅታዊ የሱዳን ቀውስ ላይ ለመወያየት ልዩ ስብሰባ ጠሩ።

የጂቡቲው ፕሬዚዳንት ከኡጋንዳው አቻቸው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ጋር በስልክ ተመካክረው፣ ኡጋንዳ ስብሰባውን እንድታስተናግድ ያቀረቡላቸውን ጥያቄ መቀበላቸውን፣ የጂቡቲ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስቴር ያወጣው መግለጫ አመልክቷል። በዚህም መሠረት የተጠራው የኢጋድ ልዩ ጉባዔ በቀጣዩ ሳምንት ሐሙስ ታኅሳስ 9 ቀን 2016 ዓ.ም. እንደሚካሄድ አስታውቋል።

ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌ ልዩ የኢጋድ ስብሰባውን የጠሩት፣ የተለመደውን አሠራር ተከትለው፣ በኢጋድ ጽሕፈት ቤት በዋና ጸሐፊው በወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) በኩል ሳይሆን፣ በኢጋድ ሊቀመንበርነታቸው በቀጥታ መሆኑ ታውቋል።

በመሆኑም በአስቸኳይ ስብሰባው ለሚሳተፉ የኢጋድ አባል አገሮች፣ እንዲሁም ለአፍሪካ ኅብረትና ለዓለም አቀፍ አጋሮች ይፋዊ ግብዣ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ የመላክ ኃላፊነትን የጂቡቲ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስቴር ወስዷል።

በጂቡቲ የሚገኘው የኢጋድ ጽሕፈት ቤት በስብሰባው የሚሳተፉ የኢጋድ አባል አገሮች ተወካዮች በታቀደው ቀንና ቦታ እንዲገኙ አስፈላጊውን የማመቻቸት ኃላፊነት እንዲወጣ፣ ስብሰባውንም ከሚመለከታቸው የኡጋንዳ መንግሥት አካላት ጋር ተባብሮ ለማዘጋጀት የሚያስፈልገውን ተገቢ ዕርምጃ እንዲወስድ የጂቡቲ ፕሬዚዳንት ማዘዛቸው ታውቋል።

ኢትዮጵያና ሶማሌላንድ ታኅሳስ 22 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በመግባቢያ ስምምነቱ ከተካተቱ ይዘቶች መካከል፣ ሶማሌላንድ በግዛቷ ውስጥ ለኢትዮጵያ ባህር ኃይል መቀመጫና የባህር በር እንደምትሰጥ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ደግሞ ከሶማሊያ ተገንጥላ ራስ ገዝ አስተዳደር ላቋቋመችው ሶማሌላንድ ዕውቅና ለመስጠት፣ እንዲሁም ሶማሌላንድ በሊዝ ለምትሰጠው የባህር በር የሊዝ ዋጋ ጋር የሚስተካከል ድርሻ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ ለመስጠት ተስማምቷል።

የዚህ ስምምነት ይፋ መሆንን ተከትሎ ሶማሊያ ሉዓላዊነቷንና የግዛት አንድነቷን የሚጥስ ተግባር በኢትዮጵያ መንግሥት እንደተፈጸመባት እየከሰሰች ሲሆን፣ የመግባቢያ ስምምነቱንም ውድቅ አድርጋዋለች። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ የአሜሪካ መንግሥትና ሌሎች በርካታ የዓለም አገሮች የሶማሊያን አቤቱታ በመቀበል ለሶማሊያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት አጋርነታቸውን አሳይተዋል።

የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሐመድ በተጠናቀቀው ሳምንት በኤርትራ ተገኝተው በጉዳዩ ዙሪያ የተወያዩ ሲሆን፣ ይህንን ተከትሎም የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኤርትራ ተገኝተው በጉዳዩ ላይ መምከራቸው ታውቋል። በተጨማሪም ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ግብፅ ተገኝተው ተጨማሪ ውይይት እንዲያደርጉ በፕሬዚዳንት አልሲሲ መጋበዛቸው ታውቋል።

የመግባቢያ ስምምነቱ መፈረምን ተከትሎ ዲፕሎማሲያዊ ጫና የበረታባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ዓርብ ጥር 3 ቀን 2016 ዓ.ም. ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበርና ከኢጋድ ዋና ጸሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ ጋር በምዕራብ ሸዋ በወንጪ ያስገነቡትን ሪዞርት ሲጎበኙ ታይታዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር) በኢትዮጵያ ላይ ዲፕሎማሲያዊ ጫናው ቢበረታም፣ ኢትዮጵያ ይህንን እንደምትወጣው ዓርብ ዕለት በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሠፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።

‹‹የታላቁ ህዳሴ ግድብን ግንባታ ያሳካነው ተጨብጭቦልን ሳይሆን ከቅርብም ከሩቅም እየተላጋን፣ የሥጋት ከበሮ እየተደለቀ፣  ዛቻና ማስፈራሪያ በምድርም በአየርም ልምምድ እያስገመገመብን፣ ሁሉንም ዓይነት ጫና ተቋቁመን ነበር፤›› ያሉት ሬድዋን (አምባሳደር)፣ ‹‹የባህር በር ጉዳይም እንዲሁ ይሆናል፤›› ብለዋል።