በሶማሊላንድ እና ሶማሊያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጥቃት እና ዛቻ እየተፈጸመብን ነው አሉ


ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ለኢትዮጵያ የባሕር ጠረፍ ያስገኛል የተባለውን የመግባቢያ ሠነድ መፈራረማቸውን ተከትሎ በሶማሊያ እና ሶማሊላንድ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ አካላዊ ጥቃት እና የንብረት ዝርፊያዎች እየተፈጸሙ መሆኑን እንዲሁም ማስፈራሪያዎች እየደረሱ እንደሆነ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ተናገሩ። 

በተለይ በሶማሊላንድ በኢትዮጵያውያን ላይ አካላዊ ጥቃት መፈጸሙን፣ ንብረታቸው መዘረፉን እና መኖሪያ ቤታቸውን ለማቃጠል ሙከራ መደረጉን የስደተኞች ተወካይ ለቢቢሲ ተናግረዋል። 

በሶማሊያም በኢትዮጵያውያን ላይ ጥቃት እንዲፈጸም የሚጠይቁ ቅስቀሳዎች መኖራቸውን ኢትዮጵያውያኑ በተለይ ለቢቢሲ ተናግረዋል። 

ኢትዮጵያ ራስ ገዝነትን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የባሕር በር ማግኘት የሚያስችላትን የመግባቢያ ሠነድ ታኅሣሥ 22/2016 ዓ.ም. መፈራረሟ ይታወሳል።

ይህ ስምምነት ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ ለወደብ እና ለጦር ሠፈር ልማት የሚውል 20 ኪሎ ሜትር የባሕር ጠረፍ እንድታገኝ ያስችላታል የተባለ ሲሆን፣ በምላሹ ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ድርሻ እንዲሁም እንደ አገር ከአዲስ አበባ እውቅና እንደምታገኝ ተዘግቧል።

ታዲይ ይህን ስምምነት የአዲስ አበባ እና ሐርጌሳ መንግሥታት ታሪካዊ ብለው ቢያወድሱትም በሐርጌሳ እና ሞቃዲሹ የተለያዩ ስሜቶችን አስተናግዷል።

ስምምነቱ ከሶማሊያ በኩል በአገሪቱ አስተዳደር ጠንካራ ትችት የቀረበበት ሲሆን፤ በአንዳንድ የሶማሊያ ከተሞችም ስምምነቱን የሚያወግዝ የተቃውሞ ሰልፎች በስፋት ተካሂዷል።

በሶማሊላንድ ደግሞ ለስምምነቱ ድጋፍ የሚሰጡ ሰልፎች የመካሄዳቸውን ያህል በተቃራኒው በአንዳንድ አካባቢዎች ለተቃውሞ የወጡ ሰዎችም አሉ።

በሶማሊላንድ የአፍሪካ ቀንድ፣ የምስራቅ እና የመካከለኛው አፍሪካ ስደተኞች ተወካይ የሆኑት ኢትዮጵያዊው ኢብሳ አሊሾ ሃቢብ ከስምምነቱ መፈረም በኋላ በሰዎች ላይ አካላዊ ጥቃት መፈጸሙን እንዲሁም የኢትዮጵያውያን ንብረት መዘረፉን እና መኖሪያ ቤት ለማቃጠል ሙከራ መደረጉን ለቢቢሲ ተናግረዋል። 

ኢብሳ አሊሾ በሐርጌሳ “ስምምነቱ መፈረሙ የተገለጸ ዕለት ሰዎች ደስታቸውን ለመግለጽ አደባባይ ወጥተው ነበር” ይላሉ። ይሁን እንጂ እንደ ኢብሳ ገለጸ ከሆነ ከሦስት ቀናት በኋላ ደስታውን ለመግለጽ የወጣው ሕዝብ ስምምነቱን ተቃውሞ ዳግም አደባባይ መውጣት ጀምሯል። 

ኢብሳ በሁለተኛዋ ትልቋ የሶማሊላንድ ከተማ በሆነችው ቦርኦ ስምምነቱን የሚደግፍ እና የሚቃወም ሰልፍ ሲካሄድባት እንደቆየም ይገልጻሉ። 

“ከስምምነቱ ሦስት ቀናት በኋላ ጠዋት ላይ የድጋፍ ሰልፍ ነበር፤ ማታ ላይ ደግሞ የተቃውሞ ሰልፍ ተካሂዷል” ካሉ በኋላ በከተማዋ በተለይ የኦሮሞ ተወላጆች በሚኖሩበት አካባቢ ላይ ትኩረት በማድረግ “በእኛ ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ለማድረስ፣ ንብረት ለመዝረፍ፣ ቤታቸውን በእሳት ለማቃጠል ሙከራ ተደርጓል” ብሏል። 

ኢብሳ በቦርኦ ከተማ ቀጥለው የተካሄዱ የተቃውሞ ሰልፎችን ተከትሎ በኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ ጉዳት መድረሱን እና ንብረታቸው መዘረፉን ተናግረዋል። 

ይህ የስደተኞች ተወካይ እንደሚሉት ስደተኛ ነዋሪዎች ስጋታቸውን ለሶማሊላንድ ባለስልጣናት ካሳወቁ በኋላ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በስፋት በሚገኙባቸው መንደሮች የፖሊስ ኃይል ተሰማርቶ እንደነበረ ይገልጻሉ። 

በቦርኦ ከተማ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሰልፍ ከወጡ በኋላ “የኦሮሞ ተወላጅ ቤቶችን ዒላማ በማድረግ ንብረታቸውን ዘርፈዋል። ከዚህ በተጨማሪም የ70 ዓመት እና የአምስት ዓመት ታዳጊ ላይ የአካል ጉዳት አድርሰዋል” ብለዋል።

እርሳቸው በሚኖሩባት የሶማሊላንድ መዲና ሐርጌሳ እንዲሁ በተፈጸም ጥቃት አንድ የ12 ዓመት ታዳጊ ጉዳት ደርሶበት በሆስፒታል እንደሚገኝ ተናግረዋል። 

የስደተኞች ተወካዩ ጨምረው እንደገለጹት በሶማሊኛ ቋንቋ “ኢትዮጵያዊ ላይ በተገኘበት እርምጃ ይወሰድበት” የሚል በራሪ ጽሑፍ በሐርጌሳ ከተማ እየተበተነ መሆኑን ይገልጻሉ። 

ይህ ጊዜ በሶማሊላንድ ለሚገኘው 40ሺህ ለሚሆነው ኢትዮጵያዊ ስደተኛ በጣም አሳሳቢ ወቅት ነው ይላሉ።

በተመሳሳይ በሶማሊያ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውን ስደተኞች ከስምምነቱ መፈረም በኋላ የደኅንነት ስጋት እንዳለባቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል። 

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ሁለት ስደተኞች ምንም እንኳ እስካሁን ድረስ በአካል እና በንብረት ላይ የደረስ ጉዳት ስለመኖሩ እርግጠኛ ባይሆኑም ሁኔታዎች በጣም አሳሳቢ ሆነዋል ይላሉ። 

“እዚህ ያለው አብዛኛው ስደተኛ ሶማሊኛ ቋንቋ ይናገራል፤ እንደ ሶማሌ ሆኖ ነው የሚኖረው። ምንም ችግር አልነበረም። ከስምምነቱ መፈረም በኋላ ግን በጣም አስፈሪ ነገር ነው ያለው። ምን ሊፈጠር እንደሚችል አናውቅም” ብለዋል ቢቢሲ ካነጋገራቸው ስደተኞች አንዱ።

የስምምነቱን መፈረም ተከትሎ በተለይ በመዲናዋ ሞቃዲሹ በርካታ የተቃውሞ ሰልፎች መካሄዳቸውን እና በከተማዋ ኢትዮጵያ ጠል የሆኑ ስሜቶች እየበዙ መሆኑን መኖሪያቸውን በሞቃዲሹ ያደረጉ ሌላ ነዋሪ ተናግረዋል። 

የሶማሊያ ፌደራል መንግሥት ኢትዮጵያ እና ራስ ገዟ ሶማሊላንድ የደረሱት ስምምነት ሕጋዊ መሠረት የሌለው እና ተፈጻሚ ሊሆን የማይችል ነው ከማለቱም በተጨማሪ ስምምነቱ የአገሪቱን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት የሚጥስ መሆኑን በመጥቀስ አጥብቆ መቃወሙ ይታወሳል። 

እንደ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን አሃዝ ከሆነ አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን እና የየመን ዜጎች የሆኑ ወደ 36ሺህ የሚጠጉ ስደተኞች በሶማሊያ ይኖራሉ። 

በአንጻሩ ከ336ሺህ የማያንሱ የሶማሊያ ስደተኞች በኢትዮጵያ ይኖራሉ። እንደ ተመድ ከሆነ የሶማሊያ ስደተኞች በዶሎ አዶ በሚገኙ አምስት የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ወደ 215 ሺህ ስደተኞች ተጠልለው ይገኛል። 

ጂግጂጋ እና አዲስ አበባ ደግሞ ሌሎች የሶማሊያ ስደተኞች በስፋት የሚገኙባቸው የኢትዮጵያ ከተሞች ናቸው።