የሶማሊላንድ መከላከያ ሚንስትር ከኢትዮጵያ ጋር የተደረሰውን ስምምነት በመቃወም ስልጣናቸውን


ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የተፈራረሙትን የመግባቢያ ሠነድ በመቃወም የሶማሊላንድ መከላከያ ሚንስትር አብዲጋኒ መሐሙድ አቴዬ በገዛ ፍቃዳቸው ስልጣን መልቀቃቸውን ይፋ አደረጉ። 

ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ተገንጥላ ራስ ገዝ ከሆነችው ሶማሊላንድ ጋር የባሕር በር ማግኘት የሚያስችላትን የመግባቢያ ሠነድ ከአንድ ሳምንት በፊት ሰኞ ታኅሣሥ 22/2016 ዓ.ም. መፈራረሟ ይታወሳል።

ይህ ስምምነት ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ ለወደብ እና ለጦር ሠፈር ልማት የሚውል 20 ኪሎ ሜትር የባሕር ጠረፍ እንድታገኝ ያስችላታል የተባለ ሲሆን፣ በምላሹ ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ድርሻ እንዲሁም እንደ አገር ከአዲስ አበባ እውቅና እንደምታገኝ ተዘግቧል።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ‘ታሪካዊ’ ብለው የገለጹት ይህ የጋራ የመግባቢያ ሠነድ መፈረም ከአዲስ አበባ፣ ሐርጌሳ እና ሞቃዲሹ የተለያዩ ስሜቶችን አስተናግዷል። 

ስምምነቱ ከሶማሊያ በኩል በአገሪቱ አስተዳደር ጠንካራ ትችት የቀረበበት ሲሆን፤ በአንዳንድ የሶማሊያ ከተሞችም ስምምነቱን የሚያወግዝ የተቃውሞ ሰልፍ ተካሂዷል። 

በሐርጌሳ ደግሞ ለስምምነቱ ድጋፍ የሚሰጡ ሰልፎች እንደመካሄዳቸው ሁሉ በተቀረው የሶማሊላንድ አካባቢዎች ለተቃውሞ የወጡ ሰዎችም አሉ።

የመግባቢያ ሠነዱን በመቃወም ስልጣናቸውን በገዛ ፍቃዳቸው መልቀቃቸውን ይፋ ያደረጉት የሶማሊላንድ መከላከያ ሚንስትር፤ፕሬዝዳንቱ ስለ ስምምነቱ ከካቢኔያቸው ጋር ቀድመው አልተነጋገሩም ሲሉ ከሰዋል። 

አብዲቃኒ ሞሐሙድ አቴዬ የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ ከኢትዮጵያ ጋር የደረሱትን የወደብ ስምምነቱን በተመለከተ ቀደም ብለው ለሚንስትሮች ምክር ቤት አላሳወቁም ብለዋል። “ስለ ስምምነቱ የሚንስትሮች ምክር ቤትን አላማከሩም። . . . ስለ ስምምነቱ የሰማነው ከመገናኛ ብዙሃን ነው” ብለዋል።

ስልጣን የለቀቁት ሚንስትር የትውልድ ቦታቸው ኢትዮጵያ የባሕር ኃይል ጦር ሰፈር መገንባት የምትፈልግበት ሉጋሃያ ከተማ መገኛ የሆነው አዋዳል ክልል ነው።

የሶማሊያ መንግሥት አዲስ አበባ እና ሐርጌሳ የደረሱትን ስምምነት አጥብቆ ሲትች ቆይቷል። 

የፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ መንግሥት ስምምነቱንም “በሶማሊያ ነጻነት፣ ሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነት እና የሶማሊያ ፌደራላዊ ሪፐብሊክ ላይ የተቃጣ ጥቃት ነው” ብሎታል።

ትናንት ደግሞ ፕሬዝዳንቱ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የገባችውን ስምምነት “ውድቅ የሚያደርግ” ያሉትን ሕግ ፈርመው አፅድቀዋል።

ፕሬዝደንቱ በኤክስ ገፃቸውን “. . . የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሶማሊላንድ የገቡትን የመግባቢያ ሰነድ ውድቅ የሚያደርግ ሕግ ፈርሚያለሁ” ካሉ በኋላ የፈረሙት ሕግ “አንድነታችንን እና ሉዓላዊነታችንን እንዲሁም የግዛት አንድነታችንን ለመጠበቅ” ወሳኝ ነው ብለዋል።

ሶማሊላንድን እንደ አንድ ግዛቷ የምትቆጥረው ሶማሊያ ጠ/ሚ ዐቢይ እና ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሂ የገቡትን ስምምነት በመቃወም አምባሳደሯን ከአዲስ አበባ መጥራቷ ይታወሳል። 

አሁን ላይ እየወጡ ያሉ ያልተረጋገጡ ሪፖርቶች በሶማሊያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ከአገር እንዲወጡ መደረጋቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።